የእስትስቃእ (ዝናም መለመኛ) ሶላት

3105

      የእስትስቃእ ትርጓሜ

እስትስቃእ

ድርቅ ሲያጋጥምና ዝናም ሲያጥር ከአላህ ዝናም መለመን ማለት ነው፡፡

    ሶላቱል እስትስቃእ የተደነገገ ስለመሆኑ ማስረጃ

    ነቢዩ ﷺ በተግባር ያከናወኑት በመሆኑ የእስትስቃእ ሶላት የጠበቀ ሱንና ነው፡፡ ዐብዱላህ ብን ዘይድ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹ነቢዩ ﷺ ወደ መስገጃ ቦታ ወጥተው እስትስቃእ አደረጉና ፊታቸውን ወደ ቅብላ መልሰው ኩታቸውን ገልብጠው ሁለት ረከዓ ሰገዱ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የእስትስቃእ ሶላት ወቅት

    መሬት ሲደርቅና ዝናም ሲጠፋ፣ወይም የምንጭና የጉድጓድ ውሃ ሲመነምን፣ወይም ወንዞች ሲደርቁና ተመሳሳይ የድርቅ ሁኔታ ሲከሰት የእስትስቃእ (የዝናም መለመኛ) ሶላት መስገድ የተደነገገ ይሆናል፡፡

    የመስገጃ ጊዜው እንደ ዒድ ሶላት ጸሐይ ወጥታ በዓይን ግምት የጦር ዘንግ ያህል ከፍ ካለች በኋላ መሆኑ የተወደደ ነው፡፡ ይህም ጸሐይ ከወጣች ከሃያ ደቂቃዎች ያህል በኋላ ማለት ነው፡፡

    የእስትስቃእ ሶላት መስገጃ ቦታ

    የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ሱንናው በመስጊድ ሳይሆን በመስገጃ ሜዳ መስገዱ ነው፡፡ የነቢዩ ﷺ ተግባራዊ ሱንና ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

    የእስትስቃእ ሶላት አሰጋገድ

    1 - የእስትስቃእ ሶላት ያለ አዛንና እቃማ የሚሰገድና ድምጽ ከፍ ተደርጎ የሚቀራበት ሁለት ረክዓ ሶላት ነው፡፡

    2 - ሰጋጁ ከእሕራም ተክቢራ በኋላ በመጀመሪያው ረክዓ ሰባት ጊዜ ተክቢራ ይላል፡፡ በሁተኛው ረክዓ ከሱጁድ ቀና ሲል ከሚያደርገው ተክቢራ ሌላ አምስት ጊዜ ተክቢራ ይላል፡፡

    3 - ሰጋጁ ከያንዳንዱ ተክቢራ ጋር እጆቹን ከፍ ያደርጋል፡፡ በተክቢራዎቹ ጣልቃ አላህን ያመሰግናል፣ያወድሳል፤በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት (በአክብሮት የተቀናጀ የአላህ እዝነትና ሰላም) ያወርዳል፡፡

    4 - ከሶላቱ በኋላ ኢማሙ እስትግፋርና የቁርኣን ትላዋ የበዛበት አንድ ኹጥባ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ዱዓእ በማድረግ መእሡር የሆኑ መሰረት ያላቸውን ዱዓዎች አብዝቶና ደጋግሞ በአጽንኦት አላህን ይለማመናል፣ይማጸናል፡፡

    ለአላህ ራሱን አስተናንሶና አዋርዶ ደካማነቱንና ተንበርካኪነቱን ከአላህ ኃያልነት ፊት በማሳየት ሁለት አጆቹን ከፍ አድርጎ አብዝቶና ደግሞ ደጋግሞ ወደ አላህ ይወተውታል፡፡

    5 - ኢማሙ ፊቱን ወደ ቅብላ ያዞራል፤በቀኝ በኩል ያለውን ወደ ግራው፣የግራውን ወደ ቀኙ በማድረግ ኩታውን ያዛዞራል፡፡ ጌታውን መለማመኑንም ይቀጥልበታል፡፡

    የእስትስቃእ ሶላትን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች በከፊል

    1 - ከሶላቱ በፊት የሰዎችን ልብ የሚያለሰልስ፣ከኃጢአት ተመልሰው በመጸጸት ተውበት እንዲያደርጉ የሚገፋፋ፣ለተበደሉት ሰዎች ሐቃቸውን በመመለስና ሙሉ ይቅርታቸውን በማግኘት ራሳቸውን ንጹሕ እንዲያደርጉ የሚያሳስብ፤መዕሲያ (በአላህ ትእዛዝ ላይ ማመጽ) ለዝናም መጥፋት ምክንያት መሆኑን፣ተውበት እስትግፋርና አላህን በፍጹም ልቦና መፍራት ዱዓእ ተቀባይነትን እንዲያገኝ፣ጸጋና በረከት እንዲሰፍን መንስኤ መሆናቸውን የሚያብራራ ምክርና ግሳጼ በኢማሙ ይቀርባል፡፡

    ለአላህ እዝነትና ለርኅራሄው ማስገኛ ምክንያት በመሆኑ ሰዎች ምጽዋት እንዲሰጡና ለቸገራቸው እንዲቸሩ ያበረታታቸዋል፡፡

    2 - ሰዎች አስቀድሞ ይዘጋጁ ዘንድ ለሶላቱ የሚወጣበት እለት አስቀድሞ ይነገራል፡፡

    3 - ወደ ሶላቱ ሲወጣ ራስን ለአላህ በማስተናነስ፣ልቦናን ለርሱ በማጥራት፣በደካማነትና መላ የለሽነት ስሜት ለርሱ በማጎብደድ ሁኔታ ወደ መስገጀው መሄድ ሱንና ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ቀን ማጌጥም ሆነ ሽቶ መቀባት የተደነገገ አይደለም፡፡

    እብን ዐባስ ነቢዩ ﷺ ለእስትስቃእ ሶላት የወጡበትን ሁኔታ ሲገልጹ ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ ወደ መስገጃው ሲያመሩ፣ከማጌጥና ከውበት በራቀ አኳኋንና ራሳቸውን በማስተናነስ ለአላህ አጎብድደው ነበር የወጡት፡፡››[በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    4 - በእስትስቃእ ኹጥባ ውስጥ ሁለት እጆችን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ እሰትግፋርና ዱዓእ ማብዛት፡፡

    ዝናም በሚጥልበት ጊዜ የተወደደ ነገር

    ዝናምሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጥል ቆም ብሎ ለዝናሙ ራስን ማጋለጥ የተወደደ ነው፡፡ አነስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹ከአላህ መልእክተኛ ﷺ ጋር ሆነን ዝናም መታንና የአላህ መልእክተኛ ﷺ ዝናሙ እስኪነካቸው ድረስ ልብሳቸውን ሰብሰብ አደረጉ፤የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ለምን እንዲህ ያደርጋሉ? አልናቸው፡፡ እሳቸውም ﷺ (አዲስ የሚዘንበው ዝናም) የጌታው U አዲስ ፍጥረት (ክንውን) በመሆኑ ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡፡

    ዝናም ከአንድ አላህ ብቻ የተሰጠ ችሮታው ነው
    አንድ ሙስሊም ዝናም የሚጥለው አንዳንዶች ‹‹በዚህና በዚያ ኮከብ ምክንያት ዘነበልን›› እንደሚሉት ሳይሆን፣አላህ ለባሮቹ በዋለላቸው ችሮታና በእዝነቱ መሆኑን ማመን ይኖርበታል፡፡ በዚህና በዚያ ኮከብ ምክንያት ነው የዘነበው ማለት - አላህ ይጠብቀንና - ሽርክ ነው፡፡