ተየሙም

5384

      የተየሙም ትርጓሜ

ተየሙም በቋንቋ ትርጉሙ

ማሰብና ወደ አንድ ነገር ማምራት፡፡

ተየሙም በሸሪዓዊ ትርጉሙ

ለጦሃራ ዓላማ ፊትና እጆችን በንጹሕ የመሬት ገጽ ማበስ

    ተየሙምን የሚመለከት ብያኔ

    እንደ ሶላት ላሉና ጦሃራ ቅድመ ግዴታ (ሸርጥ) ለሆነባቸው ዕባዳዎች ውሃ ሲጠፋ ወይም መጠቀሙ አዳጋች ሆኖ ሲገኝ ተየሙም ማድረግ ግዴታ ይሆናል፡፡ ጦሃራ ሙስተሐብ ለሆነባቸው ቁርኣንን መቅራት ለመሳሰሉ ጉዳዮች ደግሞ የተወደደ ይሆናል፡፡

    ተየሙም የተደነገገ ስለመሆኑ ማስረጃዎች

    1 - አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ፡፡ ከሱም ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን እበሱ፡፡›› [አል ማኢዳህ፡6].

    2 - ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል - ‹‹ከኔ በፊት ለማንም ልተሰጡ አምስት ነገሮች ተሰጥተውኛል፡- ያንድን ወር የጉዞ ርቀት በጠላቶች ላይ በተለቀቀ ፍርሃት ብቻ (በአላህ) ታግዤያለሁ፡፡ ምድሪቱ በሞላ መስገጃና ንጽሕና መስጫ ተደርጋልኛለችና ሶላት ደረሰበት ማንኛውም ሰው በደረሰበት ቦታ ይስገድ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]ብለዋል፡፡

    የተየሙም ድንጋጌ የያዘው ጥበብ

    1 - ለመሐመድ ﷺ ኡመት ዕባዳን ገር ማድረግ፡፡

    2 - እንደ በሽታ ወይም ከባድ ቅዝቃዜ ባሉትና በመሳሰሉት

    አንዳንድ ሁኔታዎች ውሃን በመጠቀም ሊደርስ

    የሚችለውን ጉዳት ማስወገድ፡፡

    3 - ከዕባዳ ጋር የማያቋርጥ ትስስር መፍጠርና በውሃ መቋረጥ ከዕባዳ መቆራረጥን ማስቀረት፡፡

    ተየሙም መቼ?

    1 - ውሃ በሚታጣበት ጊዜ

    አላህ U እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ፡፡›› [አል ማኢዳህ፡6]

    2 - ውሃ እያለም ቢሆን ውሃውን መጠቀም አዳጋች ሲሆን

    ሕመምተኛ ወይም መንቀሳቀስ የተሳነውና ዉዱእ ለማድረግ የሚያግዘው የሌለው በዕድሜ የገፋ ሰውን የመሳሰለ፡፡

    በዕድሜ የገፋ ሰው
    የታመመ ሰው

    3 - ውሃን መጠቀም ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋት ሲኖር

    ከነዚህ መካከል፡-

    ሀ- ውሃን ቢጠቀም ሕመሙ የሚበረታበት በሽተኛ፡፡

    ለ- ከባድ ብርድ ያለበትና ውሃውን የሚያሞቅበት ነገር የሌለው ሆኖ በቀዝቃዛው ቢታጠብ እታመማለሁ የሚል ጠንካራ ግምት ያደረበት ሰው፡፡ አምር ብን አልዓስ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ቅዝቃዜው ስለበረታ ተየሙም ማድረጋቸውን ነቢዩ ﷺ ተቀብለው ያጸደቁላቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ [በአቡ ዳውድ የተዘገበ]

    ሐ- ራቅ ያለ ቦታ ላይ ከሆነና ለመጠጥ ከሚያስፈልገው አነስተኛ ውሃ ብቻ ኖሮት ሌላ ውሃ ማምጣት የማይችል በሚሆንበት ጊዜ፡፡

    የተየሙም አደራረግ

    1 - አፈሩ ላይ በሁለት እጆቹ አንድ ጊዜ ብቻ መምታት፡፡

    2 - ከዚያም የተጣበቀ አፈር ካለ ለመቀነስ እጆቹን ላይ እፍ ማለት፡፡

    3 - በመቀጠል አንድ ጊዜ ፊቱን በእጆቹ ማበስ፡፡

    4 - ከዚም የመዳፎቹን የውጭ ክፍል የቀኙን መዳፍ ጀርባ በግራው የውስጥ መዳፍ፣የግራውን ጀርባ ደግሞ በቀኙ ውስጥ መዳፍ ማበስ፡፡ ለዚህ ማሰረጃው ከዐማር (ረዐ) የተላለፈውና ነቢዩ ﷺ ሁለቱን መዳፎቻቸውን መሬት ላይ መትተው እፍ ካሉባቸው በኋላ ፊታቸውንና መዳፎቻቸውን አበሱ፤ [-በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] የሚለው ሐዲስ ነው፡፡

    የተየሙም ግዴታዎች

    1 - ንይያ ማድረግ፡፡

    2 - ፊትን ማበስ፡፡

    3 - ሁለቱን መዳፎችን ማበስ፡፡

    4 - ቅደም ተከተሉን መጠበቅ፤ከፊት በመጀመር መዳፎችን ማስከተል፡፡

    5 - ማከታተል፤መዳፎችን ፊትን ካበሱ በኋላ ወዲያውኑ አከታትሎ ማበስ፡፡

    ተየሙምን የሚያበላሹ ነገሮች

    1 - ውሃ መገኘት

    2 - የአየር ከሆድ መውጣትን የመሳሰለ ዉዱእ አፍራሽ ነገር መከሰት፡፡

    3 - የወሲብ ሕልምን የመሳሰለና ገላን መታጠብ ግዴታ የሚያደርግ ነገር መከሰት፡፡

    4 - በሽታና የመሳሰለ ተየሙም እንዲፈቀድ ያደረገው ችግር መወገድ፡፡

    ውሃ ያጣ ሰው
    በሳይንሳዊ መንገድ ተረጋግጧል
    የመሬት ገጽ አፈር በብናኙ ውስጥ አጥሪ (ኦክሲዳንት) የሆነ ንጥረ ነገር ይዟል፡፡ ይህ ንጥረነገር ጀርሞችን በየዓይነታቸው የማጥቃት አቅም አላቸው፡፡ ሚክሮቦችንና ቫይረሶችንም ማስወገድ ይችላል፡፡

    ጠቃሚ ነጥቦች

    1 - ውሃን መጠቀም አዳጋች በሚሆንበት ጊዜ ሶላትን በተየሙም መስገድ፣በሽንት ወይም በዓይነ ምድር እየተወጠሩ በዉዱእ ከመስገድ የተሸለ ነው፡፡

    2 - አፈር ወይም አቧራ ያለባቸው ካልሆነ በስተቀር በግድግዳ ወይም በምንጣፍ ላይ ተየሙም ማድረግ አይፈቀድም፡፡

    3 - ተየሙም ያደረገ ሰው ተየሙሙ እስካልፈረሰ ድረስ የፈለገውን ያህል ፈርድና ሱንና ሶላቶችን መስገድ ይችላል፡፡

    4 - ውዱእ ያደረገ ሰው ተየሙም ያደረገውን ሰው ተከትሎ መስገድ ይቻላል፡፡ ዐምር ብን አልዓስ ቅዝቃዜው ስለበረታ ተየሙም አድርገው ባልደረቦቻቸውን ማሰገዳቸውን ነቢዩ ﷺ ሰምተው ያጸደቁላቸው መሆኑ ተረጋግጧልና፡፡ [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]

    5 - ተየሙም አድርጎ የሰገደና የሶላቱ ጊዜ ከማብቃቱ በፊት ወሃ ያገኘ ሰው ሶላቱን እንደገና አይሰግድም፡፡ ከአቡ ሰኢድ አልኹድሪይ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹ሁለት ሰዎች በጉዞ ላይ ሆነው ውሃ ሳይኖራቸው የሶላት ጊዜ ደረሰና ንጹሑን የምድር ገጽ አስበው (ተየሙም አድርገው) ሰገዱ፡፡ ከሰገዱ በኋላ ወቅቱ ሳያልፍ ውሃ ተገኘና አንደኛቸው ዉዱእ አድርጎ ሶላቱን እንደገና ሲሰግድ ሌላኛው በድጋሜ ሳይሰግድ ቀረ፡፡ ከዚያ ወደ አላህ መልእክተኛ ﷺ መጡና የሆነውን ነገሯቸው፡፡እሳቸውም ﷺ ሶላቱን በድጋሜ ላልሰገደው ‹ትክክለኛውን ሱንና ተከትለሃል› ሲሉት፣ ዉዱእ አድርጎ እንደገና ለሰገደው ደግሞ ‹ሁለት ጊዜ አጅር ታገኛለህ› አሉት፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]

    6 - ተየሙም አድርጎ ከመስገዱ በፊት ወይም ሶላት ውስጥ እያለ ውሃ ያገኘ ሰው ውሃውን መጠቀም ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና፡- ‹‹ንጹሕ የመሬት ገጽ ለአስር ዓመታት እንኳ ውሃ ሳያገኝ ቢቀር፣የሙስሊሙ ንጽሕና መስጫ ነው፤ካገኘ ግን ቆዳውን ያስነካው (ውሃ መጠቀሙ) መልካም ነውና፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    7 - ውሃ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ሶላትን ወደ ወቅቱ መጨረሻ ማዘግየት ይፈቀዳል፡፡ እንደማያገኝ ተስፋ ከቆረጠ ግን በወቅቱ መጀመሪያ ላይ አስቀድሞ መስገድ የተወደደ ነው፤በላጩ ሶላት በወቅቱ የተሰገደ ሶላት ነውና፡፡

    8 - አንድ ሰው የሶላቱ ወቅት ያልፋል ብሎ ከሰጋ፣ውሃ መጠቀም ከቻለ ተየሙም ማድረግ አይጠቅመውም፤የሶላቱ ወቅት ቢያልፍ እንኳ ዉዱእ ማድረግ ግዴታ ይሆንበታል፡፡

    9 - ሙስሊሙን ከሶላት የሚያስተጓግለው ምንም ነገር አይኖርም፤ውሃ ቢያጣ ወይም መጠቀሙ አዳጋች ሲሆንበት ተየሙም ያደርጋል፡፡ ተየሙም ቢያጣም ያለ ጦሃራ ወቅቱን ይሰግዳል፤እንደገና የመስገድ ግዴታ አይኖርበትም፡፡ ይህም ‹‹ፋቅዱ አጥ’ጠሁረይን›› (ውሃም ሆነ አፈር ያጣ) በመባል ይታወቃል፡፡ አላህ U ፡-‹‹አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት፤›› [አል-ተጋቡን፡16]



Tags: