የኩሱፍና ኹሱፍ ሶላት

4812

      የኩሱፍና የኹሱፍ ትርጓሜ

የጸሐይ ግርዶሽ

የጸሐይ ብርሃን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በቀን መጥፋት፡፡

የጨረቃ ግርዶሽ

በሌሊት የጨረቃ ብርሃን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መጥፋት፡፡

    ከኩሱፍና ኹሱፍ በስተጀርባ ያለው ጥበብ

    አላህ ባሮቹን ወደርሱ ይመለሱ ዘንድ የሚያስፈራራባቸው ከምልክቶቹ ውስጥ ሁለት ምልክቶች ናቸው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ፀሐይና ጨረቃ በአንድ ሰው መሞትም ሆነ መኖር ምክንያት አይጋረዱም፤አላህU ባሮቹን የሚያስፈራራባቸው ከምልክቶቹ ውስጥ የሆኑ ሁለት ምልክቶች ብቻ ናቸውና ግድርዶሽ ሲጥልባቸው ወደ ሶላት ተጣደፉ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የኩሱፍና የኹሱፍ ሶላትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች

    ሶላቱ የጠበቀ ሱንና ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ፀሐይና ጨረቃ ከአላህU ምልክቶች (ታምራት) ውስጥ የሆኑ ሁለት ምልክቶች ናቸውና በአንድ ሰው መሞትም ሆነ መኖር ምክንያት አይጋረዱም፡፡ ያንን (ግርዶሹን) ባያችሁ ጊዜ አላህን ለምኑ፣ተክቢራ አድርጉ፣ስገዱ፣ምጽዋት ስጡ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የኩሱፍና የኹሱፍ ሶላት ወቅት

    - ወቅቱ የፀሐይ ወይም የጨረቃ ግርዶሹ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግርዶሹ እስከሚጠራበት ጊዜ ድረስ ነው፡፡

    - ሰጋጁ ግርዶሹ ቢሄድ እንኳ ሶላቱን ያሟላል፡፡ ከተሰገደ በኋላ ግርዶሹ ቢቀጥል ሶላቱ በድጋሜ አይሰገድም፡፡ ሙስሊሞች ዱዓእና እስትግፋሩን ይቀጥሉበታል፡፡

    የኩሱፍና የኹሱፍ ሶላት አሰጋገድ

    ዓእሻ (ረዐ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በአላህ መልእክተኛ ﷺ ዘመን የፀሐይ ግርዶሽ ተከስቶ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሰዎችን አሰገዱ፤(በኹሱፉ ሶላት) የተራዘመ ቅያም ቆሙ፣ከዚያ ሩኩዕ አድርገው ረዘም ያለ ጊዜ ቆዩ፡፡ ከሩኩዕ ቀና ብለው ከመጀመሪያው ቅያም አነስ ያለ ግን የተራዘመ ቅያም ቆሙ፤ከዚያም ከመጀመሪያው ሩኩዕ አነስ ያለ ግን የተራዘመ ሩኩዕ አደረጉ፡፡ በመቀጠል ሱጁድ ወርደው የተራዘመ ሱጁድ አደረጉ፡፡ በሁለተኛው ረክዓም በመጀመሪያው ረክዓ ያደረጉትን አደርገው ሲያበቁ ፀሐይ ጠርታለች፡፡ ከዚያ ለሰዎች ኹጥባ አደረጉና አላህን በማመስገን አወደሱት፤በመቀጠልም ‹‹ፀሐይና ጨረቃ ከአላህU ምልክቶች (ታምራት) ውስጥ የሆኑ ሁለት ምልክቶች ናቸውና በአንድ ሰው መሞትም ሆነ መኖር ምክንያት አይጋረዱም፡፡ ያንን (ግርዶሹን) ባያችሁ ጊዜ አላህን ለምኑ፣ተክቢራ አድርጉ፣ስገዱ፣ምጽዋት ስጡ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡፡

    በዚህም መሰረት የፀሐይ ወይም የጨረቃ ግርዶሽ ሲከሰት ፡-

    1 - ‹‹አስ’ሶላቱ ጃሚዓ›› ተብሎ ለሶላቱ ጥሪ ይደረጋል፡፡

    2 - ሰዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ኢማሙ ድምጽ ከፍ አድርጎ የሚቀራባቸውን ሁለት ረዣዥም ረክዓዎች ያሰግዳል፡፡ በመጀመሪያው ረክዓ ፋቲሓንና ረዥም የሆነ አንድ ሱራ ይቀራል፣ከዚያ ሩኩዕ አድርጎ በሩኩዑ ላይ ለረዥም ጊዜ ይቆያል፡፡ ከሩኩዑ ‹‹ሰምዐል’ሏሁ ልመን ሐምደህ፣ረብ’በና ወለከል ሐምዱ›› እያለ ቀና ይላል፡፡

    ከዚያም ፋቲሓና ከበፊቱ አጠር ያለ ሱራ ይቀራል፡፡ በመቀጠልም ሩኩዕ ያደርግና ከበፊቱ አነስ ያለ ረዥም ቆይታ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ‹‹ሰምዐል’ሏሁ ልመን ሐምደህ፣ረብ’በና ወለከል ሐምዱ›› እያለ ከሩኩዕ ቀና ብሎ ሱጁድ በመውረድ ሁለት የተራዘሙ ሱጁዶችን ያደርጋል፡፡ በሁለቱ ሱጁዶች መካከል የሚቀመጥ ሲሆን ቆይታው አጠር ያለ ይሆናል፡፡

    ከሁለተኛው ሱጁድ ተክቢራ ብሎ ቀና ይላል፡፡ ሁለተኛውን ረክዓም ቆይታው ከመጀመሪያው ረክዓ አጠር ያለ ከመሆኑ ውጭ በቅያሙ፣በሩኩዑና በሱጁዱ ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ያሰግድና ለተሸሁድ ተቀምጦ ሶላቱን በሰላምታ ያጠናቅቃል፡፡

    የኩሱፍና የኹሱፍ ሶላት ሱንናዎች

    1 - በጀማዓ መስገድ፡፡ በነጠላ ቢሰገድም ምንም የለበትም፡፡

    2 - የሚሰገደው በመስጊድ ሆኖ ሴቶች መጥተው ቢሰግዱት አይከለከልም፡፡

    3 - ግርዶሹ ጠርቶ ካልሆነ በስተቀር ሶላቱን በቅያሙ፣በሩኩዑና በሱጁዱ የተራዘመ እዲሆን ማድረግ፡፡ ግርዶሹ ጠርቶ ካሆነ ግን አሳጥሮ ይጨርሳል፡፡

    4 - ሁለተኛው ረክዓ በቅያሙ፣በሩኩዑና በሱጁዱ ከመጀመሪያው ረክዓ ያጠረ መሆን፡፡

    5 - ከሶላቱ በኋላ ሰውን መምከር፣የአላህን ኃያልነትና ቻይነቱን እንዲገነዘቡ ማሳሰብ፣ከግርዶሽ በስተጀርባ ያለው ጥበብ ምን እንደሆነ ማብራራት፣ሰናይ ተግባራትን እንዲሰሩና ከእኩይ ሥራ እንዲታቀቡ መቀስቀስ፡፡

    6 - አላህ ምህረቱን ያወርድ ዘንድ ዱዓእ፣ተማጽኖ፣እስትግፋር፣ሶደቃና ሌሎች የትሩፋት ሥራዎችን ማብዛት፡፡

    7 - በኩሱፍ እጆችን በዱዓእ ጊዜ ከፍ ማድረግ የተፈቀደ ነው፡፡ ዐብዱረሕማን ብን ሰሙራ ባስተላለፉት መሰረት ‹‹ነቢዩ ﷺ በሶላት ላይ ሆነው እጆቻቸውን ወደ ላይ እንዳደረጉ ወደሳቸው መጣሁ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    መመሪያዎች

    1 - ግርዶሹ ካለፈ በኋላ እንጂ መከሰቱ ያልታወቀ ከሆነ ሶላቱ ተሰግዶ አይከፈልም፡፡

    2 - በዘመናዊው ሳይንስ የፀሐይና የጨረቃ ግርዶሽ መንስኤ መታወቁ አላህ ባሮቹን የሚያስፈራራባቸው ሁለት ምልክቶቹ መሆናቸውን አያስቀርም፡፡ በመሆኑም አንድ ሙስሊም ግርዶሹን በመመልከትና በመጠባበቅ ሳይሆን በአላህ ዕባዳና በዱዓእ ሊጠመድ ይገባል፡፡ አቡ በክራ ባስተላለፉት መሰረት ‹‹በአላህ መልእክተኛ ﷺ ዘመን የፀሐይ ግርዶሽ ተከስቶ (ነቢዩﷺ) ኩታቸውን እየጎተቱ ተጣድፈው ወጡ . . ›› ብለዋል፡፡ ይህም ነቢዩ ﷺለአላህ ያላቸው ፍርሃት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

    3 - አንድ ሰው ለኩሱፍ ሶላት አንድ ረክዓ ደረሰ ሊባል የሚችለው በመጀመሪያው ሩኩዕ ከደረሰ ብቻ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሩኩዕ ያመለጠው ሰው በሁለተኛው ሩኩዕ ቢደርስ ረክዓው አምልጦታልና ኢማሙ ካበቃ በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ሰግዶ ረክዓውን ማሟላት ይኖርበታል፡

    4 - የኩሱፍ ሶላት፣መስገድ በሚከለከልባቸው ወቅቶችም ቢሆን ይሰገዳል፡፡

    5 - የፀሐይና የጨረቃ ግርዶሽ ሶላት በዓይን እስካልታየ ድረስ ግርዶሽ ይከሰታል በሚል ወሬ ብቻ አይሰገድም፡፡