ኡድሕይ’ያ

3958

      የኡድሕይ'ያህ ትርጓሜ

ኡድሕይ’ያ

በመሰዊያ ቀናት ወደ አላህ ለመቃረቢያ ዕባዳ ተብሎ የሚታረድ የቤት እንስሳ ነው፡፡

    ኡድሕይ’ያን የሚመለከት ድንጋጌ

    ኡድሕይ’ያ የጠበቀ ሱንና ነው፡፡ አላህ ፡- ‹‹ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፤(በስሙ) ሠዋም፡፡›› [አል-ከውሠር:2] ብሏልና፡፡

    ከአነስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹ነቢዩ ﷺ መልካቸው ነጫጭና በጥቂቱ ጥቁር ያለባቸው ሁለት ቀንዳማ በጎችን ለኡድሕይ’ያ ሠውተዋል፤ሁለቱንም ብስምልላህ ወል’ሏሁ አክበር ብለው በእጃቸው ያረዱ ሲሆን እግራቸውን በበጎቹ አንገቶች አካባቢ ላይ አድርገው ነበር፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ኡድሕይ’ያ የሚታረድበት ጊዜ

    የማረጃ ጊዚው በመሠዊያው ቀን ከዒድ ሶላት በኋላ ጀምሮ እስከ አይ’ያም አት’ተሸሪቅ (የወርሐ ዙልሕጃ አስራ አንደኛው፣አስራ ሁለተኛውና አስራ ሦስተኛው ቀናት) የመጨረሻው ቀን ጸሐይ መጥለቅ ድረስ ነው፡፡

    ለኡድሕይ’ያ ብቁ የሆነ እንስሳ

    1 - አንድ በግ ለአንድ ግለሰብ በቂ ሲሆን የፈለገውን ሰው በአጅሩ ተካፋይ ማድረግ ይችላል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ኡድሕያቸውን ለማረድ ሲፈልጉ ‹‹ብስምል’ላህ፣አላህ ሆይ! (ይህን) ከሙሐመድ፣ከሙሐመድ ቤተሰብና ከሙሐመድ ኡመት (ሕዝቦች) ተቀበል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - አንዱ ግመል እና ወይፈን ለሰባት ሰዎች ብቁ ኡድሕይ’ያ ነው፡፡ ሰባት ሰዎች በአንድ ግመል ወይም ወይፈን በጋራ መሳተፍ ይፈቀዳል፡፡ ከጃቢር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ በግመልና በበሬ በየሰባታችን በአንድ ግመል እንድንሻረክ አዘውናል፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ለኡድሕይያ ብቁ የሆነ የእንስሳ ዕድሜ

    - ከበግ የስድስት ወርና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያለው፡፡

    - ከፍየል ያንድ ዓመት ዕድሜ ያለው፡፡

    - ወይፈን ሁለት ዓመት የሞላው፡፡

    - ከግመል አምስት ዓመት የሞላው፡፡

    ከሁሉም በላጩ ኡድሕይ’ያ

    ከሁሉም በላጩ ኡድሕይ›ያ ሙሉ በሙሉ ከሆነ በዋጋውም የበለጠ ውድና ለድኾችም ይበልጥ ጠቃሚ በመሆኑ ግመል ነው፡፡ ቀጥሎ ሙሉ በሙሉ ያለ ማሻረክ ከተሰዋ ኮርማ በሬ ነው፡፡ ከዚያ በግ፣ከዚያ ቀጥሎ ግመል ለሰባት፣ቀጥሎም በሬ ለሰባት ነው፡፡

    የኡድሕይ'ያ እንስሳ እንከኖች

    1 - ብቁነትን የሚከለክሉ ጉድለቶች

    - ሸውራራ: በዓይኑ ላይ መንሸዋረር ያለበት ሲሆን ዓይኑ የታወረም በዚህ ውስጥ ይካተታል፡፡

    - አንካሳ: መራመድና መጓዝ የማይችል ነው፡፡

    - ከሲታ: በጣም የከሳና ምንም መቅኒ (ስብ) የሌለው፡

    - በሽተኛነቱ በግልጽ የሚታይ

    ለዚህ ማስረጃው ከበራእ ብን ዓዝብ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹ሸውራራነቱ የጎላ ሸውራራ፣አንካሳነቱ የጎላ አንካሳ፣በሽተኛነቱ የጎላ በሽተኛና ምንም መቅኒ የሌለበት ከሲታ እንስሳ ለኡድሕያ አይፈቀድም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    ብለዋል ማለታቸው ነው፡፡ ከነዚህ እንከኖችና ጉድለቶች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውና ከነዚህም የከፉ ጉድለቶች በዚህ ውስጥ ይደመራሉ፡፡

    ሸውራራ
    አንካሳ
    ከሲታ

    2 - ከብቁነት የማያግዱ እንከኖች

    - ጅራተ ቆራጣ: ጅራት ወይም ላት የሌለው፡፡

    - ቀንድ አልባ: ምንም ዓነት ቀንድ የልተፈጠረበት፡፡

    - ቅጥቅጥ: የተቀጠቀጠ በግ፡፡

    - ጆሮው የተቀደደ ወይም የተበሳ ወይም ቀንዱ የተሰበረ፡፡

    ብቁነትን አስመልክቶ ለኡድሕይያ የተባለው ሁሉ ለቤዛና ለሀድይም የሚሠራ ነው፡፡

    ቀንደ ሰባራ
    ቀንድ አልባ
    ጅራተ ቆራጣ

    የኡድሕይያ ክፍፍል

    ከኡድሕይ ሥጋ ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ባለቤቱ ራሱ መብላት፣አንድ ሦስተኛውን በስጦታ መስጠትና አንድ ሦስተኛውን ምጽዋት መስጠት የተደነገገ ነው፡፡ ሁሉንም በሶደቃ መስጠት የተፈቀደ ሲሆን አብዛኛውን ለራሱ ቢበላም የተፈቀደ ነው፡፡

    ጠቃሚ ነጥብ
    ኡድሕይያ የማረድ ሃሳብ ያለው ሰው የዙልሕጃ ወር ከገባ በኋላ እስኪያርደው ድረስ ከጸጉሩ፣ከጥፍሩና ከገላው ምንም ነገር መውሰድ አይፈቀድም፡፡
    ከኡምሙ ሰለማ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹(ከዙልሕጃ የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ከጀመረና አንዳችሁ ኡድሕይያ ማረድ ካሰበ ከጸጉሩና ከገላው ምንም ነገር አይንካ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡
    እንደ ባለቤትና ልጆች ያሉ ስለነሱ ኡድሕይያው የሚታረድላቸው ግን እገዳው አይመለከታቸውም፡፡


Tags: