ሐጅና ዑምራን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች

4114

      ሐጅ

      የሐጅ ትርጓሜ

የሐጅ የቋንቋ ትርጉም

ማሰብና ማምራት ነው፡፡

የሐጅ ሸሪዓዊ ትርጉም

የተለየ የዕባዳ ክንውን ለመፈጸም በተወሰነ ወቅት ወደ መካ ማምራት ነው፡፡

      ሐጅን የሚመለከት ድንጋጌና ትሩፋቱ

      ሐጅ አላህ በአገልጋዮቹ ላይ የደነገገውና ከእስላም ማእዘናት አንዱ የሆነ ማእዘን ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መኼድን፣በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው፤የካደም ሰው አላህ ከዓለማት ሁሉ የተብቃቃ ነው፡፡›› [ኣል-ኢምራን:97]

      ነቢዩምﷺ ፡- ‹‹እስላም በአምስት (ማእዘኖች) ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ (እነሱም) ፡- ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን መመስከር፣ሶላትን ደንቡን ጠብቆ አዘውትሮ መስገድ፣ዘካን መስጠት፣የሐጅ ሥርዓተ ጸሎት መፈጸምና ረመዷንን መጾም ናቸው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      በተጨማሪም የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹መጥፎ ሳይናገርና የትእዛዝ ጥሰት (መዕሲያ) ሳይፈጽም ሐጅ ያደረገ ሰው፣ያለፈ ኃጢአቱ ይሰረይለታል፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      የሐጅ ሥርዓትን በዕድሜ ዘመን ውስጥ አንድ ጊዜ መፈጸም ግዴታ (ዋጅብ) ነው፡፡

      ለሐጅ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

      1 - ሙስሊም መሆን

      በካፍር ላይ ግዴታ አይሆንም፤ከርሱ ተቀባይነት የለውም፡፡

      2 - የአእምሮ ጤንነት

      ራሱን በሳተ የአእምሮ ሕመምተኛ ላይ ግዴታ አይሆንም፡፡ ነቢዩﷺ ፡- ‹‹ሦስት ሰዎች በሚሰሩት ሥራ አይጠየቁም (ጥፋት አይመዘገብባቸውም)፡፡ የተኛ ሰው እስኪነቃ ድረስ፣ ሕጻን ልጅ ለአቅመ አዳም/ሔዋን እስኪደርስ ድረስ፣ያበደ ሰው ወደ አእምሮው እስኪመለስ ድረስ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

      3 - ለአቅመ አዳም/ሔዋን መድረስ

      በሕጻን ልጅ ላይ ግዴታ አይሆንም፡፡ ለሐጅ እሕራም ካደረገ ሐጁ ትክክለኛ (ሶሒሕ) ሲሆን፣የጌዴታውን ሐጅ መተካት የማይችል ነፍል ሐጅ ነው የሚሆነው፡፡ እብን ዐባስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት አንዲት ሴት ሕጻን ልጅ ወደ አላህ መልእክተኛ ﷺ ከፍ አድርጋ እያሳየች ይኸ ሐጅ ማድረግ ይችላልን? ስትላቸው ‹‹አዎ፣አንቺም አጅር አለሽ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] አሏት ብለዋል፡፡

      ሕጻን ልጅ ለሐጅ እሕራም ማድረግ ይፈቀዳል

      4 - ከጫንቃ ተገዥነት ነጻ መሆን

      በጫንቃ ተገዥ አገልጋይ ላይ ግዴታ አይሆንም፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሐጅ ያደረገና ከዚያ በኋላ ነጻ የወጣ ማንኛውም የሰው አገልጋይ ሌላ ሐጅ ማድረግ ይኖርበታል፡፡››[በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

      5 - የአቅምና የችሎታ መኖር

      ይህም የስንቅና [ስንቅ ማለት አስፈላጊ የሆነ ምግብ፣መጠጥና ልብስ ነው፡፡] የመጓጓዣ [ማጓጓዣ እንደ መኪና አይሮፕላን ወይም መርከብ ያለ ማመላለሻ ነው፡፡] መኖር ነው፡ አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መኼድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን የመጎብኘት ግዴታ አለባቸው፤›› [ኣል-ኢምራን:97]

      6 - ከሴት ጋር መሕረም [መሕረም ማለት እንደ አባትና ወንድም ያለ በደም የሚዛመድ፣ ወይም እንደ ባል፣የባል አባት ያለ በጋብቻ የሚዛመድ፣እንደ ጡት አባትና የጡት ወንድም ያለና የመሳሰለው ከሴቲቱ ጋር በጋብቻ መጣመር የማይችል ወንድ ዘመድ ነው፡፡] መኖር

      እብን ዐባስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ነቢዩ ﷺ ኹጥባ አድርገው ፡- ‹‹ሴት በጋብቻ ሊጣመራት ከማይችል የሥጋ ዘመድ ጋር እንጂ አትሳፈርም፡፡›› ሲሉ አንድ ሰውዬ ተነስቶ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ባለቤቴ ሐጅ ለማድረግ ሄዳለች፣ እኔ ደግሞ ለዘመቻ ተመድቤያለሁ›› አላቸው፡፡ እሳቸውም ﷺ ‹‹ሂድ ድረስባትና ከባለቤትህ ጋር ሐጅ አድርግ›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] አሉት ብለዋል፡፡

      ለሐጅ ሌላ ሰው ስለ መወከል

      በዕድሜ መግፋት ወይም የመዳን ተስፋ በሌለው በሽታ ምክንያት ወይም በአካላዊ ድክመት መሳፈር ባለመቻሉ ሐጅና ዑምራ ማድረግ ያቃተው ሰው፣በርሱ ፋንታ ሐጅና ዑምራ የሚያደርግለትን ሰው መወከል ይገባዋል፡፡ ወኪሉ ለሐጅና ዑምራ እሕራም ካደረገ በኋላ ከበሽታው ቢፈወስ እንኳ የሐጅ ግዴታውን የተወጣ ይሆናል፡፡

      ፈድል ብን ዐባስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹የኸሥዐም ጎሳ የሆነች አንዲት ሴት የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አባቴ የአላህ የሐጅ ግዴታ የጸናበት ሲሆን ዕድሜው የገፋ ሽማግሌ በመሆኑ በግመል ጀርባ ተቀምጦ መጓዝ አይችልም ስትላቸው ‹‹ስለሱ ሆነሽ ሐጅ አድርጊለት፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] አሏት ብለዋል፡፡

      ሐጅ ማድረግ ያቃተው ሰው

      ሌላ ሰው ወክሎ ሐጅ የሚያደርግ ሰው ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል ፡-

      1 - ቀደም ሲል የተጠቀሱ የሐጅ ሸርጦችን የሚያሟላ መሆን፡፡

      2 - ተወካዩ ለራሱ የሐጅ ግዴታውን የፈጸመ መሆን፡ ለራሱ ሐጅ ሳያደርግ ለሌላ ሰው ሐጅ ያደረገ ሰው ሐጁ ትክክለኛ አይሆንም፣ያደረገው ሐጅ ለራሱ ያደረገው የሐጅ ግዴታ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ለዚህ ማስረጃው እብን ዐባስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹ነቢዩﷺ ስለ ሹብሩማ ሆኜ ለሐጅ ለብበይከ› የሚል ሰውዬ ሰሙና ‹ሹብሩማ ማነው? አሉት፡፡ የኔ ወንድም ነው ወይም ዘመዴ ነው አላቸው፡፡ ለራስህ ሐጅ አድርገሃል? ሲሉት አላደረኩም አላቸው፡፡ ለራስህ ሐጅ አድርግና ከዚያ በኋላ ሹብሩማን ወክለህ ሐጅ አድርግለት፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] አሉት ብለዋል፡፡

      ዑምራ

      የዑምራ ትርጓሜ

የዑምራ የቋንቋ ትርጉም

ጉብኝት ማለት ነው፡፡

የዑምራ ሸሪዓዊ ትርጉም

ወደ መካ በመሄድ በይቱል ሐራምን በማንኛውም ወቅት የተለየ የዕባዳ ሥርዓትን ለማከናወን ዓላማ መጎብኘት ማለት ነው፡፡

    ዑምራን የሚመለከት ድንጋጌና ትሩፋቱ

    ዑምራ እንደ ሐጅ ሁሉ በዕድሜ ዘመን አንድ ጊዜ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ ነቢዩምﷺ ፡- ‹‹እስላም በአምስት (ማእዘኖች) ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ (እነሱም) ፡- ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንቡን ጠብቆ አዘውትሮ መስገድ፣ዘካን መስጠት፣ የሐጅ ሥርዓተ ጸሎት መፈጸምና ረመዷንን መጾም ናቸው፡፡››[በእብን ኹዘይማ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    በተጨማሪም የአላህ መልእክተኛﷺ ‹‹አንዱ ዑምራ እስከ ቀጣዩ ዑምራ በመካከላቸው ለተፈጸመ (መለስተኛ ኃጢአት) ማበሻ ነው፡፡ ተቀባይነት ያለው ሐጅ ከጀነት በስተቀር ሌላ ምንዳ የለውም፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡