የመዲና ጉብኝት የመዲና ትሩፋትና የላቀ ደረጃዋ

4498

    የነቢያዊው ከተማ (መዲና) ስሞች

    1 - መዲና:

    አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ወደ መዲና ብንመለስ አሸናፊው ወራዳውን በእርግጥ ከርሷ ያወጣል ይላሉ፤›› [አል-ሙናፊቁነ:8]

    2 - ጧባ:

    ጃቢር ብን ሰሙራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹አላህ መዲናን ጣባ ብሎ ሰይሟል፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

    3 - ጠይባ:

    ዘይድ ብን ሣቢት (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹እሳት የብርን ቆሻሻ እንደሚያስወግድ ሁሉ ኃጢአቶችን የምታስወግድ ጠይባ ናት፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የነቢያዊው ከተማ (መዲና) ትሩፋት

    ሰዐድ ብን አቢ ወቃስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ መዲና ትሻላቸው ነበር፤አላህ ከርሱ የተሸለውን የሚተካላት ቢሆን እንጂ በፍላጎቱ የሚተዋት ማንም ሰው የለም፡፡ እኔ በቅያማ ቀን አማላጅ ወይም መስካሪ የምሆንለት ቢሆን እንጅ ማንም በኑሮ ችግሯና በአስቸጋሪ ሁኔታዋ ላይ ጸንቶ የሚኖር አንድም ሰው አይኖርም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    አቡ ሁረይራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹(ለህጅራ) መንደሮችን ወደምትበላ (የምታሸንፋቸው ወደ ሆነች) እና የሥሪብ ወደሚሏት መንደር (እንድሰደድ) ታዝዤያለሁ፤እሷ መዲና ስትሆን የአንጥረኛ መናፍ የብረትን ቆሻሻ አንደሚያጠራ ሰዎችን ታጠራለች፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ከነቢያዊው ከተማ (መዲና) ልዩ ባህርያት መካከል

    1 - በዐይርና በሠውር - ሁለት ተራሮች ናቸው - መካከል ያለው ጸጥተኛ፣የተከበረና የተጠበቀ ሐረም (ክልል) ስትሆን ዛፏ አይቆረጥም፤አውሬዋም አይታደንም፡፡

    የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹መዲና በዐይር እና በሠውር መካከል ያለው የተከበረ ሐረም ነውና በርሷ ውስጥ ብድዓ የሠራ ወይም ብድዓ ሠሪን ያስጠለለ ሰው፣ የአላህ የመላእኮችና የሰዎች ሁሉ እርግማን ይውረድበት፡፡ አላህ በቅያማ ቀን ከርሱ ዋጅቡንም ሆነ ሱናውን አይቀበልም፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ኢብራሂም መካን ሐረም እንዳደረጉ ሁሉ የአላህ መልእክተኛ ﷺ መዲናን ሐረም አድርጓታል፡፡ ዐብደላህ ብን ዘይድ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹ኢብራሂም መካን የተከበረ ሐረም አድርገው ዱዓእ አድርገውላታል፡ ኢብራሂም መካን የተከበረ ሐረም እንዳደረጉ ሁሉ እኔ መዲናን የተከበረ ሐረም አድርጌያለሁ፡ ኢብራሂም ለመካ ዱዓእ እዳደረጉላት ሁሉ ሙዷዋ እና ሷዕዋ (ይበረክት ዘንድ ለመዲና) ዱዓእ አድርጌያለሁ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በመካ ሐረምና በመዲና ሐረም መካከል ያለው ልዩነት የመካ ሐረም በማስረጃዎችና በእጅማዕ ተረጋግጦ የጸና ሲሆን የመዲና ሐረም የአቋም ልዩነት (ኽላፍ) ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ትክክለኛው አቋም ሐረም መሆኑ ነው፡፡

    የሠውር ተራራ
    የዐይር ተራራ

    2 - መዲና የተሰገደ ሶላት አጅሩ እጥፍ ድርብ ነው፡፡

    ነቢዩ ﷺ ‹‹በዚህ በኔ መስጊድ የሚሰገድ አንድ ሶላት መስጅድ አልሐራም ብቻ ሲቀር በሌላ ቦታ ከሚሰገደው አንድ ሺህ ሶላት የበለጠ ነው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - ከጀነት ጨፌዎች የሆነና እዚያ መስገድ ሱና የተደረገ ረውዷ (ጨፌ) ያለባት መሆኑ፡፡

    አቡ ሁረይራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹በቤቴና በምንበሬ መካከል ከጀነት ጨፌዎች አንዱ የሆነ ጨፌ (ረውዷ) ይገኛል፡ በምንበሬና በኔ ሐውድ (ማጠጫ) ላይ ነው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የተከበረው ረውዷ

    4 - በመጨረሻዎቹ ዘመናት መሲሕ አድደጃል (ሐሳዊው መሲሕ) የማይገባባትና ወረርሽኝም የማይገባባት መሆኑ፡፡

    አነስ ብን ማሊክ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹ደጃል ወደ መዲና ይመጣና መላእኮች የሚጠብቋት ሆና ያገኛል፤አላህ ካለ ደጃልም ሆነ ወረርሽኝ በሽታ አይገባባትም፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    5 - ነቢዩ ﷺ ብሩክ እንድትሆን ዱዓእ አድርገውላታል፡

    አነስ ብን ማሊክ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹አላህ ሆይ! በመካ ያኖርከውን በረከት እጥፍ በመዲና አድርግ፡፡››[በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    6 - የመካ አውሬ አደን ኃጢአትና ክፍያ ያለበት ሲሆን የመዲና አውሬ ግድያ ግን ኃጢአት እንጂ ክፍያ የለበትም፡፡ የመካ እንስሳ ግድያ የሚያስከትለው ኃጢአት ከመዲናው የበለጠ ነው፡፡ [አልሙምትዕ ቅ 7 ገጽ 257 ይመልከቱ፡፡]

    የነቢዩን ﷺ መስጊድ ጉብኝት የሚመለከት ድንጋጌ

    የነቢዩን ﷺ መስጊድ መጎብኘት ከሐጅ ሸርጦች፣ከማእዘናቱ፣ከዋጅቦቹም ሆነ ከሱናዎቹም ውስጥ አይደለም፡፡ ጉብኝቱ በማንኛውም ወቅት የተደነገገ ነው፡፡

    የገብኝቱ ዓላማ መቃብሩን ለመጎብኘት ሳይሆን በመስጊዱ ሶላት ለመስገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አቡ ሁረይራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹ወደ ሦስት መስጊዶች ብቻ እንጂ (ለዕባዳ ተብሎ) ጉዞ አይደረግም፤እነሱም ፡- (የመካው) የተከበረው መስጊድ፣የመልእክተኛው ﷺ መስጊድና የአልአቅሷ መስጊድ ናቸው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ሸይኹል እስላም እብን ተይምይያ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የጉዞ ዓላማው በመስጊዳቸው ለመስገድ ሳይሆን መቃብሩን መጎብኘት ከሆነ . . . የኢማሞችና የአብዛኞቹ ዑለማእ አቋም ይህ ያልተደነገገና ያልታዘዘ ነው የሚል ነው፡፡ . . .

    የነቢዩን ﷺ መቃብር መጎብኘትን የሚመለከቱ ሐዲሶች በሁሉም የሐዲስ ሊቃውንት ሙሉ ስምምነት ዷዒፍ (ደካማ) ሐዲሶች ናቸው፡፡እንዲያውም የፈጠራ (መውዱዕ) ሐዲሶች ናቸው፡፡ ተቀባይነት ካላቸው የሱነን ባለቤቶች ውስጥ አንድም ሰው አልዘገባቸውም፤ከኢማሞች ውስጥም አንድም ኢማም አንዱንም (ሐዲስ) በማስረጃነት አላቀረበም፡፡›› [መጅሙዕ አልፈታዋ ክፍል 27 ገጽ 26]

    ዝያራንና ኣዳቡን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች

    1 - ጎብኚው ወደ መስጊዱ ሲደርስ ቀኝ እግሩን አስቀድሞ ‹‹አልሏሁምመ እፍተሕ ሊ አብዋበ ረሕመትከ›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ሱና ነው፡፡

    2 - ሁለት ረክዓ ተሕይቱል መስጅድ ይሰግዳል፡፡ ሶላቱ በተከበረው ረውዷ ቢሰግድ በላጭ ነው፡፡

    3 - የነቢዩን ﷺ እና የሁለቱ ባልደረቦቻቸውን መቃብር መጎብኘት ሱና ይሆናል፡፡ ከነቢዩ ﷺ መቃብር ትይዩ በአደብና በእርጋታ ቆሞ ድምጹን ዝቅ በማድረግ ‹‹አስ’ሰላሙ ዐለይከ አይ’ዩሀን’ነቢዩ ወረሕመቱሏሂ ወበረካቱህ፤ሰል’ለል’ሏሁ ዐለይከ፤ወጀዛከ ዐን ኡም’መትከ ኸይረን፡፡›› ይላል፡፡

    ትርጉሙ ‹‹ አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣እዝነቱና በረከቶቹ ለርስዎ ይሁን፡፡ ከአክብሮት የተቀናጀ የአላህ ረሕመት በርስዎ ላይ ይውረድ፡፡ አላህ ለኡመትዎ ለዋሉት ውለታ መልካሙን ይዋልልዎት፡፡›› ማለት ነው፡፡

    ከዚያም ወደ ቀኝ አንድ ወይም ሁለት እርምጃዎችን በመራመድ ከአቡበክር (ረዐ) መቃብር ፊት በመቆም ‹‹አስ’ሰላሙ ዐለይከ ያ አባ በክር ያኸሊፈተ ረሱሊልላህﷺ ወረሕመቱልሏሂ ወበረካቱሁ፤ረድየሏሁ ዐንከ፣ወጀዛከ ዐን ኡምመት ሙሐመድን ﷺ ኸይረን፡፡›› በማለት ሰላምታ ማቅረብ፡፡

    ከዚያም ወደ ቀኝ አንድ ወይም ሁለት እርምጃዎችን በመራመድ ከዑመር (ረዐ) መቃብር ፊት በመቆም ‹‹አስ›ሰላሙ ዐለይከ ያ ዑመር ያ አሚረል ሙእምኒን ወረሕመቱልሏሂ ወበረካቱሁ፤ረድየሏሁ ዐንከ፣ወጀዛከ ዐን ኡምመት ሙሐመድን ﷺ ኸይረን፡፡›› በማለት ሰላምታ ማቅረብ፡፡

    4 - የነቢያዊውን መስጊድ ለሚጎበኝ ሰው የአምስቱንም ወቅቶች ሶላት በነቢዩﷺ መስጊድ መስገድ፣መስጊዱ ውስጥ የአላህን ዝክርና ዱዓእ፣የሱና ሶላቶችን በተለይም በተከበረው ረውዷ ውስጥ ማብዛት ሱንና ነው፡፡

    5 - የቁባእ መስጊድን እዚያ ለመስገድ መጎብኘት ሱንና

    ሲሆን ጉብኝቱ ቅዳሜ ቀን ቢሆን በላጭ ነው፡፡ ከእብኑ ዑመር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ በእንስሳ ጀርባ ተምጠውና በእግርም ወደ ቁባእ መስጊድ ይመጡና ሁለት ረክዓ ይሰግዱበት ነበር፡፡››ብለዋል፡፡ በሌላ ዘገባ ‹‹ወደ ቁባእ ይመጡ ነበር›› የሚል ተመልክቷል፡፡ በየቅዳሜው ማለት ነው፡፡ [በሙስሊም የተዘገበ]

    6 - የበቂዕ መቃብሮችን፣የሹሀዳእና የሐምዛን መቃብር መጎብኘትም ሱንና ነው፤ነቢዩ ﷺ ይጎበኟቸውና ‹‹አስ’ሰላሙ ዐላ አህል አድ’ዲያር ምነል ሙእምኒነ ወልሙስሊሚን፣ወእን’ና እንሻአል’ሏሁ ብኩም ላሕቁን፡፡ አስአሉል’ሏሀ ለና ወለኩም አልዓፍያ›› [በሙስሊም የተዘገበ] በማለት ዱዓእ ያደርጉላቸው ነበር፡፡

    በዚያራ ውስጥ የሚከሰቱ ስህተቶችና ማሳሰቢያዎች

    1 - መቃብሩንና በመዲና የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለመጎብኘት ዓላማ መሳፈር፡፡ የተደነገገው ነቢያዊውን መስጊድ ለመጎብኘትና እዚያ ለመስገድ ዓላማ ጉዞ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ መቃብሩን መጎብኘትም በዚህ ውስጥ ይገባል፡፡

    2 - በዱዓእ ጊዜ ፊትን ወደ መቃብሩ ማዞር፡፡

    3 - ነቢዩን ﷺ መለመንና ከአላህ ሌላ ጉዳዩን እንዲፈጽሙለትና ሃጃውን እዲሞሉለት መጠየቅ፡፡ ይህን ማድረግ በአላህ ማጋራትና ዐቢይ ሽርክ ነው፡፡

    4 - በክፍሉ ግድግዳ ላይ በረከት ለማግኘት ዓላማ መተሻሸትና በእጅ መነካካት፡፡ ይህ ሐራም የሆነ ብድዓና ወደ ሽርክ የሚያደርስ መረማመጃ ነው፡፡

    5 - በነቢዩ ﷺ መቃብር አጠገብ ድምጽን ከፍ ማድረግና ብዙ መቆም፣ወደዚያ በገቡ ቁጥር ከሩቅ ሆኖ ሰላምታ መደጋገም፣ሰላምታ በሚያቀርብበት ጊዜ ሶላት ውስጥ እንደሚደረገው ዓይነት ቀኝ እጅን ደረት ላይ በግራው ላይ አድርጎ መያዝ፡፡



Tags: