ጦሃራና ውሃዎች

6281

 

 

 

የጦሃራ ትርጓሜ

ጦሃራ የቋንቋ ትርጉሙ

ከቆሻሻዎች መጽዳትና ንጹሕ መሆን

ጦሃራ ሸሪዓዊ ትርጓሜው

ሐደሥን (ሶላትና ጠዋፍን የመሳሰሉ ዕባዳዎችን ከማከናወን የሚከለክሉ የንጽሕና - ጦሃራ - መጓደል ሁኔታን) እና ነጃሳን ማስወገድ

የጦሃራ ዓይነቶች

1 - ሕሊናዊ ጦሃራ

ሕሊናዊ ጦሃራ የልብ ከሽርክ፣፤ከኃጢአቶችና ካጎደፈው ነገሮች ሁሉ መጽዳትና ንጹሕ መሆን ነው፡፡ ልብ ውስጥ የሽርክ (በአላህ የማጋራት) ነጃሳና ርክሰት እያለ ጦሃራና ንጽሕና እውን መሆን አይችልም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው፤ከዚህም ዓመታቸው (ዘጠነኛው ዓመተ ህጅራ) በኋላ የተከበረውን መስጊድ አይቅረቡ፣ድኽነትንም ብትፈሩ አላህ ቢሻ ከችሮታው በእርግጥ ያከብራችኋል፤አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡›› [አል-ተውባህ፡28]

የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አማኝ (ሙእምን) ሰው አይረክስም (ነጃሳ አይሆንም)፡፡› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

2 - አካላዊ ንጽሕና

አካላዊ ንጽሕና የገላ ከሐደሦችና ከርክሰቶች ሁሉ ንጹሕና ጽዱ መሆን ነው ፡፡ እሱም በሁለት ይከፈላል ፡-

1-ከሐደሥ ንጹሕ መሆን

ሐደሥ ፡- ማለት በገላ ላይ ተከስቶ አንድን ሙስሊም፣ጦሃራ ቅድመ ሁኔታ (ሸርጥ) የተደረገባቸውንና እንደ ሶላትና ጠዋፍ (በተከበረው ቤት ዙሪያ መዞርን) የመሳሰሉ ዕባዳዎችን እንዳያከናውን የሚያግደው ክስተት ነው፡፡ ሐደሥ በሁለት ይከፈላል፡-

መለስተኛ ሐደሥ መለስተኛ ሐደሥ ዉዱእ ማድረግን ግዴታ የሚያደርግ እንደ ውሃ ሽንት፣ ዓይነምድርና ዉዱእ አፍራሽ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ የሚያካትት ክስተት ነው፡፡ አላህ U እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሶላት በቆማችሁ ጊዜ (ለመቆም ባሰባችሁ ጊዜ ፊቶቻችሁን እጆቻችሁንም እስከ ክርኖች እጠቡ፡፡ ራሶቻችሁንም (በውሃ) እበሱ፡፡ እግሮቻችሁንም እስከ ቁርጭምጭሚቶች ድረስ እጠቡ፡፡ . . ›› [አል-ማኢዳህ፡6]

ከፍተኛው ሐደሥ ከፍተኛው ሐደሥ እንደ ግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ እንደ ወር አባባና የመሳሰሉ ነገሮች ምክንያት ገላን የመታጠብ ግዴታ የሚያስከትል ክስተት ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ . . . (በከፍተኛው ሐደሥ ምክንያት) የረከሳችሁም ብትኾኑ (ገላችሁን) ታጠቡ፡፡ . . . ›› [አል-ማኢዳህ፡6]

በውሃ ዉዱእ ማድረግ ወይም ገላን መታጠብ አስቸጋሪ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ንጽሕና መስጫው ተየሙም (ደረቅ ዉዱእ) ይሆናል፡፡ አላህ U እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ፡፡› [አል-ማኢዳህ፡6]

ሐደሥ (የንጽሕና ብቃትን የሚያሳጣ ክስተት) ሶላት መስገድን ይከለክላል
ዉዱእና ጦሃራ ለመለስተኛው ሐደሥ
ገላን መታጠብ ለከፍተኛው ሐደሥ

2-ከቆሻሻ መጽዳት

ከነጃሳ (ቆሻሻና ርክሰት) ንጹሕ ሆኖ መጽዳት የሚፈጸመው ቆሻሻን ከገላ ከልብስና ከዕባዳ ማከናወኛ ቦታ ላይ ማስወገድ ነው፡፡ ርክሰትንና ቆሻሻን ማስወገድ ግዴታ (ዋጅብ) ነው፡፡ ይህም አላህ ፡- ‹‹ልብስህንም አጥራ፡፡›› [አል-ሙደሢር፡4]

ባለው መሰረትና ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹አብዛኛው የመቃብር ውስጥ ሥቃይ በሽንት ምክንያት (ከነጃሳው ባለ መጠበቅ) ነው፡፡›› [በእብን ማጀህ የተዘገበ]

ባሉት መሰረት ነው፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹አንዳችሁ ወደ መስጊድ ከመጣ ጫማዎቹን ይመልከትና ቆሻሻ ወይም የሚያውክ ነገር ካየባቸው መሬት ላይ ይጠራርገውና ይስገድባቸው፡፡›› [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

ገላን ንጹሕ ማድረግ
ልብስን ንጹሕ ማድረግ
ቦታን ንጹሕ ማድረግ

የውሃ ዓይነቶች

አንደኛ፡ ንጹሕ (ጠሁር) ውሃ

ጠሁር ውሃ ለራሱ ንጹሕ ሆኖ ለሌላውም በንጽሕና መስጫነት የሚያገለግል ውሃ ነው፡፡ ምሳሌው፡-

1 - ሙጥለቅ (ተፈጥሯዊ ባህሪይውን እንደ ያዘ የሚገኝ) ውሃ

ሙጥለቅ ውሃ የተፈጥሮ በህሪይውን እንደ ያዘ የሚገኝ ከሰማይ የሚወርድ እንደ ዝናም፣ በረዶ፣አመዳይ [አመዳይ (በረድ)፡- ከበረዶ ባነሰ ጥቃቅን ጠጣር መልክ ከዳመና የሚወርድ ውሃ ነው፡፡] ፣ያለም ይሁን በመሬት ገጽ ላይ የሚፈስ እንደ ባሕር ፣ወንዝ፣የዝናምና የመሳሰለውን ነው፡፡

አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ከሰማይም አጥሪ ውሃን አወረድን፤›› [አል-ፉርቃን፡48]

በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ . . . ውሃንም በርሱ ሊያጠራችሁ፣ . . ከሰማይ ባወረደላችሁ ጊዜ (አስታውሱ) ፡፡›› [አል-አንፋል፡11]

ነቢዩ ﷺ ዱዓእ ሲደርጉ እንዲህ ይሉ ነበር፡- ‹‹አላህ ሆይ ! ከኃጢአቶቼ በበረዶ፣በውሃና በአመዳይ እጠበኝ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

የባሕር ውሃን በማስመልከትም እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እርሱ (ባሕር) ውሃው ንጹሕ፣ እውስጡ የሚኖር የሞተ እንስሳው የተፈቀደ (ሳይታረድ ሐላል) የተደረገ ነው፡፡›› [በአሕመድና አቡ ዳዉድ የተዘገበ]

ዝናም
ወንዞች
ባሕሮች
የውሃ ጉድጓዶች

2 - ያገለገለ (ሙስተዕመል) ውሃ

ያገለገለ (ሙስተዕመል) ውሃ ዉዱእ ከሚያደርግ ወይም ገላውን ከሚታጠብ ሰው ገላ ላይ የወደቀ እጣቢ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱን ውሃ ለንጽሕና መስጫነት መጠቀም ችግር የለውም፡፡ ማስረጃው ከእብን ዐባስ የተላለፈው የሚከተለው ሐዲሥ ነው፡፡ ‹‹ከነብዩ ﷺ ባለቤቶች አንደኛቸው በጀፍነህ [ትልቅ ጥስት ዌም ሳፋ ዓይነት ዕቃ] (ጥስት መሰል የውሃ ዕቃ) ታጠቡና የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከዚ ውሃ ዉደእ ማድረግ ፈለጉ፡፡ ባለቤታቸው ግን አላህ መልእክተኛ ሆይ! ጁኑብ (ገላን የመታጠብ ግዴታ ያለብኝ) ሆኜ የታጠብኩበት ነው አሏቸው፡ (ነቢዩም) ፡- ‹ውሃ ግን ጁኑብ አይሆንም (አይረክስም)፡፡› አሏቸው፡፡›› [በትርምዚ ተዘገበ]

3 - ንጹሕ (ጣህር) የሆነ ነገር የተቀላቀለበት ውሃ

ይህ ንጹሕ የሆነ እንደ የዛፍ ቅጠል፣ አፈር፣ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ ዝግት ያለ ነገር የተቀላቀለበት ሆኖ ውሃ የሚያሰኘውን ስም በሚያሳጣው ደረጃ ለውጥ ያላስከተለበት ውሃ ነው፡፡ ይህን አስመልክተው ነብዩ ﷺ የሴት ልጃቸውን አስከሬን ሲያጥቡ ለነበሩ ሴቶች፡- ‹‹ሦስት ጊዜ፤ወይም አምስት ጊዜ፤(አስፈላጊ ከሆነም) ከዚያም በላይ በውሃና በቀርቁራ [ሲድር የቁርቁራ ዛፍ ቅጠል ሲሆን ተፈጭቶ ለንጽሕና መስጫነት ያገለግላል፡፡] ቅጠል እጠቧት፤የመጨረሻውን ከካፉር ጋር አድርገት፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

አፈር የተቀላቀለበት ውሃ
የውሃ ማጠራቀሚያ ዝገት
የዛፍ ቅጠል የተቀላቀለበት ውሃ
የውሃ መለወጥ
ውሃ ለውጥ በሚያስከትልበትና ከውሃነት ወደ ሌላ ነገር በሚቀ ይረው እንደ ሻይ፣ጭማቂ ወይም ሌላ ነገር ከተለወጠ ለንጽሕና መስጫነት መጠቀም ትክክለኛ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውሃ ተብሎ አይጠራምና፡፡
መረቅ
ቀለም
ሻይ
የፍራፍሮ ጭማቂ

4 - ነጃሳ የሆነ ነገር የተቀላቀለበትና ከውሃነት ግን ያልቀየረው

ይህ ደግሞ እንደ ሽንት ወይም የበከተ እንስሳና የመሳሰለሉ ጥቂት ነጃሳ ነገሮች ገብተውበት ከባሕርያቱ አንዱም ያልተለወጠ ውሃ ነው፡፡ እነዲህ ዓይነቱ ውሃ ንጹሕና ለንጽሕና መስጫነት ያገለግላል፡ ነብዩ ﷺ፡- ‹‹ውሃ ንጹሕና ንጽሕና ሰጪ (ጠሁር) በመሆኑ ምንም ነገር አያረክሰውም፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ]

ብለዋልና፡፡ ይህም ሰዎች በውሃ ጉድጓዶች አካባቢ ቆሻሻ ይጥሉ ነበር፡፡ ቆሻሻው በጎርፍ አማካይነት ወደ ውሃ ጉድጓዱ ገብቶ ቢቀላቀልም መጠኑ የበዛ በመሆኑ የነዚህ ነገሮች መቀላቀል በውሃው ላይ ተጽእኖ አይኖረውም፤ አይለውጠውምም ማለት ነው፡፡

ሁለተኛ፡- የተነጀሰ (የረከሰ) ውሃ

የተነጀሰ ውሃ እንደ ሽንት ወይም በክት ያለ ነጃሳ ገብቶበት በነጃሳው ምክንያት ከሦስቱ የውሃ ባሕርያት - ጠረኑ፣ጣዕሙ፣ወይም መልኩ - አንዱ የተለወጠ ውሃ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ውሃ በሁሉም ሊቃውንት የጋራ አቋም (በእጅማዕ) ነጃሳና የረከሰ በመሆኑ ለንጽሕና መስጫነት መጠቀም የተፈቀደ (ጃእዝ) አይደለም፡፡

ውሃውን ያልለወጠ የሞተ እንስሳ
ውሃውን የቀየረ የሞተ እንስሳ
ጠቃሚ ነጥቦች

1 - ውሃ በመሰረቱ ንጹሕ ነው፡፡ ንጹሕ ወይም ነጃሳ መሆኑ ተለይቶ ያልታወቀ ውሃ ካለ በመሰረታዊ ንጽሕና መርሑ መሰረት ውሃው ንጹሕ (ጣህር) ነውና ከመጠቀም ማመንታትና ያልተጠየቅነውን ግዴታ በራስ ላይ መጨጫን ተገቢ አይደለም፡፡ ውሃው ከመሰረቱ ነጃሳ የነበረ ሆኖ ንጹሕ ነው ወይስ ነጃሳ የሚል ጥርጣሬ ካደረ ግን ብያኔው ከመሰረቱ ምን ነበረ በሚለው ላይ የተመረኮዘ ይሆናል፡፡

2 - በዘምዘም ውሃ ዉዱእ ማድረግ፣ነቢዩ ﷺ በትልቅ ባልዲ የዘምዘም ውሃ አስመጥተው መጠጣታቸው እና በሱ ዉዱእ ማድረጋቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ይፈቀዳል፡፡[በአሕመድ የተዘገበ]