አዛንና እቃማ

11015

      የአዛንና የእቃማ ትርጓሜ

አዛን

በተለየ ዝክር የሶላት ወቅት መድረሱን ማሳወቂያ ነው፡፡

እቃማ

በተለየ ዝክር ሶላት ሊጀመር መሆኑን ማሳወቂያ ነው፡፡

    አዛንና እቃማን የሚመለከት ብያኔ

    1 - ለብዙ (ለጀማዓ)

    ለአምስቱ የግዴታ ሶላቶች ብቻ ለነዋሪም ሆነ ለመንገደኛ የወል ግዴታ (ፈርድ አል ክፋያ) [ፈርድ አልክፋያ የሚበቃው ያህል ሰው ከፈጸመው ከተቀሩት ላይ ኃላፊነቱ የሚነሳ የወል ግዴታ ነው፡፡] ነው፡፡

    አዛንና እቃማ ጉልህ ከሆኑ የእስላም መለያ ምልክቶችና መገለጫዎች አንዱ በመሆናቸው መተው አይፈቀድም፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ሶላት ሲደርስ አንዳችሁ አዛን ያድርግላችሁ፤ከዚያም ታላቃችሁ በኢማምነት ያሰግዳችሁ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - ለነጠላ ግለሰብ

    ለነጠላ ግለሰብ ሱንና ነው፡፡ ዑቅባ ብን ዓምር t ባስተላለፉት መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹ጌታህ በተራራ አናት ላይ በጎች በሚጠብቅና ከዚያ ለሶላት አዛን አድርጎ በሚሰግድ እረኛ ይገረማል (ይደሰታል)፤አላህ ﷺ ፡- ይህን አገልጋዬን ተመልከቱት፣አዛን ያደርጋል፤እቃማ አድርጎም ይሰግዳል፤እኔን ይፈራል፤ለአገልጋይ ባሪያዬ ምሕረት አድርጌያለሁ፤ጀነትም አስገበዋለሁ ይላል›› [በነሳኢ የተዘገበ] ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

    አዛን ያዘለው ጥበብ

    1 - የሶላት ወቅት መድረሱንና ቦታውን ማስታወቅ፡፡

    2 - ለጀማዓ ሶላት መቀስቀስ፡፡

    3 - ከታላላቅ ጸጋዎች አንዱ የሆነውን ሶላት ይሰግዱ ዘንድ ቸልተኞችን መቀስቀስ የዘነጉትን ማስታወስ፡፡

    አዛን መቼና በምን ምክንያት ተደነገገ ?

    አዛን የተደነገገው በመጀመሪያው ዓመተ ህጅራ ነው፡፡ መናሻው የሶላት ወቅት መድረሱን በሁሉም ሰው ዘንድ እንዲታወቅ ለማድረግ የምልክት መኖር አስፈላጊነትን ሲረዱ ሙስሊሞች በጉዳዩ ላይ ተመካከሩ፡፡

    በዚያው ሌሊት ዐብደላህ ብን ዘይድ ደወል የተሸከመ ሰው በሕልም አዩና ‹‹ይህን ደወል ትሸጣለህ?›› ብለው ሲጠይቁት ሰውየው ‹‹ምን ታደርግበታለህ?›› አላቸው፡፡ ዐብደላህም ፡- ‹‹ለሶላት ጥሪ እናደርግበታለን›› አሉት፡፡

    ሰውየው መለሰና ‹‹ከዚህ በላጭ የሆነውን ነገር ላመላክትህ?›› ሲላቸው ‹‹አዎ›› አሉትና ዛሬ የሚታወቀውን አዛን አስተማራቸው፣ከዚያም እቃማን አስተማራቸው፡፡ [በዳሪሚ የተዘገበ]

    ሲነጋ ወደ አላህ መልእክተኛ ﷺመጣሁና ያየሁትን ነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹ይኸ - እንሻአሏህ- እወነተኛ ሕልም ነውና ከቢላል ጋር ተነስተህ ያየኸውን አድርሰውና እርሱ ካንተ የበለጠ ከፍተኛና ያማረ ድምጽ ስላለው በዚህ ለሶላት ጥሪ (አዛን) ያድርግበት፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] አሉኝ ብለዋል ዐብደላህ፡፡

    የአዛን ትሩፋት

    1 - ድምጹ ደርሶት የሰማ ሰው ሁሉ በቅያማ ቀን ለሙአዝኑ አላህ ﷺ ዘንድ ይመሰክርለታል፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ጅን፣ሰውም ሆነ ማንኛውም ነገር የሙአዝንን ድምጽ ሰምቶ በቅያማ ቀን ሳይመሰክርለት የሚቀር አይኖርም፡፡››[በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - ሰዎች አዛን ማድረግ የያዘውን ትሩፋት ቢያውቁ ኖረው በተሸቀዳደሙበት ነበር፡፡ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሰዎች በአዛንና በመጀመሪያው ሶፍ ያለውን (ታላቅ አጅር) ቢያዉቁና ያንን ለማግኘት እጣ መጣል [ሙአዝንነትንና የመጀመሪያ ሶፍን በእጣ ለማግኘት እጣ መጣል] ቢኖርባቸው እንኳ በእጣ በተሸቀዳደሙበት ነበር፡፡››[በቡኻሪ የተዘገበ]

    አዛን ትክክለኛ እንዲሆን መሟላት ያላባቸው ቅድሚያ ሁኔታዎች

    1 - ሙአዝኑ ሙስሊም፣ወንድና ጤናማ አእምሮ ያለው መሆን፡፡

    2 - ቅደም ተከተሉን የጠበቀ መሆን፡፡

    3 - በቃላቱ መካከል ብዙ የጊዜ ልዩነት በማይሰጥ ሁኔታ ተከታታይ መሆን፡፡

    4 - የሶላት ወቅት በሚገባበት ጊዜ መሆን፡፡

    የአዛን ሱናዎች

    1 - ፊትን ወደ ቅብላ ማዞር፡፡

    2 - ሙአዝኑ ከሁለቱ ሐደሦች ንጹሕ መሆን፡፡

    3 - ‹‹ሐይ’ያ ዐለስ’ሶላህ ሐይ’ያ ዐለል ፈላሕ›› ሲባል አንገት ወደ ቀኝና ወደ ግራ ማዞር፡፡

    4 - ሙአዝኑ አመልካች ጣቶቹን በሁለቱ ጆሮዎች ውስጥ ማድረግ፡፡

    5 - ሙአዝኑ ጥሩና ከፍተኛ የሆነ ድምጽ ያለው መሆን፡፡

    6 - አዛኑን ግልጽ በሆነ የቃላት አደራደርና ረጋ ባለ ሁኔታ ማድረግ፡፡

    ጣቱን ጆሮዎቹ ውስጥ ያደርጋል

    የአዛንና የእቃማ አደራረግ

    1 - የአዛን ቃላት ፡- ‹‹አል’ሏሁ አክበሩ አል’ሏሁ አክበር፣አልሏሁ አክበሩ አልሏሁ አክበር፤አሽሀዱ አንላእላሀ እል’ለል’ሏህ፣አሽሀዱ አንላእላሀ እል’ለል’ሏህ፣ አሽሀዱ አን’ነ መሐመደን ረሱሉ’ልሏህ፤አሽሀዱ አን’ነ መሐመደን ረሱሉ’ልሏህ፤ሐይ’ያ ዐለስ’ሶላህ፣ሐይ’ያ ዐለስ’ሶላህ፤ሐይ’ያ ዐለል ፈላሕ፣ሐይ’ያ ዐለል ፈላሕ፤አል’ሏሁ አክበሩ አል’ሏሁ አክበር፣ላእላሀ እል’ለል’ሏህ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    ትርጉሙ፡- ‹‹አላህ ከሁሉም በላይ ኃያል ነው፡፡ ከአላህ በስተቀር አምልኮት የሚገባው ሌላ አምላክ አለመኖሩን እመሰክራለሁ፡፡ ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ፡፡ ወደ ሶላት ኑ! ወደ መድህን ኑ! አላህ ከሁሉም በላይ ኃያል ነው፡፡ ከአላህ በስተቀር አምልኮት የሚገባው ሌላ አምላክ የለም፡፡›› ማለት ነው፡፡

    2 - የእቃማ ቃላት ፡- ‹‹አል’ሏሁ አክበሩ አል’ሏሁ አክበር፣ አሽሀዱ አንላእላሀ እል’ለል’ሏህ፣አሽሀዱ አን’ነ መሐመደን ረሱሉ’ልሏህ፤ሐይ’ያ ዐለስ’ሶላህ፣ሐይ’ያ ዐለል ፈላሕ፣ቀድ ቃመትስ’ሶላቱ ቀድ ቃመትስ’ሶላህ፤አል’ሏሁ አክበሩ አል’ሏሁ አክበር፣ላእላሀ እል’ለል’ሏህ፡፡››

    ተጨማሪው ‹‹ቀድ ቃመትስ’ሶላህ›› ማለት እነሆ ሶላቱ ተጀመረ›› ማለት ነው፡፡

    አዛን ሲደረግ ለሰማ ሰው ማድረጉ የተወደደ ነገር

    1 - ሙአዝኑ የሚለውን ደግሞ ማለት፣ ‹‹ሐይ’ያ ዐለስ’ሶላህ፣ሐይ’ያ ዐለል ፈላሕ›› ሲል ብቻ ‹‹ላ ሐውለ ወላ ቁው’ወተ እል’ላ ብል’ላህ›› ማለት፡፡ ትርጉሙ ‹‹መላም ሆነ ኃይል ከአላህ ብቻ ነው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    2 - ከአዛን በኋላ፡- ‹‹አሽሀዱ አንላእላሀ እል’ለል’ሏህ፣ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ፣ወአን’ነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ፣ረዲቱ ብል’ላህ ረብ’በን ወብሙሐመድን ረሱለን፣ወብል እስላም ዲና፡፡››ማለት፡፡ ትርጉሙ፡-‹‹ከአላህ በስተቀር አምልኮት የሚገባው ሌላ አምላክ አለመኖሩን፣እርሱ ምንም ሸሪክ የሌለው አንድ አምላክ መሆኑንና ሙሐመድ አገልጋዩና መልእክተኛው መሆናቸውን እመሰክራለሁ፡፡ በአላህ ጌታነት፣በሙሐመድ መልእክተኛነትና በእስላም ሃይማኖት ረክቼበ ታለሁ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    3 - በነቢዩ ﷺ ላይ ሰለዋት ካወረደ በኋላ ‹‹አልሏሁም’መ ረብ’በ ሃዚህ አድ’ደዕወት አት’ታም’መህ፣ወስ’ሶላት አል ቃእመህ፣ኣት ሙሐመደን አል ወሲለተ ወል ፈዲለህ፣ወብዐሥሁ መቃመን መሕሙደን አል’ለዚ ወዐድተህ፡፡›› ማለት፡፡

    ትርጉሙ ፡-‹‹የዚህ የተሟላ ጥሪና የሚሰገደው ሶላት ጌታ (ባለቤት) የሆንከው አላህ ሆይ! ለሙሐመድ ወሲላን (በጀነት ውስጥ ያለ ታላቁን ደረጃ) እና ብልጫን ስጣቸው፡፡ ቃል ወደ ገባህላቸው ምስጉን ደረጃም ከፍ አድርጋቸው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    4 - በዚህ ወቅት ዱዓእ ተቀባይነት ስላለው በአዛንና በእቃማ መካከል ለራስ ዱዓእ ማድረግ፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ዱዓእ በአዛንና በእቃማ መካከል ተቀባይነት አያጣም፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    ከአዛንና እቃማ ድንጋጌዎች

    1 - እንደ ዙህርና ዐስር ያሉ ሶላቶች በጥምረት (ጀምዕ) ሲሰገዱ በአንድ አዛን ብቻ በመወሰን ለየሶላቱ እቃማ ማድረግ፡፡

    2 - እቃማ ከተደረገ በኋላ ሶላቱ ሳይጀመር ቢቆይ እቃማውን እንደገና ማድረግ አስፈላጊ አይደለም፡፡

    3 - ሙአዝኑ በአዛን ቃላት ላይ ስህተት ላለመስራት መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፡-

    ሀ) ‹ኣ›ን ‹ኣ› ራብዕ አድርጎ ‹‹ኣልሏሁ አክበር›› ማለት፡፡ ይህ አላህ ኃያል ነውን ? የሚል ጥያቄ ማቅረብ ነው፡፡

    ለ) ‹‹አል’ሏሁ አክባር›› ‹በ›ን በ‹ባ› ራብዕ መለወጥ፡፡

    ሐ) ‹‹አል’ሏሁ ወአክበር›› በማለት ‹ወ›ን መጨመር፡፡

    4 - ለሶላት እቃማ ከተደረገ በኋላ ሱንና ሶላት መጀመር አይፈቀድም፡፡ ሱንናውን ከጀመረ በኋላ እቃማ ከተደረገ ግን ለማጠናቀቅ ትንሽ ብቻ ከቀረው ያጠናቅቃል፤ካልሆነ ግን ያለ ሰላምታ አቋርጦት ከኢማሙ ጋር የፈርዱን ሶላት ይቀላቀላል፡፡

    5 - ራሱን በደንብ ያወቀ ሕጻን ልጅ አዛን ቢያደርግ አዛኑ ትክክለኛ ነው፡፡

    6 - በእንቅልፍ ወይም በመዘንጋት ላመለጠ ሶላት አዛንና እቃማ ማድረግ የተደነገገ ነው፡፡ ሶሓባ ጸሐይ እስክትወጣ ድረስ ተኝተው የሱብሕ ሶላት ሲያመልጣቸው፣ነቢዩ ﷺ ቢላልን አዘዙና አዛን አደረጉ፡፡ ከዚያም ዉዱእ አደረጉና ሁለት ረክዓ የፈጅርን ሱንና ሰገዱ፡፡ በመቀጠልም ቢላልን እቃማ እንዲያደርጉ አዘው አደረጉና (ነቢዩﷺ) የሱብሕን ሶላት አሰገዷቸው፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]

    7 - መስጊድ ውስጥ የነበረ ሰው ዑዝር ከሌለው በስተቀር አዛን ከተደረገ በኋላ ከመስጊድ አይወጣም፡፡ አቡ ሁረይራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት፡- ‹‹አንዳችሁ መስጊድ ውስጥ እያለ ለሶላት ጥሪ (አዛን) ከተደረገ ሶላቱን ሳይሰግድ እንዳይወጣ የአላህ መልእክተኛ ﷺ አዞናል፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    8 - መአዝኑ በሁለቱ ሸሃዳ ጊዜ ድምጹን ቀነስ አድርጎ ‹‹ሐይ’ያ . . ›› ላይ ሲደርስ መልሶ ወደነበረበት ይመልሳል፡፡ ይህም በሱንና [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] የተረጋገጠ በመሆኑ ነው፡፡

    ተገቢ አይደለም

    1 - አዛንን ፍደላቱን፣አናባቢዎቹንና ተነባቢዎቹን በሚለውጥና በቃላቱ ላይ ጉድለት ወይም ጭማሬ በሚያስከትል ሁኔታ በዜማና በቅላጼ ማድረግ፡፡

    2 - ከአዛን በኋላ በነቢዩ ﷺ ሶላትና ሰላም ሲያወርዱ ድምጽን ከፍ ማድረግ፡፡

    3 - ‹‹ቀድ ቃመትስ’ሶላቱ›› ሲባል አንዳንዶች ሲሉት የሚሰማው ‹‹አቃመሃሏሁ ወአዳመሃ›› ማለት፡፡

    የፈጅር አዛን…..

    ለሱብሕ ሶላት የተደነገገው ሁለት አዛን ነው፡፡ አንደኛው የሶላቱ ወቅት ከመግባቱ በፊት ሲሆን፣ሁለተኛው በሶላቱ ላይ ለመገኘት ወቅቱ መግባቱን ለማሳወቅ ነው፡፡ በመጀመሪው አዛን ሙአዝኑ ሁለት ጊዜ ‹‹አስ›ሶላቱ ኸይሩን ምነን›ነውም›› ይላል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹በሱብሕ ሶላት በመጀመሪያው አዛን ስታደርግ አስ›ሶላቱ ኸይሩን ምነን›ነውም›› አስ›ሶላቱ ኸይሩን ምነን›ነውም›› በል፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡ ይህም ‹‹ሶላት ከእንቅልፍ በላጭ ነው›› ማለት ነው፡፡

    አዛን ሸይጣን ያባርራል
    ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹ለሶላት ጥሪ ሲደረግ አዛኑን ላለመስማት ሸይጣን (ከፍርሃቱ ብዛት) ሆዱን እያስተነፈሰ ይሸሻል፤አዛኑ ሲያበቃ ተመልሶ ይመጣል:: እቃማ ሲደረግ ደግሞ ይሸሻል፤ተሥዊቡ [እዚህ ላይ ተሥዊብ ማለት እቃማን ለማመልከት ነው፡፡] (እቃመው) ሲያበቃ ተመልሶ ይመጣና (ሰጋጁ ሶላቱን ሲጀምር) እንዲህ ያለውን እንደዚያ ያለውን ነገር አስታውስ በማለት ያላስታወሰውን እያመጣለት ይወሰውሰዋል፤ሰውየው ስንት እንደሰገደ እንኳ እንዳያውቅ እስከማድረግ ድረስ ይጎተጉተዋል፡፡ ስለዚህ አንዳችሁ ሦስት ይሁን አራት ስንት እንደሰገደ ካላወቀ እንደ ተቀመጠ ሁለት ሱጁድ ያድርግ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
    ጠቃሚ ነጥቦች

    1 - ከአዛን በኋላ ከእቃማ በፊት ከመስጊድ መውጣት የተፈቀደ አይደለም፡፡ አቡ ሁረይራ (ረዐ) ከአዛን በኋላ መስጊድ ጥሎ የወጣ ሰው አይተው ‹‹ይኸማ የአቡል ቃሲምን (የነቢዩንﷺ) ትእዛዝ የጣሰ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

    2 - ለማንኛውም የነፍል ሶላት፣ለዒዶችም፣ለእስትስቃእም፣ለጀናዛ ሶላትም ሆነ ለኩሱፍ ሶላት አዛንም ሆነ እቃማ አይደረግም፡፡ ለኩሱፍ ሶላት ብቻ ነው ‹‹አስ’ሶላቱ ቃእመህ›› (እነሆ ሶላት ሊሰገድ ነው) የሚባለው፡፡

    3 - ሙአዝኑ በዝናም ወይም በከባድ የብርድ ሁኔታ ‹‹ሐይ’ያ ዐለስ’ሶላት›› ካለ በኋላ ‹‹እነሆማ በየሰፈራችሁ ስገዱ!›› ይላል፡፡