የዘካት ባለመብቶችና የዘካት አወጣጥ

10474

      የዘካት ባለ መብቶች

      የዘካት ባለመብቶች ዘካት ሊሰጣቸው የሚገቡ ወገኖች ሲሆኑ፣እነሱም አላህ ቁርኣን ውስጥ የዘረዘራቸው ስምንቱ መደቦች ናቸው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹ግዴታ ምጽዋቶች፣(የሚከፈሉት) ለድኾች፣ለምስኪኖችም፣በርሷም ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ልቦቻቸውም (በእስላም) ለሚለማመዱት፣ ጫንቃዎችንም ነጻ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣በመንገደኛም ብቻ ነው፤ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት፤አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡›› [አል-ተውባህ፡60]

      1 - ድኾች

      ድኾች

      ፈቂር ብዙው ፉቀራእ፣እንደ ምግብና መጠጥ፣ልብስና መጠለያ ያለ የራሱንና የሚያስተዳድራቸውን ቤተሰቦች መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚያሟላበት ነገር የሌለው ሰው ነው፡፡ ይህ መደብ ለራሱና ለቤተሰቡ አንድ ዓመት ሙሉ የሚበቃ ነገር ከዘካ ይሰጠዋል፡፡

      2 - ምስኪኖች

      ምስኪኖች

      ምስኪን ብዙው መሳኪን፣ከፍላጎቱ ውስጥ ግማሹን ወይም ከግማሽ በላይ የሆነውን ብቻ ማግኘት ሚችል ሰው ማለት ነው፡፡ አንድ መቶ ኖሮት ሁለት መቶ የሚያስፈልገው ዓይነት ሲሆን የራሱንና የቤተሰቡን ፍላጎት የሚያሟላበትና ለአንድ ዓመት የሚበቃው ያህል ይሰጠዋል፡፡

      3 - በዘካት አሰባሰብ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች

በዘካት አሰባሰብ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች

እነዚህ ከባለሥልጣናት በኩል ዘካውን እንዲሰበስቡና ለሚያስፈልጋቸው እንዲከፋፍሉ የተመደቡ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ሀብታሞች ቢሆኑ እንኳ መደበኛ የሙሉ ሰዓት ሥራቸው በመሆኑ በሠሩት ልክ ከዘካው ይከፈላቸዋል፡፡ ከመንግሥት የሚሰጣቸው ክፍያ ወይም ደሞዝ ካለ ግን ከዘካው አይሰጣቸውም፡፡ የዘካት አሰባሰብ ሠራተኞች በማሰባሰብና በጽሕፈት ሥራ፣በጥበቃውና ለሚገባቸው በማከፋፈሉ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡

      በዘካት አሰባሰብ ላይ ለሚሰሩ ሠራተኞች ስለመስጠት
      በዘካት አሰባሰብ ላይ የሚሠራና ባለ ዕዳ - ሀብታም ቢሆኑ እንኳ - ዘካት ይሰጣቸዋል፡፡ ሰርቶ ማደር የሚችል ሰው ሙሉ ጊዚውን የሸሪዓ ዕውቀት ለመማር የሚያውል ከሆነ ዕልምን መቅራት በአላህ መንገድ መታገል (ጅሃድ) በመሆኑ ሌላ የገቢ ምንጭ የሌለው እስከ ሆነ ድረስ ዘካት ይሰጠዋል፡፡
      በአላህ መንገድ የሚታገል ሙጃህድና ልቦቻቸው እስላምን የሚለማመዱም እንደዚሁ ይሰጣቸዋል፡፡ ራሱንና ጊዜውን ግዴታ ላልሆኑ ዕባዳዎች ለማዋል ብሎ ሰርቶ ማደር እየቻለ መስራት ለተወ ሰው ግን ዘካ አይሰጥም፡፡
      ዕልም ከመማር በተቃራኒ የዕባዳ ጥቅም በዕባዳ አድራጊው ላይ የተወሰነ ነውና፡፡ ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ካፈራችሁትና ከዚያም ለናንተ ከምድር ካወጣንላችሁ ከመልካሙ ለግሱ፤መጥፎውንም ለመስጠት አትሰቡ፤በርሱ ዓይኖቻችሁን ጨፍናችሁ እንጂ የማትወስዱት ስትኾኑ ከርሱ (ከመጥፎው) ትሰጣላችሁን? አላህም ተብቃቂ ምስጉን መኾኑን ዕወቁ፡፡ ሰይጣን (እንዳትለግሱ) ድኽነትን ያስፈራራችኋል፤በመጥፎም ያዛችኋል፤አላህም ከርሱ የኾነን ምሕረትና ችሮታን ይቀጥራችኋል፤አላህም ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነው፡፡›› [አል-በቀራህ፡267-268]

      4 - ልቦቻቸው የሚለማመዱ

ልቦቻቸው የሚለማመዱ

እነዚህ በወገኖቻቸው ዘንድ ተሰሚነት ያላቸውና ዘካው ቢሰጣቸው ይሰልማሉ ተብሎ ተስፋ የሚደረግባቸው፣ወይም ከክፋታቸው ለመጠበቅ ሲባል፣የሙስሊሞችን ጠላቶች እንዲ ከላከሉ ለማድረግ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ልቦቻቸውን ለማለማመድ በሚያስችል መጠን ከዘካው ይሰጣቸዋል፡፡

      5 - የጫንቃ ተገዥ አገልጋይ

      የጫንቃ ተገዥ አገልጋይ

      በባርነት ሥር የሚገኝና ቤዛ ከፍሎ ራሱን ከጌታው እጅ ነጻ የሚያወጣ (ሙካተብ) ሲሆን የቤዛ ዕዳውን መክፈል የሚያስችል ያህል ከዘካው ይሰጠዋል፡፡ ይህም ነጻ ሰው ሆኖ ሙሉ ነጻነቱን በመጎናጸፍ በሕብረተሰቡ ውስጥ ተገቢ ሚናውን እንዲጫወትና በሙሉ ነጻነት አላህን ብቻ እንዲገዛ ለማስቻል ነው፡፡ በጦርነት ላይ የተማረኩ ሙስሊሞች የቤዛ ክፍያም በዚህ ውስጥ ይካተታል፡፡

      6 - ባለ ዕዳዎች

      ባለ ዕዳዎች

      ጋ’ርም ብዙ ጋሪሙን፣ዕዳ ያለበት ሰው ማለት ነው፡፡ ባለ ዕዳ ሁለት ዓይነት ሲሆን እነሱም፡-

      አንደኛ - ለግል ጉዳዩ የተበደረ ባለ ዕዳ ነው፡፡ ድኻ ከሆነ ዕዳውን የሚሸፍንለት ያህል ዘካ ይሰጠዋል፡፡

      ሁለተኛ - በሁለት የሙስሊሞች ጭፍራ መካከል እርቅ ለማውረድ ሲል የተበደረ ባለ ዕዳ ሲሆን ሀብታምም ቢሆን ዕዳውን የሚሸፍንለት ያህል ዘካ ይሰጠዋል፡፡

      7 - በአላህ መንገድ

      በአላህ መንገድ

      በአላህ መንገድ የሚታገሉ ሙጃህዶች ናቸው፡፡ እነዚህ በአላህ መንገድ ለመታገል የሚያስፈልጋቸው ያህል ከዘካው ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ በአላህ መንገድ እንደ መታገል የሚቆጠሩና ለሥራቸው ማከናወኛ ገንዘብ የማያገኙ ብዙ የደዕዋ እንቅስቃሴዎች ይካተታሉ፡፡

      8 - መንገደኛ

መንገደኛ

ከአገሩ የወጣና ገንዘብና ስንቁ ያለቀበት መንገደኛ (ሙሳፍር) ነው፡፡ በአገሩ ሀብታም ቢሆን እንኳ ወደ አገሩ የሚመልስበት ያህል ከዘካ ይሰጠዋል፡፡

    ማሳሰቢያዎች

    1- ለመስጊዶች፣ትምህርት ቤቶች፣ሆስፒታሎችና የመሳሰሉ በሌላው ሰደቃ ሊሰሩ ለሚችሉ የበጎ አድራጎትና የትሩፋት ሥራዎች ቢሆን እንኳ፣ከተዘረዘሩት ስምንት መደቦች ውጭ ዘካት አይሰጥም፡፡

    2- ዘካት ሲከፋፈል ስምንቱን መደቦች ማዳረስ ሸርጥ አይደለም፤ከስምንቱ መደቦች ውስጥ ለአንዳቸው መስጠት የተፈቀደ ነው፡፡

    ዘካት የማይሰጣቸው

    1 - ሀብታሞችና መስራት የሚችሉ ወገኖች

    ነቢዩም ﷺ ፡- ‹‹ሀብታምም ሆነ ሰርቶ ማደር የሚችል ሰው ከርሱ (ከዘካት) እጣ የለውም፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡፡

    2 - ወላጆች፣ሌሎች ዘመዶች፣ሚስትና ቀለባቸው ግዴታ የሆነ ወገኖች

    እንደ ወላጆች፣አያቶች፣ልጆችና የልጅ ልጆች ላሉና ቀለባቸው በአንድ ሙስሊም ላይ ግዴታ ለሆነ ሰዎች ዘካት መስጠት አይፈቀድም፡፡ ለነዚህ ዘካት መስጠት ያለበትን እነሱን የመቀለብ ግዴታ ከራሱ ላይ ማውረድ ማለት በመሆኑና ይህን ማድረግ የዘካው ጥቅም ወደ ሰጭው ወደ ራሱ የሚመለስ በመሆኑ ዘካውን ራሱ ሰጥቶ ራሱ መልሶ የወሰደው ያደርገዋል፡፡

    3 - ልባቸው የማይላመድ ካፍሮች

    ልቦቻቸውን ወደ እስላም ለመሳብና ለማለማመድ ዓላማ ካልሆነ በስተቀር ዘካን ለካፍሮች መስጠት አይፈቀድም፡፡ ነቢዩም ﷺ ፡- ‹‹ከሀብታሞቻቸው ተወስዶ ወደ ድኾቻቸው ይመለሳል፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    ይህም ማለት ከሙስሊም ሀብታሞች ወደ ሙስሊም ድሆች ማለት ነው፡፡ የዘካት ዓላማም ድሃ ሙስሊሞች ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ፣በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ የፍቅርና የወንድማማችነት መሰረቶችን ማጠናከር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከካፍሮች ጋር አይፈቀድም፡፡

    4 - የነቢዩ ﷺ ቤተሰቦች [የነቢዩ ቤተሰብ የሚባሉት በኒ ሃሺም (የሃሺም ጎሳ ዝርዮች) ናቸው፡፡]

    ለክብራቸውና ለደረጃቸው ሲባል ዘካት መውሰድ ለነቢዩ ﷺ ቤተሰቦች የተፈቀደ አይደለም፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹እነዚህ ሰደቃዎች (ዘካት) የሰዎች ቆሻሻ እንጂ ሌላ አይደሉም፤ለሙሐመድም ሆነ ለሙሐመድ ቤተሰቦች የተፈቀዱ አይደሉም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    5 - የነቢዩ ﷺ ቤተሰቦች ነጻ ያወጧቸው የቀድሞ አገልጋዮች (አልመዋሊ)

    እነዚህ የነቢዩ ﷺ ቤተሰቦች ነጻ ያወጧቸው የቀድሞ ባሮች ናቸው፡፡ ‹‹ዘካት ለኛ አይፈቀድም፤የሰዎች የቀድሞ አገልጋዮችም ከነሱ ከራሳቸው ወገን ናቸው፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    በሚለው ሐዲስ ውስጥ ‹‹ከነሱ ከራሳቸው›› የሚለው ድንጋጌው እነሱንም ይመለከታል ማለት በመሆኑ በቀድሞ የበኒ ሃሺም አገልጋዮቻቸውም ላይ ዘካ መውሰድ ሐራም ነው፡፡

    6 - የጫንቃ ተገዥ አገልጋይ

    የጫንቃ ተገዥ የሆነ ባሪያ ገንዘቡ የጌታው ገንዘብ በመሆኑ ዘካት አይሰጠውም፡፡ ቀለቡና ወጭው የአሳዳሪው ኃላፊነት ነውና ዘካ ከተሰጠው ንብረትነቱ ወደ ጌታው ይተላለፋል፡፡ ቤዛ ከፍሎ ራሱን ነጻ እንዲያወጣ ከአሳዳሪው ጋር የተስማማ አገልጋይ (ሙካተብ) ግን ዕዳውን ለጌታው ከፍሎ ራሱን ነጻ እንዲያወጣ ዘካት ይሰጠዋል፡፡ በዘካት አሰባሰብ ሥራ ላይ የተሰማራ የጫንቃ ተገዥ - አገልጋይ በጌታው ፈቃድ ተቀጥሮ መሥራት ስለሚፈችል - ዘካ ሊወስድ ይችላል፡፡

    የዘካት አወጣጥ

    ወቅቱ

    መክፈል እስከ ተቻለ ድረስ የመክፈያ ጊዜው እንደ ደረሰ ወዲያውኑ መክፈል ግዴታ ነው፡፡ ገንዘቡ ከባለቤቱ ራቅ ባለ አገር በመሆኑ ወይም ተይዞ የቆየ በመሆኑና በመሳሰለው ምክንያት ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ማዘግየት አይፈቀድም፡፡

    ዘካው ግዴታ በሆነበት ወቅት ወዲያውኑ ሳይዘገይ መክፈል ዋጅብ መሆኑን የሚያረጋገጠው የሚከተለው የአላህ ቃል ነው ፡- ‹‹ባጨዳውም ቀን ተገቢውን (ዘካ) ስጡ፤›› [አል-አንዓም፡141] ‹‹ምጽዋትንም ስጡ፤›› [አል-ኑር፡56]

    ‹‹ስጡ›› የሚለው የትዕዛዝ አንቀጽ ነውና ወዲያውኑ ተፈጻሚ መሆንን ይጥይቃል፡፡

    ዘካ ማዘግየትን የሚመለከተ ድንጋጌ

    ገንዘቡ በወቅቱ ንሷብ የሞላ ከሆነ ለሁለት ዓመታት ማዘግየት ይፈቀዳል፡፡

    ዘካት የሚወጣበት ቦታ

    በላጩ ገንዘቡ ባለበት አገር ላሉ ሰዎች መስጠት ነው፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ዘካን ካለበት አገር በቅርብ ወይም በርቀት ወደሚገኝ ሌላ አገር ማዛወር ይፈቀዳል፡፡ ራቅ ያለው አገር የበለጠ ድኻ በመሆኑ ወይም ዘካ ከፋዩ በዚያ አገር እንደ አገሩ ድኾች ሁሉ እዚያ ድኻ የኾኑ ዘመዶች ያሉት በመሆኑ የዘካና የዝምድና መቀጠል ትሩፋትን ለማጣመርና በመሳሰሉት ምክንያቶች ዘካን ካንዱ አገር ወደ ሌላው ማዘዋወር ይቻላል፡፡

    ይፈቀዳል የሚለው አቋም ቀጥሎ በሰፈረው የአላህ ቃል መሰረት ትክክለኛው አቋም ነው፡፡ ‹‹ግዴታ ምጽዋቶች፣(የሚከፈሉት) ለድኾች፣ለምስኪኖችም፣ . . . ብቻ ነው፤›› [አል-ተውባህ፡60] ይህም በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ድኾችና ምስኪኖችን ማለት ነው፡፡

    ከዘካት የሚሰጠውና የማይሰጠው ዓይነት

    ለዘካት ክፍያ የሚውለው ከዋነኛውም ከመናኛውም ያልሆነ መካከለኛው ዓይነት ነው፡፡ በመሆኑም የከፋዩ ፍላጎት ካልሆነ በስተቀር ሙክቱን ወይም እርጉዟን፣ወይም የዓይን ማረፊያ የሆነ ቀልብ የሚስብ ምርጥ ፍሬውን እንዲከፍል አይገደድም፡፡

    በአንጻሩም ጥሩውን ትቶ መናኛውን መስጠትም፣ንብረቱ ሁሉ መናኛው ዓይነት ካልሆነ ወይም ከብቶቹ ሁሉ በሸተኞች ካልሆኑ በስተቀር አይፈቀድለትም፡፡ ከሆኑ ግን ካለው ይከፍላል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹መጥፎውንም ለመስጠት አትሰቡ፤በርሱ ዓይኖቻችሁን ጨፍናችሁ እንጂ የማትወስዱት ስትኾኑ ከርሱ (ከመጥፎው) ትሰጣላችሁን ? ›› [አል-በቀራህ፡267-268]

    በሐዲስም ‹‹ዘካ ሲወጣ ያረጀ እንስሳ፣እንከን ያለበትም ሆነ (የማይጠቅም) የፍየል ትንሽ ግልገል ወሳጅ የፈለገው ካልሆነ በስተቀር አይሰጥም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ተብሏል፡፡

    በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ‹‹ውድ ንብረቶቻቸውን ከመውሰድ ተጠንቀቅ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    መመሪያዎች

    1 - ዘካ ሰጪው ዘካው ለሚገባቸው ወገኖች መሰጠቱን ማረጋገጥ ሲኖርበት ለማይገባቸው የሚሰጥ ዓመታዊ ልማድ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ነቢዩﷺ ‹‹ሀብታሙም ሆነ ሰርቶ ማደር የሚችል ሰው ከርሱ (ከዘካት) እጣ የለውም፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    2 - ዘካ ሰጪው ይበልጥ ዘካው የሚገባው ማን እንደ ሆነና ይበልጥ የተቸገረውና የሚያስፈልገው ማን እንደሆነ ለማወቅ በቂ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የበዛ የተገቢነት መመዘኛ ያለው እንደ ሥጋ ዘመድና ድኻ የዲን ዕውቀት ተማሪ የመሳሰሉት ዘካ ለመቀበል የበለጠ የተገቡ ይሆናሉ፡፡

    ዘካት ይበልጥ የሚገባቸው
    ዘካ ሰጪው ይበልጥ ለዘካው ተገቢ ሰው ማን እንደ ሆነና ይበልጥ የተቸገረውና የሚያስፈልገው ማን እንደሆነ ለማወቅ በቂ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የበዛ የተገቢነት መመዘኛ ያለው እንደ ሥጋ ዘመድና ድኻ የዲን ዕውቀት ተማሪ የመሳሰሉት ዘካ ለመቀበል የበለጠ የተገቡ ይሆናሉ፡፡

    ዘካትን የሚመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች

    ዘካን በዋጋው ተመን መክፈል

    ዘካት በመሰረቱ መከፈል ያለበት ከራሱ ከንብረቱ በዓይነት ሲሆን፣የግድ ሲሆን ወይም ለተቀባዩ የበለጠ የሚጠቅም ሆኖ ሲገኝ ግን የዋጋ ተመኑን መክፈል ይፈቀዳል፡፡

    መንግሥት ከዘካት ጋር ያለው ግንኙነት

    የገንዘብ ዘካ በመሰረቱ የመንግሥት ኃላፊነት ሲሆን ለግለሰብ ዘካ አውጭዎችና ለነሱ ግላዊ ግምት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ የሥልጣን ባለቤቱ ኃላፊነቱን ችላ ካለ ግን ግዴታው በያንዳንዱ ሙስሊም ትከሻ ላይ ይወድቃል፡፡

    የዘካ ገንዘብን ለሚገባቸው ክፍሎች ጥቅም ኢንቨስት ማድረግ

    ጥቅሙና ገቢው ዘካት ለሚገባቸው ወገኖች በሚውል ፕሮጄክት ላይ የዘካ ገንዘብን ኢንቬስት ማድረግ ይፈቀዳል፡፡ ይህም የዘካ ገንዘቡን ወዲያውኑ ለሚገባቸው ወገኖች ማከፋፈልን የሚጠይቅ አስቸኳይ ሁኔታ የሌለ ከሆነ ነው፡፡

    ከዘካት ክፍያ ውጭ በአንድ ሰው ሀብት ላይ ግብርን የመሳሰለ ሌላ ክፍያ አለ ?

    - ዘካት ከሀብት ላይ በዑደት የሚከፈልና አቅም ባላቸው ወገኖች ላይ ነፍስ ወከፍ ግዴታ የሆነ በመጠን የተወሰነ ክፍያ ነው፡፡

    - በሀብት ላይ ከዘካት ውጭ ሌሎች የክፍያ ግዴታዎች ሲኖሩ ተለይቶ የተወሰነ መጠን የሌላቸውና እንደዘካት ቋሚ ያልሆኑ የጊዜያዊነት ባህሪ ያላቸው ክፍያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ግዴታ የሚሆኑት በገንዘብ ምክንያት ሳይሆን በአጋጣሚ ምክንያቶች ነው፡፡ ገንዘብ ለግዴታነታቸው ቅድመ ሁኔታ ሲሆን ለምሳሌ ያህል የወላጆች፣የዘመዶችና የሚስት ቀለብ፣ እንደዚሁም በአገር ግምጃቤት ገቢ መሸፈን ሳይቻል ሲቀር አደጋዎችና አስቸኳይ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ የሚውል ወጭን ያጠቃልላል፡፡

    - ግብር ፍትሐዊ ቢሆን እንኳ ዘካን መተካት አይችልም፡፡ ዘካት ከአላህ ዕባዳዎች አንዱ ዕባዳ ሲሆን፣ግብር የሲቪል ግዴታ በመሆኑ አንዱ ሌላውን ማስቀረት አይችልም፡፡