የሶላት ደረጃና ብያኔው

3.9
7642

      የሶላት ትርጓሜ

የሶላት የቁም ትርጉም

ዱዓእ (ጸሎት) ማለት ነው፡፡

የሶላት ሸሪዓዊ ትርጉም

አላህን ለመገዛት ተብሎ በተለዩ ቃላትና ተግባራት የሚከናወን በተክቢር (አል’ሏሁ አክበር) ተጀምሮ በተስሊም (አስ’ሰላሙ ዐለይኩም) የሚያበቃ ዕባዳ (አምልኮ) ነው፡፡

    ሶላት እስላም ውስጥ ያለው ደረጃ

    1 - ሶላት ከእስላም ማእዘናት ሁለተኛው ማእዘን ነው፡፡

    ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እስላም በአምስት (ማእዘኖች) ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ (እነሱም) ፡- ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን መመስከር፣ሶላትን ደንቡን ጠብቆ አዘውትሮ መስገድ፣ . . . ናቸው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

    2 - ሶላት ከሥራዎች ሁሉ በላጩ ነው፡፡

    የአላህ መልእክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ከሥራዎች ሁሉ በላጩ ሶላትን በወቅቱ መጀመሪያ ላይ መስገድ ነው፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    3 - ሶላት የእስላምና የኩፍር መለያ ነው፡፡

    ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በአንድ ሰውና በማጋራትና በክህደት (በሽርክና በኩፍር) መካከል ያለው መለያ ሶላትን መተው ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    4 - ሶላት - ከተውሒድ በኋላ - እስላም የሚገነባበት ምሶሶ ነው፡፡

    ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የዚህ ጉዳይ ራስ እስላም ነው፣ምሰሶው ደግሞ ሶላት ነው፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ]

    የሶላት ትሩፋት

    1 - ሶላት ለሰጋጁ ብርሃን ነው፣ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሶላት ብርሃን ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    2 - ሶላት የኃጢአቶች ማበሻ ነው፡፡ አላህ U እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሶላትንም በቀን ጫፎች (ጧትና ከቀትር በኋላ) ከሌሊትም ክፍሎች ፈጽም፤መልካም ሥራዎች ኃጢአቶችን ያስወግዳሉና፤ይህ ለተገሳጮች ግሳጤ ነው፡፡›› [ሁድ፡114]

    ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንዳችሁ ከደጃፉ ወንዝ ቢኖረውና በየቀኑ አምስት ጊዜ ገላውን ቢታጠብበት ከእድፉ አንዳች ነገር ገላው ላይ ይቀራልን? ንገሩኝ ሲሉ፣(ሶሓባ) ምንም እድፍ አይቀርበትም አሏቸው፤ነቢዩ ﷺ ፡- ይህ እንግዲህ አላህ ኃጢአቶችን የሚያብስባቸው የአምስቱ ሶላቶች ምሳሌ ነው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

    3 - ሶላት ጀነት ለመግባት ምክንያት ነው፤ነቢዩ ﷺ ለረቢዓ ብን ከዕብ በጀነት አብሯቸው ለመሆን ሲጠይቁ፡- ‹‹ሱጁድን በማብዛት በራስህ ላይ አግዘኝ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ሶላትን የሚመለከት ድንጋጌ

    የአምስቱ ወቅት ሶላቶች በክታብ (በቁርኣን) በሱንና እና በእጅማዕ ግዴታ (ዋጅብ) ናቸው፡-

    1 - ክታብ (ቁርኣን)፡- ‹‹ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፤ዘካንም (ግዴታ ምጽዋትን) ስጡ፤(ለጌታችሁ) ከአጎንባሾች ጋርም አጎንብሱ፡፡›› [አል-በቀራህ፡43]

    2 - ሱንና፡- ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እስላም በአምስት (ማእዘኖች) ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ (እነሱም) ፡- ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን መመስከር፣ሶላትን ደንቡን ጠብቆ አዘውትሮ መስገድ፣ዘካን መስጠት፣የሐጅ ሥርዐተ ጸሎት መፈጸምና ረመዷንን መጾም ናቸው፡፡››[በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

    - ከጠልሓ ብን ዑበይድላህ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት አንድ ሰውየ ነቢዩን ﷺ ስለ እስላም ሲጠይቃቸው ፡- ‹‹በአንድ ቀንና ሌሊት አምስት ሶላቶችን መስገድ ነው አሉ፤ከነሱ ሌላ አለብኝ ወይ? ሲላቸው በፍላጎትህ የምታደርገው (ተጠው’ዉዕ) ካልሆነ ሌላ የለብህም፡፡››[በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] አሉት፡፡

    3 - እጅማዕ፡- በአንድ ቀንና ሌሊት አምስት ሶላቶችን መስገድ ግዴታ መሆኑን ኡመቱ (ሕዝበ ሙስሊሙ) በአንድ ድምጽ ተስማምቶበታል፡፡

    ሶላት በማን ላይ ግዴታ ይሆናል?

    ሶላት ለአቅመ አዳም/ሔዋን በደረሰና አእምሮው ጤነኛ በሆነ በያንዳንዱ ሙስሊም ወንድና ሴት ላይ ግዴታ ነው፡፡

    ያመለጠ ሶላትን ሰግዶ መክፈል
    እስላም ከበፊቱ የነበረውን ነገር ስለሚያብስ አንድ ካፍር ከመስለሙ በፊት ያመለጠውን ሶላት ሰግዶ እንዲከፍል አይታዘዝም፡፡

    ሶላትን የተወ ሰው የሚመለከት ድንጋጌ

    1 - ሶላት ግዴታ መሆኑን የሚክድ ሶላት የተወ ሰው

    የማያውቅ ከሆነ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ ግዴታነቱን ማስተባበል ከቀጠለበት በአላህ በመልእክተኛውና በሙስሊሞች የጋራ ስምምነት እስላምን ያስተባበለ ካፍር ነው፡፡

    2 - በስንፍና ሶላትን የተወ ሰው

    ሶላትን ሆን ብሎ በስንፍና የተወ ሰው ከሐዲ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ወሊዩል አምር እንዲሰግድና ተጸጽቶ ተውበት እንዲያደርግ ለሦስት ቀናት ጊዜ ጥሪ ሊያድርግለት ይገባል፡፡ ተጸጽቶ ከተመለሰ ተመለሰ ካልተመለሰ ግን ተቀልባሽ (ሙርተድ) በመሆኑ ይገድለዋል፡፡ ይህም ነቢዩ ﷺ ፡-‹‹በኛና በነሱ መካከል ያለው መለያ ቃል ሶላት ነው፣ሶላቱን የተወ ሰውም ከሃዲ ሆኗል፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    ባሉት መሰረት ነው፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹በአንድ ሰውና በማጋራትና በክህደት (በሽርክና በኩፍር) መካከል ያለው መለያ ሶላትን መተው ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የትንሽ ልጅ ሶላት
    ልጆች ሰባት ዓመት ሲሞላቸው እንዲለማመዱት ሶላት እንዲሰግዱ ይታዘዛሉ፡፡ አስር ዓመት ሲሞላቸው ካልሰገዱ በማያሳምም ሁኔታ እንዲሰግዱ ይመታሉ፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ልጆቻችሁን ሰባት ዓመት ሲሞሉ እንዲሰግዱ እዘዟቸው፡፡ ዐስር ዓመት ሲሞሉ (ካልሰገዱ) እንዲሰግዱ ምቷቸው፡፡›› [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡