ችግር ያለባቸው ሰዎች ሶላት

5672

      የአዕዛር ትርጓሜ

አዕዛር (ችግሮች)

በሽታ፣ጉዞ፣ፍርሃት

    1 - የታመመ ሰው ሶላት

    የታመመ ሰው ጤናው በፈቀደለት መጠን ሶላትን መስገድ ይኖርበታል፡፡ እንደ ጤነኛ ሰው መስገድ ከቻለ ያን ማድረግ ግዴታ ይሆናል፡፡ ካልቻለም በሚችለው ሁኔታ ይሰግዳል፡፡

    ቆሞ መስገድ የሚችል ከሆነ ቆሞ የመስገድ ግዴታ ነው፡፡ መቆም ካልቻለ ተቀምጦ ይሰግዳል፡፡ መቀመጥ ካልቻለ በጎኑ ተኝቶ ፊቱን ወደ ቅብላ በመመለስ ይሰግዳል፡፡ በጎኑ መስገድ ካልቻለ በጀርባው ተኝቶ ከተመቸው እግሮቹን ወደ ቅብላ በማድረግ ካልተመቸም እንደሚችለው ሆኖ ይሰግዳል፡፡

    ማሰረጃው ፡- ‹‹አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት፤›› [አል-ተጋቡን፡16]

    የሚለው የአላህ ቃል ነው፡፡ ነቢዩም ﷺ ለዒምራን ብን ሐሲን (ረዐ) ፡- ‹‹ቆመህ ስገድ፤ካልቻልክ ተቀምጠህ፣ካልቻልክም በጎንህ ተኝተህ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የታመመ ሰው ሶላትን ከሚመለከቱ ብያኔዎች በከፊል

    1 - የታመመ ሰው ተቀምጦ ከሰገደና ሱጁድ ማድረግ የሚችል ከሆነ ሱጁድ ግዴታ ይሆንበታል፡፡

    2 - ተቀምጦ ሰግዶ ሱጁድ መውረድ ከተሳነው፣ለሱጁድ ከሩኩዕ ትንሽ ዝቅ በማለት በአካል ምልክት ሩኩዕና ሱጁድን ያመለክታል፡፡ በአካሉ ማመልከት ካቃተው በራሱ ምልክት ያደርጋል፡፡ በጀርባው ሆኖ ሲሰግድም እንደዚሁ በራሱ ያመለክታል፡፡

    3 - የታመመ ሰው ለየሶላቱ ጦሃራ ማድረግ የሚቸግረው ከሆነ፣ወይም ሶላቶችን በጊዜያቸው መስገድ የሚከብደው ከሆነ፣ዙህርና የዐስርን ሶላት አንድ ላይ፣የመግሪብና የዕሻእ ሶላትን አንድ ላይ፣ምቹ ሆኖ ባገኘው በአንደኛው ወይም በሁለተኛው ወቅት አንድ ላይ በማጣመር (በጀምዕ) መስገድ ይችላል፡፡

    4 - አእምሮውን እስካልሳተ ድረስ ከታመመ ሰው ላይ የሶላት ግዴታ ምን ጊዜም ቢሆን አይነሳም፡፡ በመሆኑም ታምሜያለሁ በሚል ሶላትን ችላ ማለት የለበትም፣በተቻለው ሁሉ ሶላቱን ለመስገድ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

    5 - ታማሚው ለቀናት ራሱን ስቶ ከዚያ የሚነቃ ከሆነ ሲነቃ በሚችለው መንገድ ይሰግዳል፡፡ ራሱን በሚስትበት ቀናት ያመለጡትን ሶላቶች መክፈል አይኖርበትም፡፡

    ራሱን የሚስተው ለአጭር ጊዜ፣ለምሳሌ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ብቻ ከሆነ ግን በሚመቸው ጊዜ ያመለጠውን ሶላት ሰግዶ ይከፍላል፡፡

    ተክቢራ
    ቅራኣ (ምንባብ)
    ሩኩዕ
    ሱጁድ

    2 - የሙሳፍር (መንገደኛ) ሶላት

    ለመንገደኛ ሰው የባለ አራት ረክዓ ሶላቶችን (ዙህር፣ዐስርና ዕሻእ) ወደ ሁለት ረክዓ አሳጥሮ መስገድ የተደነገገ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹በምድር ላይ በተጓዛችሁ ጊዜ፣እነዚያ የካዱት ያውኩናል ብላችሁ ብትፈሩ፣ከሶላት (ባለ አራት ረክዓ የኾኑትን) ብታሳጥሩ በናንተ ላይ ኃጢአት የለም፤ከሓዲዎች ለናንተ በእርግጥ ግልጽ ጠላት ናቸውና፡፡›› [አል-ኒሳእ፡101]

    አነስ ብን ማሊክ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹ከአላህ መልእክተኛ ﷺ ጋር ከመዲና ወደ መካ ስንሄድ እስክንመለስ ድረስ ሁለት ረክዓ ያሰግዱን ነበር፡፡›› [በነሳኢ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የጉዞ ምንነት

    በተለምዶ ጉዞ ነው ተብሎ የሚጠራ ርቀት ሁሉ ሶላት የሚያጥርበት ጉዞ (ሰፈር) ነው፡፡

    ሶላትን ማሳጠር (ቀስር)

    1 - አንድ መንገደኛ ሶላትን ማሳጠር የሚጀምረው የሚኖርበትን አገር መኖሪያዎች ለቆ ከሄደ በኋላ ነው፡፡ በመኖሪያ ቦታው እያለ ማሳጠር አይፈቀድለትም፡፡ ነቢዩ ﷺ ለቀው ከሄዱ በኋላ እንጂ ማሳጠራቸው አልተረጋገጠምና፡፡

    2 - ተጓዡ መንገደኛ ወደ አንድ አገር ደርሶ አራት ቀናትና ከዚያ በላይ እዚያ ለመቆየት ከፈለገ ሶላትን አሟልቶ መስገድ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ከአራት ቀናት ላነሰ ጊዜ መቆየት ካሰበ ግን ማሳጠር ይፈቀድለታል፡፡

    የተወሰነ ጊዜ የመቆየት ሀሳብ ከሌለውና ጉዳይ ኖሮት እስኪፈጸምለት ብቻ የሚጠብቅ ከሆነ፣ ቆይታው ከአራት ቀናት በላይ ቢሆን እንኳ እሰኪመለስ ድረስ ሶላትን አሳጥሮ መስገድ ይፈቀድለታል፡፡

    3 - ነዋሪ ከሆነ ኢማም ጋር የሚሰግድ መንገደኛ፣የደረሰበት አንድ ረክዓ ብቻ ቢሆን እንኳ ሶላቱን አሟልቶ መስገድ ይኖርበታል፡፡

    4 - ነዋሪ የሆነ ሰው ሶላቱን አሳጥሮ በሚሰግድ መንገደኛ ኢማምነት የሚሰግድ ከሆነ ከኢማሙ ሰላምታ በኋላ ተነስቶ ሶላቱን ማሟላት ይኖርበታል፡

    ሁለት ሶላቶችን ማጣመር (ጀምዕ)

    1 - ለመንገደኛና ለታመመ ሰው ሁለት ሶላቶችን፣ዙህርና ዐስርን በአንደኛቸው ወቅት፣መግሪብና ዕሻንም በአንደኛቸው ወቅት አንድ ላይ በማጣመር መስገድ ይፈቀዳል፡፡

    በመጀመሪያው ሶላት ወቅት አጣምሮ ከሰገደ ቀዳሚ ጥምረት (ጀምዑ ተቅዲም) ፣ በሁለተኛው ሶላት ወቅት ካጣመረ ደግሞ የዘገየ ጥምረት (ጀምዑ ተእኺር) ይሆናል፡፡

    2 - በመስጊድ ለሚሰግድ ሰው በዝናም ምክንያት ችግርና አዋኪ ሁኔታ የሚፈጠርበት ከሆነ ሁለት ሶላቶችን ማጣመር ይፈቀዳል፡፡ ለሴቶችና እቤት ለሚሰግዱት ግን ማጣመር አይፈቀድላቸውም፡፡

    3 - ማጣመርና ማሳጠር (ጀምዕና ቀስር) የግድ አንድ ላይ መሆን የለባቸውም፡፡ ማጣመርና ማሳጠር አንድ ላይ ሊፈጸም ይችላል፤ማሳጠር የሌለበት ማጣመር ብቻም ሊሆን ይችላል፡፡

    የመንገደኛ ሶላት በተሳፈረበት ማጓጓዣ ላይ

    1 - ነፍል (ግዴታ ያልሆነ) ሶላት

    ሶላቱ በዑዝርም ሆነ ያለ ዑዝር ያለ ገደብ ይፈቀዳል፡፡ ይህም የአላህ መልእክተኛ ﷺ ነፍል ሶላትን በግመላቸው ላይ ሆነው ወደ ሄደችበት አቅጣጫ ይሰግዱ እንደ ነበር [በቡኻሪ የተዘገበ] የተረጋገጠ በመሆኑ ነው፡፡

    2 - የግዴታ ሶላት ከሆነ

    ወደ መሬት ወርዶ መስገድ የማይችል ከሆነ፣ወይም ከወረደ ተመልሶ ለመሳፈር የሚቸገር ከሆነ፣ወይም በጠላት እንዳይጠቃ ከሰጋና በመሳሰሉት ሁኔታዎች በተሳፈረበት መጓጓዣው ላይ ሆኖ መስገዱ ትክክለኛ ይሆናል፡፡ አሰጋገዱ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ፡-

    ሀ- መርከብ ላይ ያለ ሆኖ ፊቱን ወደ ቅብላ ማዞር፣ሩኩዕና ሱጁድ ማድረግ የሚችል ከሆነ ሶላቱን በተለመደው የአሰጋገድ ሁኔታ መስገድ ይኖርበታል፡፡

    ለ- ፊቱን ወደ ቅብላ ማዞር ቢችልም ሩኩዕና ሱጁድ ማድረግ የማይችል መሆን፡፡ በዚህ ሁኔታ በእሕራም ተክቢራ ላይ ፊቱን ወደ ቅብላ አድርጎ ሶላቱን ይጀምርና ማጓጓዣው ወዳመራበት አቅጣጫ ይሰግዳል፤ሩኩዕና ሱጁድን በምልክት ያደርጋል፡፡

    3 - የፈራ ሰው ሶላት (ሶላቱል ኸውፍ)

    ሶላቱል ኸውፍ በሚኖሩበት ቦታም ሆነ በጉዞ ላይ፣በሁሉም ዓይነት የተፈቀደ ውጊያ ላይም የተደነገገ ነው፡፡ ክታብና ሱንና ድንጋጌውን አመልክተዋል፡፡

    1 - ከቁርኣን ሚከተለውን የአላህ ቃል እናገኛለን ‹‹በውስጣቸውም በኾንክና ሶላትን ለነርሱ ባስሰገድካቸው ጊዜ፣ከነሱ አንዲት ጭፍራ ካንተ ጋር ትቁም፤መሣሪያዎቻቸውንም ይያዙ፡ በግንባራቸውም በተደፉ ጊዜ፣ከስተኋላችሁ ይኹኑ፤(እነዚህ ይኺዱና) ያልሰገዱትም ሌሎቹ ጭፍሮች ይምጡ፤ከአንተም ጋር ይስገዱ፤ጥንቃቄዎቻቸውንና መሣሪያዎቻቸውንም ይያዙ፡፡›› [አል-ኒሳእ፡102]

    2 - የሱንና ማስረጃው ደግሞ ነቢዩ ﷺ ከሶሓባቸው ጋር መስገዳቸውና ከሳቸውም በኋላ ሰሓባ t መስገዳቸው ነው፡፡

    የሶላቱል ኸውፍ አሰጋገድ

    የፍርሃት መኖር በሶላት የረክዓ ቁጥር ላይ ተጽእኖ የለውም፡፡ በነዋሪነት ከሆነ በመደበኛው አሰጋገድ ይከናወናል፡፡ በጉዞ ላይ ከሆነ ግን የአሰጋገዱ ሁኔታ የተለየ ሆኖ በማሳጠር (በቀስር) ይሰገዳል፡ አሰጋገዱን አስመልክቶ የተለያዩ ገጽታዎች የተገለጹ ሲሆን ሁሉም የተፈቀዱ ናቸው፡፡

    ይህን ሶላት የሚያስፈቅደው ፍርሃት በሁለት ሁኔታዎች ይገለጻል ፡-

    አንደኛው ሁኔታ ፡- ጠላት ጥቃት እንዳይሰነዝር መፍራት

    ሶላቱ ከነቢዩ ﷺ ከተላለፉት የአሰጋገድ ሁኔታዎች በአንደኛው የአሰጋገድ ሁኔታ ይሰገዳል፡፡ ከዘገባዎቹ ታዋቂው (መሽሁሩ) በሰህል ብን አቢ ሐትማህ (ረዐ) ሐዲሥ ውስጥ የቀረበው ሲሆን እሱም፡- ኢማሙ ጦሩን በሁለት ቡድን ይከፍልና አንደኛው ቡድን የጠላትን ግንባር ይጠብቃል፡፡

    ሁለተኛው ቡድን ከኢማሙ ጋር አንድ ረክዓ ይሰግዳል፤ኢማሙ ለሁለተኛ ረክዓ ተነስቶ ሲቆም ከኢማሙ የመለየት ንይ’ያ አድርጎ ለራሱ ሰግዶ በሰላምታ ያበቃና ወደ ጠላት ግንባር ለጥበቃ ይሄዳል፡፡

    ከዚያ አንደኛው ቡድን ይመጣና ከኢማሙ ጋር ሁለተኛውን ረክዓ ይሰግዳል፤ኢማሙ ለተሸሁድ ሲቀመጥ እነሱ ይነሱና ሁለተኛውን ረክዓ ለራሳቸው ይሰግዳሉ፡፡ ኢማሙ በተሸሁድ ላይ ቆይቶ እዚያው ይጠብቃቸውና ተቀምጠው ተሸሁድ ካሉ በኋላ ኢማሙ ከነሱ ጋር ሶላቱን በሰላምታ ያበቃል፡፡ [በቡኻሪ የተዘገበ]

    ይኸኛው አሰጋገድ ሶላቱ በጉዞ ላይ (ሶላቱል ሙሳፍር) ከሆነ ወይም በመኖሪያ አገር የፈጅር ሶላት ከሆነ ነው፡፡ በመኖሪያ ቦታ ከሆነ ወይም የመግሪብ ሶላት ከሆነ ግን፣የመጀመሪውን ቡድን ሁለት ረክዓ ያሰግድና ከርሱ የመለየት ንይ’ያ አድርገው ቀሪውን ለራሳቸው አሟልተው በሰላምታ ያበቃሉ፡፡

    የሰገደው ቡድን ይሄድና ሁለተኛው ቡድን ይመጣል፤ኢማሙ የቀረውን ረክዓ አሰግዷቸው ለመጨረሻው ተሸሁድ ተቀምጦ እዚያው ይጠብቃቸዋል፡፡ እነሱ ግን ከርሱ የመለየት ንይ’ያ በማድረግ ተነስተው የቀረውን ረክዓ ያሟሉና ለመጨረሻው ተሸሁድ ተቀምጠው ከኢማሙ ጋር ሶላቱን በሰላምታ ያጠናቅቃሉ፡፡

    ሁለተኛው ሁኔታ ፡- ፍርሃቱ አይሎ ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ መስገድ ሳይቻላቸው ሲቀር

    በዚህ ሁኔታ ውስጥ እግረኛም ፈረሰኛም ሆነው ከተቻለ ፊታቸውን ወደ ቅብላ በማዞር ካልተቻለም ወደ ማንኛውም አቅጣጫ ይሰግዳሉ፡፡ ይህም እብን ዑመር (ረዐ) እንዳሉት ሁሉ፡- ‹‹ከዚያ የበረታ ፍርሃት ከኖረ እግረኛ ወይም ጋላቢም ሆነው ፊታቸውን ወደ ቅብላ አዙረው ወይም ሳያዞሩ ይሰግዳሉ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]

    ማለት ነው፡፡ ሩኩዕና ሱጁድን በምልክት ያደርጋሉ፡፡ ውጊያ ሲበረታ እንደሚሆነው ዓይነት እግረኛ ወይም በአይሮፕላን ወይም በታንክ ውስጥና ሶላትን በመደበኛው አሰጋገድ መፈጸም በማያስችሉ መሰል ሁኔታዎች ውስጥ እንደ አመቺነቱ ይሰግዳሉ፡፡ ‹‹ብትፈሩም እግረኞች ወይም ጋላቢዎች ኾናችሁ (ስገዱ)፣›› [አል-በቀራህ፡239]

    አይሮፕላን ውስጥ ይሰግዳል
    መርከብ ውስጥ ይሰግዳል
    ታንክ ውስጥ ሆኖ ይሰግዳል
    የሸሪዓው ገርነት
    ከእስላማዊው ሸሪዓ ልዩ መለያዎች ውስጥ አንዱ ገርነቱ፣ቀላልነቱና ችግር አስወጋጂነቱ ነው፡፡ ‹‹የሚከብድ ነገር ማቅለያውን ያስከትላል›› የሚለው በሸሪዓው ውስጥ አጠቃላይ የሆነ መርሕ ነው፡፡