የመካ ስም በካ በሚል ቃል በቀጣዩ የአላህ ቃል ውስጥ ተመልክቷል፡- ‹‹ለሰዎች (መጸለያ) መጀመሪያ የተኖረው ቤት ብሩክና ለዓለማት ሁሉ መምሪያ ሲኾን፣ያ በበካህ (መካ) ያለው ነው፡፡›› [ኣል-ዒምራን:96]
የመካ ታሪክ የመጀመሪያ ነዋሪዎቿ ወደ ሆኑት ነቢዩ ኢብራሂምና ልጃቸው ነቢዩ እስማዒል ዘመን ከልደት በፊት ወደ አስራ ዘጠነኛው ምእተ ዓመት ይመልሰናል፡፡ አላህ ስለ ኢብራሂም ሲናገር ፡- ‹‹ጌታችን ሆይ! አዝመራ በሌለው ሸለቆ ውስጥ በተከበረው ቤትህ (በከዕባ) አጠገብ ከዘሮቼ አስቀመጥሁ፤ጌታችን ሆይ! ሶላትን ያቋቁሙ ዘንድ (አስቀመጥኳቸው)፤ከሰዎችም ልቦችን ወደነሱ የሚናፍቁ አድርግ፤ያመሰግኑህም ዘንድ ከፍሬዎች ስጣቸው፡፡›› [ኢብራሂም:37]
ብሏል፡፡ ከእናታቸው ከሃጀር ውሃና ምግብ ሲሟጠጥ በነቢዩ እስማዒል እግሮች ስር የዘምዘም ውሃ በነቢዩ ኢብራሂም ዱዓእ መነጨ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዐረብ ጎሳዎች ወደ ውሃው ምንጭ መጉረፍ ጀመሩና ደረቁ ሸለቆ ሕይወት መዝራት ጀመረ፡
በአከባቢው የሚሰፍሩ የዐረብ ጎሳዎች ወደ ቦታው መጉረፋቸውን በመቀጠል እየበዙ መጡ፡፡ ጎሳዎቹን የመምራትና የማስተዳደርር ኃላፊነት ወደ ቁረይሽ ጎሳ እጅ ገባ፡፡ በተከበረችው የመካ ከተማና በመላው ዓለም የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ታላቅ የለውጥ ተጽእኖ የነበራቸው ነቢዩ ሙሐመድ ﷺ እስከ መጡበት ጊዜ ድረስ የቁረይሽ ጎሳ መሪነቱ እንደያዘ ቆየ፡፡
ሙሐመድ ﷺ በመካ በነቢይነት ከአላህ ወደ መላው የሰው ልጆች ተላኩ፡፡ ከዕባ የሙስሊሞች ቅብላ (በሶላት ጊዜ ፊታቸውን የሚያዞሩበት አቅጣጫ) ሆነ፡፡ መካም የእስላማዊው ደዕዋ (ጥሪ) ማእከል ሆነች፡፡ የመካ ነዋሪዎች ግን ከሰዎች ሁሉ ከጥሪው ያፈነገጡ ከሁሉም በላይ ተከታቹን ያሰቃዩ ስለነበር፣ሙስሊሞች ወደ መዲና ለመሰደድ ተገደው የእስላም መንግሥት እዚያ ተመሰረተ፡፡ በኋላ ነቢዩ ﷺ በድል አድራጊነት ወደ መካ ተመለሱ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መካ ትልቅ እስላማዊት አገር ሆናለች፡፡
የተከበረችው የመካ ከተማና በተለይም የመካው ሐረም ከሙስሊሞች ኸሊፋዎችና መሪዎች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ተችሯታል፡፡ ሁሉም ከተማዋን በማሳደግ፣ በማስፋፋትና የእስላም ብርሃን ወደ መላው ዓለም የሚፈነጥቅበት ማእከል ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የመካ ትሩፋት
1 - ወደ ሐረም የገባ ሰው ሰላም የሚያገኝ መሆኑ
አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹የገባውም ሰው ጸጥተኛ ይኾናል፤›› [ኣል-ዒምራን:97] ይህም ወደ መካ ሐረም የገባ ሰው አይነካም፣የደህንነት ዋስትና ያገኛል ማለት ነው፡፡
2 - ሐሳዊ መሲሕም (ደጃል) ሆነ ወረርሽኝ በሽታ ወደ ሐረሙ የማይገባ መሆኑ
ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹መዲናና መካ በመላእካ የተከበቡ ናቸው፣በያንዳንዱ መንገድ ላይ መልአክ አለ፤ደጃልም ሆነ ወረርሽኝ በሽታ አይገባባቸውም፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
3 - በተከበረው የመካ መስጊድ የሚሰገደው ሶላት ሌላ ቦታ ከሚሰገደው በመቶ ሺህ የሚበልጥ መሆኑ
ከጃቢር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹በመስጅድ አልሐራም የሚሰገድ አንድ ሶላት ሌላ ቦታ ከሚሰገደው መቶ ሺህ ሶላት በላጭ ነው፡፡›› [በእብን ማጃህ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
4 - ከቦታዎች ሁሉ አላህ ዘንድ ይበልጥ የተወደደ መሆኑ
የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹በአላህ እምላለሁ (መካ) ከአላህ መሬት ሁሉ በላጭ ነሽ፤በአላህ ዘንድም ከአላህ ምድር ሁሉ ይበልጥ ተወዳጅ ነሽ፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
የተከበረችው መካ
መካና ሐረምን የሚመለከቱ ልዩ ድንጋጌዎች
1 - በተግባር ፈጸመውም አልፈጸመ ሐረም ውስጥ ክፉ ለመስራት ባሰበ ሰው ላይ ብርቱ ማስጠንቀቂያ የተላለፈ መሆኑ
አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹በርሱም ውስጥ (ከትክክለኛ መንገድ) በመዘንበል (በእልሓድ) በዳይ ኾኖ (ማንኛውንም ነገር) የሚፈልግ ሰው፣ከአሳማሚ ቅጣት እናቀምሰዋለን፡፡›› [አልሐጅ፡25]
እልሓድ ወይም ከቀጥተኛ መንገድ መውጣት ሁሉም ዓይነት የአላህ ትእዛዝ ጥሰትን የሚያካትት ነው፡፡ ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹አላህ ዘንድ ከሁሉም ይበልጥ የተጠሉት ሰዎች ሦስት ናቸው›› ብለው ከነዚህ ውስጥ ‹‹በሐረም ውስጥ የአላህ ትእዛዝን ጥሰት የሚፈጽም ሰው (ሙልሕድ)›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ጠቅሰዋል፡፡
2 - በርሱ ውስጥ መዋጋትና ደም ማፋሰስ ሐራም መሆኑ
አላህ ፡- ‹‹ቤቱንም (ከዕባን) ለሰዎች መመለሻና ጸጥተኛ ባደረግን ጊዜ (አስታውስ፤›› [አል-በቀራህ:125]
ብሏል፡፡ ወደ መካ የገባ ሰው የሰላምና የደህንነት ዋስትና ያገኛል፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ﷺ ‹‹መካ ውስጥ የጦር መሳሪያን መያዝ ለማንኛችሁም አይፈቀድም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ያሉት፡፡
በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹መካን አላህ ነው የታፈረ ክልል አድርጎ የከለለው፣ሰዎች አይደሉም የከለሉት፤ሰለዚህም በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሰው፣በውስጡ ደም ማፋሰስም ሆነ ዛፍ መቁረጥ አይፈቀድለትም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
ውጊያና ደም ማፍሰስ
3 - ለካፍሮችና ለሙሽሪኮች ወደ ሐረም መግባት የተከለከለ መሆኑ
አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው፤ከዘህም ዓመታቸው (ዘጠነኛው ዓመተ ህጅሪያ) በኋላ፣የተከበረውን መስጊድ አይቅረቡ፤›› [አል-ተውባህ:28]
ነቢዩ ﷺ በሚና እያሉ ፡- ‹‹ከዚህ ዓመት በኋላ ሙሽሪክ የሆነ ሰው ሐጅ እንዳያደርግና ራቆቱን የሆነ ሰውም ጠዋፍ እንዳያደርግ (በከዕባ ዙሪያ እንዳይዞር)›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ተብሎ እንዲታወጅ አዘዋል፡፡
4 - ሐረም ውስጥ አውሬ ማደን፣ዛፍ መቁረጥና ለበጎ ሥራ ካልሆነ በስተቀር የወደ ዕቃን መውሰድ ሐራም መሆኑ
ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹መካን አላህ የማይፈቀድ የታፈረ ክልል አድርጎታል፣ከኔ በፊትም ሆነ ከኔ በኋላ ለማንም አልፈቀደም፤ከቀኑ ለአንድ ሰዓት ለኔ ብቻ ነው የተፈቀደው፤ስለሆነም እርጥብ ተክሉ አይቀነጠስም፣ዛፉ አይቆረጥም፣የአደን አውሬው እንዲበረግግ አይደረግም፣ለሰናይ ተግባር ካልሆነ በስተቀር ወድቆ የተገኘ እቃም አይወሰድም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
የሐጅ ሥርዓት ክንውኖች (መሻዕር)