ሶላቱል ጀናዛ

7626

    የአስክሬን አዘገጃጀት

    የመሞት አዝማሚያ በተስተዋለበት ታማሚ ዘንድ ተገኝቶ ‹‹ላእላሀ እል’ለል’ሏሁ›› ማለትን ማስታወስ የተወደደ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ለሞት የተቃረቡ (የሚያጣጥሩ) ሰዎቻችሁን ‹ላእላሀ እል’ለል’ሏሁ› እንዲሉ አድርጓቸው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    ሲሞት ዓይኖቹ እንዲከደኑ ይደረግና ሬሳው ይሸፈናል፡፡ የአስከሬን አዘገጃጀቱ፣ሶላቱና የቀብር ሥርዓቱም ቶሎ መከናወን ይኖርበታል፡፡

    ሬሳን ማጠብ ማሰናዳትና መቅበርን የሚመለከት ብያኔ

    ሬሳን ማጠብ፣መገነዝ፣መሸከም፣የጀናዛ ሶላት መስገድና መቅበር የወል ግዴታ (ፈርድ አልክፋያ) ነው፡፡ ከፊሉ ከፈጸመው ኃላፊነቱ ከተቀሩት ላይ ይነሳል፡፡

    ሬሳ ማጠብን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች

    1 - ሬሳን ለማጠብ እምነት የሚጣልበት ታማኝና የአስተታጠቡን ሕጎች የሚያውቅ ሰው መምረጥ ተገቢ ይሆናል፡፡

    2 - በማጠቡ ቅድሚያ የሚሰጠው ሟች እንዲያጥበው የተናዘዘለት ሰው ሲሆን፣በመቀጠል የአስተታጠቡን ሕጎች የሚያውቅ ከሆነ በዝምድና ይበልጥ የሚቀርበው በቅደም ተከተል ይሆናል፡፡ ህጎቹን የማያውቅ ከሆነ ግን ለሚያውቀው ዘመድ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

    3 - ወንድ የወንዶችን ሬሳ ሲያጥብ ሴት የሴቶችን ሬሳ ታጥባለች፡፡ ባልና ሚስት አንዱ የሌላውን ሬሳ ማጠብ ይችላሉ፡፡ ነቢዩﷺ ለዓእሻ (ረዐ) ‹‹ከኔ በፊት ብትሞቺና እኔ አጥቤሽ፣ገንዜሽ፣ባንቺ ላይ ሰግጄ ብቀብርሽ ምንም የሚጎዳ ነገር የለበትም፡፡›› [በእብን ማጀህ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከሰባት ዓመት በታች የሆኑትን ማጠብ ይችላሉ፡፡ እንደ ወላጅ አባት ያለ ዘመድ ቢሆን እንኳ፣አንድ ሙስሊም ወንድ ወይም ሴት የካፍርን ሬሳ ማጠብ፣አስከሬኑን መሸከም፣መገነዝና ጀናዛ መስገድ አይፈቀድም፡፡

    4 - በውጊያ ላይ የተሰዋ ሸሂድ ሬሳ አይታጠብም፣አይገነዝም፤አይሰገድበትም፤በለበሰው ልብሱ ይቀበራል፡፡

    5 - የተጨናገፈ ጽንስ ወንድም ይሁን ሴት አራት ወር የሞላው ከሆነ፣ከአራት ወራት በኋላ ሰው ስለሚሆን ይታጠባል፣ይገነዛል፣ተሰግዶበትም ይቀበራል፡፡

    6 - ሬሳው የሚታጠብበት ውሃ ጣህር የተፈቀደ መሆን ሲገባው፣በተሸፈነ ቦታ መታጠብ ይኖርበታል፡፡ ሟቹን ከማጠብ ጋር ግንኙነት የሌለው ሰው በቦታው መገኘት የለበትም፡፡

    የሬሳ አስተጣጠብ

    1 - ሬሳው በሚታጠብበት አልጋ ላይ ተደርጎ ሀፍረተ ገላው ይሸፈንና በተለየ ክፍል ወይም ገለል ባለ ቦታ ከእይታ ርቆ ልብሶቹ ይወልቃሉ፡፡

    2 - አጣቢው በሚያጥብበት ጊዜ እጁን በጨርቅ (ጓንት) መሸፈን የተወደደ ነው፡፡

    3 - አጣቢው የሬሳውን ራስ እስከ መቀመጥ አቅራቢያ ቀና አድርጎ እጁን በሆዱ ላይ በማስኬድ ጨመቅ ያደርጋል፡፡ ከዚያም የፊትና የኋላ መውጫ መንገዶችን በማጽዳት ያለባቸውን ነጃሳ ያጥባል፡፡

    4 - ለማጠብ ንይያ አድርጎ ብስምል’ላህ ይላል፡፡

    5 - አጣቢው ለሟቹ ከመድመዷና እስትንሻቅ በስተቀር የሶላት ዓይነት ውዱእ ያደርጋል፡፡ ለመድመዷና እስትንሻቅ አፍና አፍንጫው ላይ ማበስ ብቻ በቂ ነው፡፡

    6 - የሬሳውን ራስና ጺሙን በቁርቁራ ቅጠል ውሃ ወይም በሳሙናና በመሳሰሉት ያጥባል፡፡

    7 - መጀመሪያ የቀኙን ጎን በመቀጠል የግራውን ክፍል አጥቦ ከዚያ ቀሪውን የአካል ክፍልን አዳርሶ ያጥባል፡፡

    8 - በመጨረሻው ትጥበት ላይ ካፉር ማድረግ የተወደደ ነው፡፡

    9 - ከእጥበቱ በኋላ ገላው እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡

    10 - የሴት ጸጉር ይጎነጎንና ከበስተኋላዋ ይደረጋል፡፡

    አጣቢው የሬሳውን ራስ ቀና ያደርጋል
    አጣቢው እጁን በጨርቅ ይጠቀልላል
    ሬሳው በማጠቢያ አልጋው ላይ ይደረጋል
    አጣቢው ሬሳው ሆድ ላይ በእጁ ጫን ብሎ ጨመቅ ያደርጋል
    አጣቢው የሶላት ዓይነት ዉዱእ ለሬሳው ያደርጋል
    የሬሳውን ራስና ጺሙን በውሃና በቁርቁራ ያጥባል
    የቀኙን ከዚያም የግራውን ክፍል ያጥባል
    ከትጥበቱ በኋላ ሬሳውን ያደራርቃል

    ማሳሰቢያዎች

    - ንጽሕናውን ማሟላት ከተቻለ ግዴታው አንድ ጊዜ ብቻ ማጠብ ሲሆን፣ቢጸዳም ሦስት ጊዜ ማጠቡ የተወደደ ነው፡፡

    - ውሃ በመጥፋቱ ምክንያት፣ወይም በቃጠሎና በመሳሰለው ምክንያት አካላቱ የተቆራረጡ ሆነው ሬሳውን ማጠብ አስቸጋሪ ከሆነ ተየሙም ይደረግለታል፡፡

    - ሬሳ ያጠበ ሰው ከትጥበቱ በኋላ ራሱ ገላውን መታጠብ የተወደደ ነው፡፡

    ሬሳን መገነዝ

    1 - ሱንናው ወንድን ከጥጥ በተሰሩ፣የቆዳ ቀለም በማያሳዩ፣ስስ ባልሆኑና ገላውን ሙሉ በሙሉ በሚሸፍኑ ሦስት ነጫጭ ጨርቆች መገነዝ ነው፡ ከፈኑ ውድ መሆን የለበትም፡፡ ሴት ደግሞ ከጥጥ በተሰሩ አምስት ጨርቆች ማለትም በሽርጥ (እዛር)፣በራስ መሸፈኛ (ኽማር)፣በቀሚስና በሁለት ብትን ጨርቆች ትገነዛለች፡፡

    ወንድ ሕጻን በአንድ ጨርቅ ይገነዛል፡፡ በሦስት ማድረግም ይፈቀዳል፡፡ ሴት ሕጻን በአንድ ቀሚስና በሁለት ብትን ጨርቆች ትገነዛለች፡፡

    2 - ሦስቱ ብትን መጠቅለያ ጨርቆች ቀርበው ይታጠናሉ፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሟቹን ስታጥኑት በውትር (ኢተጋማሽ ቁጥር) ይሁን፡›› [በእብን ሕባን የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    3 - ብትን ጨርቆቹ አንዱ በሌላው ላይ ሲደረግ በመካከላቸው እንደ ዐንበር፣ካፉር፣ምስክና የመሳሰሉ ሽቶዎች ቅይጥ ይደረጋል፡፡ ሟች በሐጅ ወይም በዑምራ እሕራም ላይ የነበረ ከሆነ ሽቶው አይደረግበትም፣ልብሱም አይታጠንም፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ሽቶ አታስነኩት፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    4 - ሬሳው በጀርባው በነዚህ ጨርቆች ላይ ይደረግና የላይኛው ጫፉ ከግራ በኩል በቀኙ ጎን ላይ ይጠቀለላል፡፡ ከዚያም የቀኝ ጠርዙ በግራው ላይ ይመለሳል፡፡ ከዚያም ሁለተኛውና ሦስተኛው ጨርቅ ይጠቀለልበታል፡፡ የተረፈው ከራሱ በኩል ይሰበሰብና እንዳይበተን በማሰሪያ ይታሰራል፤እስሩ ሲቀበር ይፈታል፡፡

    5 - ዋጅቡ ገላውን ሙሉ በሙሉ መሸፈን ሲሆን፣የተገኘው ገላውን የማይሸፍን ልብስ ብቻ ከሆነ ራሱ ይሸፈንበትና ሁለት እግሮቹ ላይ ትንሽ እዝኽር (ጥሩ ሽታ ያለው ተክል ነው) ይደረጋል፡ የሙስዐብ ብን ዑመይርን (ረዐ) አገናነዝ አስመለክተው ኸባብ (ረዐ) ባስተላለፉት ሐዲስ ‹‹(የሙስዐብን ሬሳ) ራሱን ሸፍነን ሁለት እግሮቹ ላይ ከእዝኽር ትንሽ እንድናደርግ ነቢዩ ﷺ አዘውናል፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    6 - በእሕራም ላይ እያለ የሞተ ሰው በእሕራም ልብሱ እንዳለ ይገነዛል፡፡ የወንድ ሙሕሪም ራስ አይሸፈንም፡ ነቢዩﷺ ‹‹በውሃና በቁርቁራ ቅጠል እጠቡት፤በሁለት ልብሶችም ገንዙት፤በሽቶ አታጥኑት፣ራሱንም አትሸፍኑ፣በቅያማ ቀን ተልቢያ (ለብ’በይከ አልሏሁም’መ ለብ’በይከ) እያለ ይቀሰቀሳልና፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በመገነዣ ጨርቁ ላይ ሽቶ ማድረግ
    ሬሳውን በጀርባው ማስተኛት
    ገላንውን ሙሉ በሙሉ መሸፈን

    የጀናዛ ሶላት

    የሶላቱል ጀናዛ ማእዘናት

    1 - ቅያም - ለሚችል ሰው መቆም፡፡

    2 - አራቱ ተክቢራዎች፡፡

    3 - ፋቲሓን መቅራት፡፡

    4 - በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት ማውረድ፡፡

    5 - ለሟቹ ዱዓእ ማድረግ፡፡

    6 - ቅደም ተከተሉን መጠበቅ፡፡

    7 - ተስሊም (ሰላምታ)፡፡

    የሶላቱል ጀናዛ ሱንናዎች

    1 - ከቅራኣ በፊት እስትዓዛ ማለት፡፡

    2 - ለራሱና ለሙስሊሞች ዱዓእ ማድረግ፡፡

    3 - ድምጽ ሳያሰሙ መቅራት፡፡

    4 - የሶላቱን ሶፍ ሦስት ረድፍ እንዲሆን ማብዛት፡፡

    የሶላቱል ጀናዛ አሰጋገድ

    ሟች ወንድ ከሆነ ኢማሙ በአስከሬኑ ራስ አቅጣጫ፣ሴት ከሆነች ደግሞ በአስከሬኑ መሀል አቅጣጫ ይቆማል፡፡ ተከትለው የሚሰግዱት እንደ ሌላው ሶላት ከኢማሙ ጀርባ ይቆማሉ፡፡ ኢማሙ አራት ተክቢራዎች በሚከተለው ዝርዝር መሰረት ያደርጋል፡-

    1 - የእሕራም ተክቢራ አድርጎ እስትዓዛና በስመላ ካለ በኋላ ፋቲሓን ይቀራል፡፡ የእስትፍታሕ ዱዓእ ግን አይደረግም፡፡

    2 - ሁለተኛውን ተክቢራ አድርጎ በመደበኛው ሶላት የመጨረሻው ተሸሁድ የሚደረገውን ዓይነት ሶላት በነቢዩ ﷺ ላይ ያወርዳል፡፡

    3 - ሦስተኛውን ተክቢራ ካለ በኋላ ለሟቹ ለራሱና ለሙስሊሞች ዱዓእ ያደርጋል፡፡ ከዱዓእ ዓይነቶች የሚከተለውን እናገኛለን፡-

    ‹‹አልሏሁም’መ እግፍርለሁ ወርሐምሁ፣ወዓፍህ ወዕፉ ዐንሁ፣ወአክሪም ኑዙለሁ፤ወወስ’ሲዕ ሙድኸለሁ፤ወግሲልሁ ብልማእ ወሥ’ሠልጅ ወልበረድ፤ወነቅ’ቂህ ምነልኸጣያ ከማ ነቅ’ቀይተ አሥ’ሠውበል አብየደ ምነድ’ደነስ፤ወአብድልሁ ዳረን ኸይረን ምን ዳሪሂ፣ወአህለን ኸይረን ምን አህሊሂ፤ወዘውጀን ኸይረን ምን ዘውጅህ፤ወአድኽልሁ አልጀን’ነተ ወአዕዝሁ ምን ዐዛበል ቀብር ወምን ዐዛብ አን’ናር፡፡››

    ትርጉሙ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ምሕረት አድርግለት፤እዘንለትም፡፡ ከቅጣትም አድነው፤ይቅር በለውም፡፡ መስተንግዶውንም አሳምርለት፤ማረፊያውንም አስፋለት፡፡ ከኃጢአቱ በውኃ በበረዶና በአመዳይ (በረድ) እጠበው፡፡ ነጭ ልብስ ከቆሻሻ እንደሚጠራ ሁሉ ከኃጢአቱ አጥራው፡፡ ከመኖሪያው የተሸለ መኖሪያ፣ከቤተሰቡ የተሻለ ቤተሰብ፣ከሚስቱ የተሸለች ሚስት ቀይርለት፡፡ ወደ ጀነትም አስገባው፤ከመቃብር ውስጥ ስቃይና (ወይም) ከእሳት ቅጣትም ጠብቀው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    ሟች ሴት ከሆነች ዱዓኡ ተውላጠ ስሙ በሴቴ ጾታ ይለወጣል፡፡ ሟች ሕጻን ወይም ጭንጋፍ ከሆነ ‹‹አልሏሁም’መ እጅዐልሁ ዙኽረን ልዋሊደይህ፣ወፈረጠን፣ወአጅረን፣ወሸፊዐን ሙጃበን››

    ‹‹አልሏሁም’መ ሰቅ’ቅል ብሂ መዋዚነሁማ፣ወአዕዝም ብሂ ኡጁረሁማ፣ወአልሕቅሁ ብሷሊሕ ሰለፍልሙእምኒን፣ወጅዐልሁ ፊከፋለት ኢብራሂመ፣ ወቅህብረሕመትከ ዐዛበል ጀሒም፡፡›› ይላል፡፡ ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ለወላጆቹ አለኝታ፣(ወደ ጀነት) ቀድሞ የሚጠብቃቸው አጅር፣(አላህ ዘንድ) ተቀባይነት ያለው አማላጅም አድርግላቸው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]

    አላህ ሆይ! የመልካም ሥራዎቻቸው ሚዛን ማክበጃም አድርገው፡፡ ምንዳቸውን በርሱ ትልቅ አድርግላቸው ፡፡ ከደጋግ አበው ሙእሚኖች ተርታም አሰልፈው፤በችሮታህም ከገሀነም ሥቃይ ጠብቀው፡፡›› ማለት ነው፡፡

    4 - ከዚያም አራተኛውን ተክቢራ አድርጎ ትንሽ ዝም ይልና ወደ ቀኝ ብቻ ሰላምታ ያደርጋል፣ወይም ሁለት ሰላምታ ያደርጋል፡፡

    አስከሬን መሸከም መሸኘትና መቅበር

    ሶላቱ ካበቃ በኋላ ግብአተ መሬቱን ቶሎ መፈጸም ሱንና ነው፡፡ አስከሬኑን የሚሸኝ ሰው በመሸከሙ ላይ መካፈል የተወደደ ነው፡፡ አስከሬኑን መቃብሩ ውስጥ የሚያስገባው ሰው ‹‹ብስምል’ላህ ወዐላ ምል’ለት ረሱሊል’ላህ›› (በአላህ ስም፣በአላህ መልእክተኛ መንገድ) [በትርምዚ የተዘገበ] ማለት ሱንና ነው፡፡

    አስከሬኑ በቀኝ ጎኑ ፊቱ ወደ ቅብላ ተድርጎ ለሕድ [ለሕድ ወደ ታች ከተቆፈረ በኋላ በቅብላ በኩል ለአስከሬኑ ማስገቢያ ወደ ጎን የሚቆፍር ጉድጓድ ነው፡፡] ውስጥ ያርፋል፤ከዚያ የከፈኑ ማሰሪያ ይፈታና የለሕዱ ክፍተት በጭቃ ይመረጋል፡፡

    አስከሬን በመሸከም ላይ መሳተፍ
    ለሕድ
    በሁለት መዳፎቹ አፈር ሞልቶ ቀብሩ ላይ ይጨምራል
    የቀብር ምልክት

    ሐዘንተኛን ማጽናናት (ተዕዝያ)

    ስሜታቸውን ለመጠበቅ፣የደረሰባቸውን ሀዘን ለማቃለልና እንዲጽናኑ ለማበረታታት ሲባል የሟች ቤተሰቦችን ማስተዛዘን የተወደደ ነው፡፡

    ሀዘንተኛውን ‹‹ሊል’ላሂ ማአኸዘ፣ወለሁ ማአዕጣ፣ወኩል’ሉ ሸይእን ዕንደሁ ብአጀ’ልን ሙሰም’ማ፤ፈልተስብር ወልተሕተስብ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ‹‹አዕዘመል’ሏሁ አጅረከ፣ወአሕሰነ ዐዛአከ፣ወገፈረ ሊመይትከ›› ማለትን በመሳሰሉ የማጽናናት መልእክቱን በሚያስተላልፉ ቃላት ማጽናናት ይቻላል፡፡

    ትርጉሙ ፡- ‹‹የወሰደው የአላህ ነው፤የሰጠውም የርሱ ነው፡፡ በርሱ ዘንድ ሁሉም ነገር በተወሰነ ቀነ ቀጠሮ ነውና ተጽናና፣ የመጽናናት አጅርህን አላህ ዘንድ ታሳቢ አድርገው፡፡›› (አላህ የሰብርህን አጅር ያብዛው፣ሐዘንህንም ያሳምረው፣ለሟችህም ይቅር ይበል፡፡›› ማለት ነው፡፡

    የሴቶች ከጀናዛ ጋር መውጣት
    የሴቶች ጀናዛን ተከትሎ መውጣት በሸሪዓው ያልተደነገገ ጉዳይ ነው፡፡ ከኡምሙ ዐጥይያ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹ጀናዛን ተከትለን ከመሄድ ተከልክለናል፤ሆኖም አልጠበቀብንም፡፡›› [በእብን ማጀህ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    መካነ መቃብርን መጎብኘት

    ለመገሰጽና ለሙታኑ ዱዓእ ለማድረግ ዓላማ መቃብሮችን መጎብኘት ለወንዶች ሱንና ነው፡፡ ነቢዩﷺ ‹‹መቃብሮችን ከመጎብኘት ከልክያችሁ ነበር፣ኣኽራን (የወዲያኛውን ዓለም) ስለሚያስታውሷችሁ ጎብኟቸው፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    በመቃብር ጉብኝት ጊዜ ከተላለፉት ዱዓዎች መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን ፡- ‹‹አስ’ሰላሙ ዐለይኩም ዳረ ቀውምን ሙእምኒን፣ወእን’ና እንሻአል’ሏሁ ብኩም ላሕቁን፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    ወይም ‹‹አስ’ሰላሙ ዐላ አህል አድ’ዲያር ምነል ሙእምኒነ ወልሙስሊሚን፣ወየርሐሙል’ሏ አልሙስተቅድሚነ ምን’ና ወልሙስተእኸሪን፣ወእን’ና እንሻአል’ሏሁ ብኩም ላሕቁን፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    ‹‹አስአሉል’ሏሀ ለና ወለኩም አልዓፍያ›› [በሙስሊም የተዘገበ] ትርጉሙ ፡- ‹‹የምእመናን ሕዝብ (መቃብር ነዋሪዎች) መንደር ሰላም ለናንተ ይሁን፤እኛም አላህ ካለ የምንከተላችሁ ሰዎች ነን፡፡››

    ‹‹ሰላም በመንደሮቹ (መቃብሮቹ) ነዋሪ ሙእምኖችና ሙስሊሞች ላይ ይሁን፤ከመካከላችን ቀድሞ ለተጓዙትና ቆይተው ለሚከተሏቸውም አላህ ይዘንልን፤እኛም አላህ ቢሻ ወደናንተው መጪዎች ነን፡፡››

    ‹‹ለኛም ለናንተም አላህ መድህኑን ይሰጠን ዘንድ እለምነዋለሁ፡፡›› ማለት ነው፡፡ የአላህን ምሕረትና እዝነቱን በመለመን ለነሱ ዱዓእ ማድረግና የመሳሰለውም የተፈቀደ ነው፡፡

    በቀብር ስነ ሥርዓት ላይ የተከለከሉ ነገሮች

    1 - የሟቹን ዝና እየደረደሩ ሙሾ ማውረድና ማልቀስ፣ትዕግስት የለሽ መሆን፣በአላህ ፍርድና ውሳኔ ማማረርና መነጫነጭ፡፡

    ነቢዩ ﷺ ‹‹ሙሾ አውራጅ አስለቃሽ ከመሞቷ በፊት ተውበት ካላደረገች በቅያማ ቀን የቀለጠ የነሐስ ቀሚስ ለብሳ ትነሳለች፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - ልብስ መቅደድ፣ጉንጮቹን መምታት፣መቧጨርና መጮህ፣ጸጉር መንጨት ወይም መላጨት፡፡

    የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹ጉንጮችን የመታ፣ወይም ልብሶችን የቀደደ፣ወይም በዘመነ ጃህሊይ’ያ ልማድ የፎከረ ሰው ከኛ ወገን አይደለም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - በመቃብሮች ላይ መብራት ማኖር፡፡

    እብን ዐባስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ መቃብሮችን የሚጎበኙ ሴቶችን፣መስጊዶች አድርገው የሚይዙትንና መብራቶች የሚያደርጉባቸውን ረግመዋል፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    መቃብሮችን ማብራትና ቀለም መቀባት አይፈቀድም

    4 - መቃብሮች ላይ መቀመጥ፣ቀለም መቀባት ወይም ቤት መስራት፡፡

    ከጃቢር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ መቃብሮችን ቀለም መቀባት፣(በመቃብሮች) ላይ መቀመጥንና (በመቃብር ላይ) ቤት መስራትን ከልክለዋል፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    5 - በመቃብሮች መባረክ፣ጠዋፍ ማድረግና ሙታኑን መለማመን፡፡

    ይኸኛው ይጠቅሙኛል ወይም ይጎዱኛል ብሎ ከልቡ በማመን ከተደረገ በአላህ ማጋራት (ሽርክ) ነው፡፡ ከአላህ በስተቀር መጥቀምም ሆነ መጉዳት የሚችል ማንም የለምና ፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህ የሻውን በስተቀር ለራሴ ጥቅምንም ጉዳትንም አልችልም፣በል፡፡›› [አል-አዕራፍ፡188]

    በመቃብሮች ዙሪያ መዞር (ጠዋፍ) አይፈቀድም

    6 - መስጊድ ውስጥ ሰው መቅበር፣ወይም መስጊዶችን መቃብሮች ላይ መስራት፣ወይም ወደ መቃብሮች ዞሮ መስገድ፡፡

    የአላህ መልእክተኛﷺ ፡- ‹‹የነቢዮቻቸውን መቃብሮች መስጊዶች አድርገው በመያዛቸው አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን አላህ ረግሟቸዋል፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የቀብር ስነ ሥርዓትን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች በከፊል

    1 - የጀናዛ ሶላት ያመለጠው ሰው አስከሬኑ ከመቀበሩ በፊት ወይም በኋላ በመቃብሩ ቦታ ይሰግድበታል፡፡ መስጊድ ታጸዳ የነበረችውን ሴት ነቢዩ ﷺ መቃብሯ ላይ መስገዳቸው ተረጋገጧልና፡፡ [በቡኻሪ የተዘገበ]

    2 - በደረሰባቸው ሀዘን ምክንያት ምግብ ከማዘጋጀት የሚጠመዱ በመሆናቸው ለሟች ቤተሰቦች ምግብ ማዘጋጀት የተወደደ ነው፡፡ የጀዕፈር ቤተሰቦች ሰው ሞቶባቸው ነቢዩ ﷺ :- ‹‹ለጀዕፈር ቤተሰቦች ምግብ አዘጋጁላቸው የሚጠመዱበት ጉዳይ መጥቶባቸዋልና፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ለሟች ቤተሰቦች ምግብ ማዘጋጀት

    3 - ያለ ቁጭት፣ድምጽ ከፍ ሳያደርጉና ሙሾ ሳያወርዱ ለሞተ ሰው ማልቀስ የተፈቀደ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ልጃቸው ኢብራሂም ሲሞት ፡- ‹‹ዐይን ያለቅሳል፣ልብም በእርግጥ ያዝናል፤ኢብራሂም ሆይ! እኛ ባንተ መለየት በእርግጥ ሀዘንተኞች ነን፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    4 - በውጊያ ላይ የተሰዋ ሸሂድ በተሰዋበት ልብሱ ሳይታጠብና ሳይሰገድበት ይቀበራል፡፡ ነቢዩ ﷺ የኡሑድ ዘመቻ ሰማእታትን ሳይታጠቡ ከነደማቸው እንዲቀበሩ ማዘዛቸው ተረጋግጧል፡፡ [በቡኻሪ የተዘገበ]

    ሸሂድ በለበሰው ልብስ ይቀበራል

    5 - በሐጅ ወይም በዑምራ እሕራም ላይ እያለ የሞተ ሰው ይታጠባል፣ግን በተቀየጠ ሽቶ አይታጠንም፤ራሱም አይሸፈንም፤ይሰገድበታል፡፡ ነቢዩﷺ በሐጅ ላይ የሞተውን ሰውዬ ‹‹በውሃና በቁርቁራ ቅጠል እጠቡት፣በሁለት ልብሶችም ገንዙት፤ራሱን ግን አትሸፍኑ፤በቅያማ ቀን ተልቢያ እያለ ይነሳልና፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡