ሶላት ትክክለኛ እንዲሆን መሟላት ያለባቸው ቅድመ ግዴታዎች (ሹሩጥ)

19629

    አንደኛ - የወቅቱ መድረስ

    የግዴታ ሶላቶችን ያለ ሸሪዓዊ ምክንያት አስቀድሞም ሆነ አዘግይቶ መስገድ ትክክለኛ የማይሆኑባቸው የተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ አላቸው፡፡ አላህ  አንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሶላት በምእመናን ላይ በጊዜ የተወሰነ ግዴታ ነው፡፡›› [አል-ኒሳእ፡103 ]

    ይህም በተለዩ ወቅቶች ተወስኖ ተደነገገ ጥብቅ ግዴታ ነው ማለት ነው፡፡

    ከአቡ ሙሳ አል ዐሽሪ በተላለፈው መሰረት ፡- ‹‹ስለ ሶላት ወቅቶች የሚጠይቅ ሰው ወደ ነቢዩ ﷺ መጥቶ (በቃላት ገለጻ) ምንም ምላሽ ሳይሰጡት ቀሩና ለፈጅር ሶላት ሰው ሰዎች አንዱ ሌላውን መለየት በሚቸገሩበት ጊዜ ገና ጎሕ ሲቀድ እቃማ አደረግሁ፡ ከዚያም ለዙህር ሶላት ጸሐይ ዘንበል ባለችበት ጊዜ እሳቸው ከነሱ ይበልጥ የሚያውቁ ሲሆን ተመልካች ግን ገና ቀትር ነው በሚልበት ወቅት ላይ እቃማ እንዳደርግ አዘውኝ ፈጸምኩ፡፡ ከዚያም ጸሐይ ከፍ ብላ እያለች አዘዟቸውና ለዐስር እቃማ አደረጉ፡፡ ከዚያም ጸሐይ እንደ ጠለቀች አዘዟቸውና ለመግሪብ እቃማ አደረጉ፡፡ ከዚያም ቀይ ወጋገን ከአድማሱ ሲጠፋ አዘዟቸውና ለዕሻእ ሶላት እቃማ አደረጉ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ፈጅር ሶላትን ተመልካች ጸሐይ ወጥታለች ወይም ለመውጣት ተቃርባለች እስኪል ድረስ አዘገዩ፡፡ ከዚያም ዙህርን ከትናንቱ የዐስር ሶላት ጋር ተቀራራቢ እስኪሆን ድረስ አዘገዩ፡፡ ተመልካች ጸሐይቱ ቀልታለች እሰኪል ድረስ ዐስርን አዘገዩ፡ ከዚያም ቀዩ ወጋገን ከአድማሱ ወረድ እስኪል ድረስ መግሪብን አዘገዩ፡፡ ከዚም የዕሻእ ሶላትን እስከ ሌሊቱ የመጀመሪያ ሲሶ ድረስ አቆዩ፡፡ ሲነጋ ጠያቂውን ጠሩትና ‹‹ወቅቱ በነዚህ በሁለቱ ጊዜያት መካከል ነው›› አሉት ብለዋል፡፡ በሌላ ዘገባ ‹‹በሁለተኛው ቀን ቀዩ ወጋገን ከመጥፋቱ በፊት ሰገዱ›› የሚል ተመልክቷል፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    የሶላት ወቅቶች፡-

    1 - የፈጅር ሶላት ወቅት

    እውነተኛው ጎሕ (በምሥራቅ በኩል አድማሱ ላይ የሚታይ ንጣት) ከታየበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ጸሐይ መውጣት ድረስ ያለው ነው፡፡

    2 - የዙህር ሶላት ወቅት

    ጸሐይ በዓይን ግምት ከመሀል ሰማይ አለፍ ካለችበት ጊዜ ጀምሮ የማንኛውም ነገር ጥላ ከራሱ ጋር እኩል እስከ ሆነበት ጊዜ ድረስ ነው፡፡ ይኸውም ጸሐይ ጧት ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ የነገሮች ጥላ በምዕራብ በኩል ይሆናል፤ከዚያም ጸሐይ ከፍ እያለች በመጣች ቁጥር ጥላው እየቀነሰ በመሄድ ጸሐይ አናት ላይ ስትሆን ጥላው ይጠፋል፤ከዚያም መጨመር ይጀምራል፡፡ ይህ ጭማሪ ሲጀምር ነው የዘዋል (የጸሐይ ከመሀል ሰማይ ወደ ምዕራብ አለፍ ማለት) ጊዜ፡፡

    3 - የዐስር ሶላት ወቅት

    የዙህር ወቅት ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ የማንኛውም ነገር ጥላ የራሱ መጠን እጥፍ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ነው፡፡

    4 - የመግሪብ ሶላት ወቅት

    ጸሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ ቀዩ ወጋገን (ሸፈቁል አሕመር) ከአድማሱ እስከ ጠፋበት ድረስ ነው፡፡ ሸፈቁል አሕመር ጸሐይ ስትጠልቅ አድማስ ላይ የሚታየው ቀይ ብርሃን ነው፡፡

    5 - የዕሻእ ሶላት ወቅት

    የመግሪብ ሶላት ካበቃበት ጊዜ አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት ያለው ጊዜ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹የዕሻእ ሶላት ወቅት እስከ መካከለኛው እኩለ ሌሊት ድረስ ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    አሁን ባለንበት ዘመን የሶላት ወቅቶችን በዘመን መቁጠሪያዎች አማካይነት በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡

    የፈጅር ሶላት
    የዙህር ሶላት
    የዐስር ሶላት
    የመግሪብ ሶላት
    የዕሻእ ሶላት
    ተገቢ አይደለም

    - ሀፍረተ ገላን ቀርጾ በሚያሳይ ጠባብ ወይም ስስና ዘርዛራ ልብስ መስገድ፣ሀፍረተ ገላ ተገልጦ ወይም ከቁርጭምጭሚት አልፎ በረዘመ ልብስ መስገድ፡፡

    - ሥዕል ባለበት ልብስ ወይም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሥዕሎች ባሉባቸው ቦታዎች፣ወይም ሥዕሎችና ቅርጾች ባለበት መስገጃ ምንጣፍ መስገድ፡፡

    - መቃብሮች ባሉባቸው መስጊዶች መስገድ፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ንቁ አስተውሉ! ከናንተ በፊት የነበሩ ሕዝቦች የነቢዮቻቸውንና የጻድቆቻቸውን መቃብሮች መስጊዶች አድርገው ይይዙ ነበር፤ንቁ አስተውሉ! መቃብሮችን መስጊዶች አድርጋችሁ አትያዙ፤ይህን ጭራሽ እንዳታደርጉ እኔ ከልክያችኋለሁ፡፡››› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    ጠቃሚ ነጥቦች

    1 - ወቅቱ ከማብቃቱ በፊት አንድ ረክዓ ደርሶ የሰገደ ሰው ሶላቱን ደርሶበት ሰግዷል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ከአንድ ሶላት አንድ ረክዓ ደርሶ የሰገደ ሰው በሶላቱ ደርሶበታል ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    2 - አንድ ሶላት በእንቅልፍ ምክንያት ወይም ተዘንግቶ ቢያልፍ ወዲያውኑ ሶላቱን መፈጸም ግዴታ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹አንድን ሶላት ረስቶ ያልሰገደ ሰው እንዳስታወሰ ወዲያውኑ ይስገደው፣ከዚህ በስተቀር ሌላ ማካካሻ የለውም፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    ሁለተኛ - ከሐደሥ መጽዳት

    1 - ከመለስተኛው ሐደሥ መጽዳት

    ይህ ዉዱእ በማድረግ ይፈጸማል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹አንዳችሁ ዉዱኡን ካፈረሰ እንደገና ዉዱእ ካላደረገ በስተቀር አላህ ሶላቱን አይቀበልም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - ከከፍተኛው ሐደሥ መጽዳት

    ይህ ገላን በመታጠብ ይፈጸማል፡፡ አላህ  እንዲህ ብሏልና፡- ‹‹የረከሳችሁም ብትኾኑ (ገላን የመታጠብ ግዴታ ካለባችሁ ገላችሁን) ታጠቡ፡፡›› [አል-ማኢዳህ፡6]

    በመስገድ ላይ እያለ ሐደሥ እንዳለበት ያስታወሰ፣ወይም እየሰገደ የሐደሥ ክስተት ያጋጠመው ሰው ሶላቱ ተበላሽቷልና ያለ ሰላምታ አቋርጦ ለጦሃራ መውጣት ይኖርበታል፡ ሰላምታ የሶላት መቋጫ በመሆኑና ሶላቱ ተቋረጠ እንጂ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ነው፡፡

    ሦስተኛ - የልብስ የገላና የቦታ ንጽሕና

    1 - የልብስ ንጽሕና

    አላህ  እንዲህ ብሏል ፡‹‹ልብስህንም አጥራ፡፡››[አል-ሙደሢር፡4]

    የልብስ ንጽሕና

    2 - የገላ ንጽሕና

    የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሁለት መቃብሮች አጠገብ ሲያልፉ ፡- ‹‹እየተሰቃዩ ነው፤የሚሰቃዩትም በትልቅ ነገር (ጥፋት) ምክንያት ሳይሆን ይኸኛው ራሱን ከሽንት አይጠብቅም፣አይጠነቀቅም ኖሯል፡፡›› [በአቡዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - የቦታ ንጽሕና

    መስጊድ ውስጥ የሸናውን ገጠሬ ዐረብ አስመልክተው ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ተውት (ሰውየውን አትንኩት)፤ በሸናበት ቦታ ላይ ባልዲ ሙሉ ወይም በትልቅ ባልዲ ድፉበት፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የመሰገጃ ቦታ ንጽሕና

    ሶላትና ነጃሳ

    ነጃሳ ያለበት ሆኖ ሳያውቅ ወይም ረስቶ የሰገደ ሰው ሶላቱ ትክክለኛ ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ እየሰገዱ ጫማቸውን አወለቁና ሰዎቹም ጫሞቻቸውን አወለቁ፡፡ ካበቁ በኋላ ነቢዩ ﷺ ‹‹ጫሞቻችሁን ለምን አወለቃችሁ?›› አሏቸው፣የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እርስዎ ሲያወልቁ አይተን አወለቅን አሉ፤ነቢዩም ﷺ ፡- ጅብሪል መጥቶ ቆሻሻ እንዳለባቸው ነግሮኝ ነው፤ አንዳችሁ ወደ መስጊድ ሲመጣ ጫሞቹን ገልብጦ ይያቸው፤ቆሻሻ ካየባቸው መሬት ላይ ይጥረገውና ይስገድባቸው፡፡›› [በአቡዳዉድ የተዘገበ] አሉ፡፡

    `በመስገድ ላይ እያለ ነጃሳ እንዳለበት ያወቀ ሰው ማስወገድ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ በላይኛው ሐዲስ መሰረት በሰገደው ላይ ተሞርክዞ ሶላቱን ይቀጥልበታል፡፡ ነጃሳውን ማስወገድ ካልቻለ ግን ሶላቱ ይበላሻል፡፡

    ምድሩ በሞላ መስጊድ ነው

    ምድሩ በሞላ ሊሰገድበት የሚችል መስጊድ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ምድሪቱ በሞላ መስገጃና ንጽሕና መስጫ ተደርጋልኛለችና ሶላት የደረሰበት ማንኛውም ሰው በደረሰበት ቦታ ይስገድ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    እንዳይሰገድባቸው እገዳ የተላለፈባቸው በመቃብር [የጀናዛ ሶላት በዚህ ውስጥ አይካተትም] ቦታና በገላ መታጠቢያ መስገድን የመሳሰሉ ከዚህ ውስጥ አይካተቱም፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹መካነ መቃብርና ገላ መታጠቢያ ሲቀሩ መሬቱ ሁሉ መስጊድ ነው፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    ብለዋልና፡፡ የግመሎች ማደሪያም የተከለከለ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹በግመሎች ማደሪያ (አዕጣን) ቦታ አትስገዱ፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡ አዕጣን የግመል ማደሪያና መጠለያ ነው፡፡

    በመታጠቢያ ቤት መስገድ
    በመቃብር ቦታ መስገድ

    አራተኛ - ሐፍረተ ገላን (ዐውረት) መሸፈን

    የወንድ ሐፍረተ ገላ (ዐውራህ)፡- ከእምብርት እስከ ጉልበት ያለው የአካል ክፍል ነው፡፡

    የሴት ሐፍረተ ገላ (ዐውራህ)፡- ፊቷና መዳፎቿ ብቻ ሲቀሩ ሙሉ አካላቷ ነው፡፡

     
     


    ሁለቱን ትከሻዎች መሸፈን…..

     

    ሰጋጁ በሁለት ክንዶቹና በአንገቱ መካከል ያለውን የሚሸፍን ነገር መልበስ ይኖርበታል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹በሁለቱ ትከሻዎቹ ላይ ምንም ሳይኖር አንዳችሁ በአንድ ልብስ አይስገድ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    አምስተኛ - ፊትን ወደ ቅብላ ማዞር

    ቅብላ የተከበረው ከዕባ ነው፡፡ አላህ  እንዲህ ብሏልና፡- ‹‹ፊትህን ወደ ተከበረው መስጊድ (ወደ ከዕባ) አግጣጫ አዙር፤የትም ስፍራ ብትኾኑም (ስትሰግዱ) ፊቶቻችሁን ወደርሱ አግጣጫ አዙሩ፤›› [አል-በቀራህ፡144]

    እዚህ ላይ አንዳንድ ነጥቦች ትኩረት ይሻሉ፡-

    1 - መስጅድ አልሐራም ውስጥ የሚሰግድ ሰው ፊቱን በቀጥታ ወደ ከዕባ ማዞር ይኖርበታል፡ ከከዕባ ራቅ ብሎ የሚሰግድ ሰው ግን ፊቱን የሚያዞረው ወደ አቅጣጫው ነው፣በቀጥታ ወደ ከዕባ ፊቱን ማዞር ሊያዳግተው ይችላልና፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹በምሥራቅና ምዕራብ መካከል ያለው ሁሉ ቅብላ ነው፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ያሉት፡፡

    2 - የሱንና ሶላት በእንስሳት ጀርባ ላይ ፡- ሰጋጁ በተቻለው መጠን በሶላቱ መጀመሪያ ላይ ፊቱን ወደ ቅብላ ለማዞር ጥረት ያደርጋል፤ያን ማድረግ ከተሳነው እንስሳው ወደሚሄድበት አግጣጫ ይሰግዳል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ወደ የትኛውም አግጣጫ ከማምራታቸው በፊት ግመላቸው ላይ ሆነው ነፍል ይሰግዱ ነበር፤እዚያው ላይ ሆነውም ውትር ይሰግዳሉ፤ የግዴታ ሶላት ግን በእንስሳ ጀርባ ተቀምጠው አይሰግዱም፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]

    ቅብላን ያላወቀ ሰው ምን ያደርጋል?

    የቅብላን አቅጣጫ ያላወቀ ሰው ቤት ውስጥ ከሆነ ወይም በአቅራቢያው ሰዎች ካሉ ይጠይቃል፡ ወይም በመስጊዶች ምሕራብ፣በኮምፓስ፣በጸሐይ፣በጨረቃና በመሳሰሉት አማካይነት ለማወቅ ጥረት ያደርጋል፡፡ ካቃተው ይሆናል ብሎ ይበልጥ ወደሚገምተው አግጣጫ ይሰግዳል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት፤›› [አል-ተጋቡን፡16]

    መካ ሐረም ውስጥ የሚሰግድ ሰው
    ከከዕባ ርቆ የሚሰግድ ሰው