የተጠው’ዉዕ ጾም

4104

      የተጠው'ዉዕ ጾም ትርጓሜ

የተጠው’ዉዕ ጾም

ግዴታ ያልሆነና አንድ ሰው ለአላህ ብሎ የሚጾመው ጾም ነው፡፡

      የተጠው’ዉዕ ጾም ትልቅ ትሩፋትና የተትረፈረፈ አጅር አለው፡፡ ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው ሐዲስ አልቁድሲ ውስጥ የአላህ መልእክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል ፡- ‹‹የኣደም ልጅ (መልካም) ሥራ ሁሉ (ምንዳው) እጥፍ ይደረጋል፤አንድ ሐሰና (መልካም ሥራ ምንዳው) ከአስር እጥፍ እስከ ሰባት መቶ እጥፍ ነው፡፡ አላህ ‹ከጾም በስተቀር፣እሱ ለኔ ነውና እኔ ነኝ ምንዳውን የምሰጠው፤›› [በቡኻሪና በሙስሊም የተዘገበ] ብሏል፡፡

      መጾም ሱና የሚሆንባቸው ቀናት

      1 - ከሸዋል ወር ስድስት ቀን

      ነቢዩﷺ ‹‹ረመዷንን የጾመና ከሸዋል ስድስት ቀናትን ያስከተለው ሰው፣ዕድሜ ልክ የመጾም ያህል ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      2 - ከዙልሕጅጃ ወር የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ቀናት

      ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ከነኚህ ቀናት - ከአስርቱ የዙልሕጃ ቀናት - ይበልጥ መልካም ሥራ አላህ ዘንድ የሚወደድበት ምንም ቀን የለም፡፡›› ሲሉ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በአላህ መንገድ መታገልም (ጅሃድ) ቢሆን? ተብለው ተጠየቁና ‹‹በአላህ መንገድ መታገልም (ጅሃድ) ቢሆን፣ራሱንና ገንዘቡንም ጭምር (ለጅሃድ) ይዞ ወጥቶ (ሕይወቱንና ገንዘቡንም ሰውቶ) አንዱንም ይዞ ያልተመለሰ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      በመሆኑም በነዚህ አስር ቀናት ውስጥ አላህን በመዘከር፣ተህሊል (ላእላሀ እልላሏህ ማለትን) በማብዛት፣ቁርኣንን በመቅራት፣ሶደቃ በመለገስና የዒዱ ቀን ሲቀር ሁሉንም ቀናት በመጾም ለዕባዳ ልዩና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሱንና ነው፡፡ ከዘጠኙ ውስጥ በጣም የጠበቀ ሱንና፣በሐጅ ሥርዓተ ጸሎት ላይ ላልሆነ ሰው የዙልሕጃ ዘጠነኛው ቀን ማለትም የዐረፋ ቀን ጾም ነው፡፡

      ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹የዐረፋ ቀን ጾም ከበፊቱ ያለውን ዓመትና ከኋላው የሚመጣውን ዓመት (ኃጢአት) ማበሻ እንዲያደርገው አላህ ዘንድ ታሳቢ አደርጋለሁ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      3 - የዓሹራእ ጾም

ዓሹራእ

የአላህ ወር የሙሐር’ረም አስረኛው ቀን ነው፡፡

      ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹የዓሹራእ ቀን ጾምን ከርሱ በፊት ያለውን ዓመት (ኃጢአት) የሚያብስ ታሳቢ ያደርገው ዘንድ አላህን እለምናለሁ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      የዓሹራን ጾም መነሻ በተመለከተ ከዐብደላህ ብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ፡- ‹‹ነቢዩ ﷺ ወደ መዲና ሲመጡ አይሁድ የዓሹራን ቀን ሲጾሙ አዩና ምን እንደሆነ ጠየቁ፤ይህ በጎ ቀን ነው፣ይህ አላህ የእስራኤል ልጆችን ከጠላታቸው ያዳነበት ቀን በመሆኑ ሙሳ የጾመበት ቀን ነው አሏቸው፡፡ (ነቢዩ ﷺ) ከናንተ ይበልጥ ለሙሳ የተገባሁ እኔ ነኝ ብለው ቀኑን ጾሙና እንዲጾምም አዘዙ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      በተጨማሪም ከዓሹራእ በፊት ያለውን ዘጠነኛውን ቀን (ታሱዓ) መጾምም የተወደደ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹እስከ መጪው (ዓመት) ድረስ ከኖርኩ ዘጠነኛውን እጾማለሁ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለታቸው በሙስሊም ተዘግቧል፡፡

      4 - ከየወሩ13ኛው፣14ኛውና 15ኛው ቀን

አያም አልቢድ (ነጫጭ ቀናት)

ይህ የጨረቃ ወር አስራ ሦስተኛ፣አስራ አራተኛና አስራ አምስተኛ ቀናት ሲሆን ብርሃናማ ተብለው የተሰየሙት ሌሊቶቻቸው በጨረቃ ብርሃን ምክንያት ነጫጭ በመሆናቸው ነው፡፡

    ዐብዱል መሊክ ብን አልምንሃል አባታቸውን በመጥቀስ ባስተላለፉት መሰረት ከነቢዩ ﷺ ጋር የነበሩ ሲሆን ነቢዩ ﷺ ነጫጭ ቀናትን እንድንጾም አዘውን ‹‹ዕድሜ ልክ እንደ መጾም ነው፡፡› [በእብን ሕባን የተዘገበ] ይሉ ነበር ብለዋል፡

    5 - በየሳምንቱ ሰኞና ሐሙስ መጾም

    ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ሥራዎች (አላህ ዘንድ) ሰኞና ሐሙስ ቀን ይቀርባሉ፤ ስለዚህም ጾመኛ ሆኜ ሥራዬ እንዲቀርብ እወዳለሁ፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    6 - አንዱን ቀን እየጾሙ ሌላውን ቀን ማፍጠር

    ለተጠው’ዉዕ ጾም በላጩ የዳዉድ U ጾም ነው፤አንድ ቀን ጾመው አንድ ቀን ይፈስኩ ነበር፡፡ ከዐብደላህ ብን ዐምር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹አላህ ዘንድ ይበልጥ የተወደደ ጾም የዳዉድ ጾም ነው፤አንድ ቀን ጾሞ አንድ ቀን ያፈጥር ነበር፡፡›› [በነሳኢ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    7 - የሙሐር’ረም ወር ጾም

    ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹ከረመዷን በኋላ በላጩ ጾም፣የአላህ ወር ሙሐረም ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    8 - የሸዕባን ወር ጾም

    ነቢዩ ﷺ በሌላው ወር የማይጾሙትን በረመዷን ውስጥ ይጾሙ ነበር፡፡ ኡሳማ ብን ዘይድ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ከሸዕባን የሚጾሙትን ያህል ከወራት ውስጥ በአንዱም ወር ሲጾሙ አላየሁዎትም ስላቸው፣ያ በረጀብና በረመዷን መካከል ሰዎች ችላ የሚሉት ወር ነው፤እርሱ ሥራዎች ለዓለማት ጌታ የሚቀርቡበት ወር ነውና እኔ ጾመኛ ሆኜ ሥራዎቼ እንዲቀርቡ እወዳለሁ፡፡›› [በነሳኢ የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡፡

    ‹‹ሸዕባን ከተጋመሰ እስከ ረመዷን ድረስ አትጹሙ፡፡›› [በእብን ኹዘይማህ የተዘገበ] በሚለው ሐዲስ የተላለፈው እገዳ፣ወይ ሁለተኛውን አጋማሽ የሚመለከት ነው፣ወይ ደግሞ የሸዕባንን ጾም ከረመዷን ጾም ጋር አለማገናኘትን ሚመለከት ነው፡፡ ከመጀመሪያው የጾመና፣ሁለተኛውን አጋማሽ ለይቶ ያል ጾመና ከረመዷን ጋር ያላገናኘው ሰው ግን ቢጾም ችግር ለውም፡፡

    መጾሙ ሐራም የሆነና መጾሙ የተጠላ

    አንደኛ - መጾሙ ሐራም የሆነ

    1 - ሁለቱን የዒድ ቀኖች መጾም ሐራም ነው፡፡ ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛﷺ ሁለት ቀኖች እንዳይጾሙ ከልክለዋል፡- የአድሓ ቀንና የፍጥር ቀን፡፡ [በሙስሊም የተዘገበ]

    2 - አይ’ያም አት’ተሸሪቅን ማለትም ከዒድ አልአድሓ ቀጥሎ ያሉ ሦስቱን ቀናት መጾምም ሐራም ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛﷺ ‹‹አይ’ያም አት’ተሸሪቅ የመብላትና የመጠጣት ቀናት ናቸው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    ሙተመት’ትዕ ወይም ቃሪን የሆነና የሚሰዋ እርድ (ሀድይ) ማቅረብ ላልቻለ ሐጅ አድራጊ ግን መጾም ይፈቀዳል፡፡ አላህ አንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ያላገኘም ሰው ሶስትን ቀኖች በሐጅ ወራት፤ሰባትንም በተመለሳችሁ ጊዜ መጾም አለበት፤›› [አል-በቀራህ፡196]

    3 - በጥርጣሬ ቀን (የውም አሽ’ሸክ) መጾምም ሐራም ነው፡፡ ይህ በሃያ ዘጠነኛው ቀን ማታ አዲስ ጨረቃ በደመና ወይም አቧራ ምክንያት ሳትታይ ከቀረች የሸዕባንን ሰላሳኛ ቀን መጾም ማለት ነው፡፡ ዐምማር (ረዐ) ‹‹በጥርጣሬ ቀን (የውም አሽ’ሸክ) የጾመ ሰው፣የአበል ቃሲምን (ነቢዩንﷺ ) ቃል ጥሷል፡፡›› [ትርምዚ ዘግበውት ሐሰኑን ሶሒሕ ብለውታል] ብለዋልና፡፡

    ሁለተኛ - መጾሙ የሚጠላ

    1 - የረጀብን ወር ለብቻው ለይቶ መጾም፣ከዘመነ ጃህሊያ የመለያ ምልክት አንዱ የረጀብን ወር ማክበር በመሆኑና መጾሙ መፈክራቸውን ሕያው ማድረግ በመሆኑ መጾሙ የተጠላ ነው፡፡

    2 - የጁሙዓን ቀን ለይቶ መጾምም እገዳ ስላለበት የተጠላ ነው፡፡ ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹ከበፊቱ የሚጾም ወይም ከኋላው የሚጾም ካልሆነ በስተቀር አንዳችሁ የጁሙዓን ቀን አይጹም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡ የጾም ልማዱ ከጁሙዓ ጋር ተገጣጥሞ ከሆነ ግን ምንም ለበትም፡፡

    3 - ጾምን ከጾም ማገናኘት (ውሳል) የተጠላ ነው፡፡ ውሳል ጾምን በመሀል ሳያፈጥሩ ከሚቀጥለው ቀን ጾም ጋር ማገናኘት ሲሆን ነቢዩ ﷺ ከልክለዋል፡፡ ዐብደላህ ብን ዑመር (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ውሳልን ከለከሉና እርስዎ ያገናኛሉና አሏቸው፡፡ ‹‹እኔ እንደ እናንተ አይደለሁም እኔ የሚያበላኝና የሚያጠጣኝ አለኝና፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡፡

    መመሪያዎች

    1 - አንድ ሙስሊም በዕባዳው በአላህ ሸሪዓ መመራት ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም ሸሪዓው እንዳይጾም የከለከለውን አይጾምም፡፡ ነቢዩ ﷺ ለይተው ያልመደቡትን እንደ ረጀብ ሃያ ሰባትና ሸዕባን አስራ አምስት ያሉ ቀኖችን በራሱ ፈጥሮ አይጾምም፡፡ ነቢዩﷺ ‹‹በዚህ ጉዳያችን (ዲናችን) ላይ ከርሱ ያልሆነውን አዲስ ፈጠራ ያስገባ ሰው ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    2 - አንድ ሙስሊም የካፍሮችን የሥርዓተ እምነት መገለጫዎችን ከማክበር መራቅ ሲኖርበት፣በአምልኮት፣ በጾምና በመሳሰሉት እነሱ የሚያከብሩትን ሥርዓተ ጸሎት ማክበር የለበትም፡፡

    ጾም በሕክምና ሳይንስ ዓይን
    ጾም ለቆዳ በሽታዎች ሕክምና ጠቃሚ ሲሆን፣ለዚህ መንስኤው ደም ውስጥ ያለውን የውሃ መጠን የሚቀንስ በመሆኑና ይህም በተራው በቆዳ ውስጥ ያለውን ውሃ በመቀነስ ቆዳ ማይክሮቦችንና በጀርም የሚተላለፉ በሽታዎችን እንዲቃወምና እንዲከላከል ተጨማሪ አቅም ስለሚፈጥርለት ነው፡፡