የጾም ማእዘናት በጾም ጊዜ የሚወደዱ የሚጠሉና ጾሙን የሚያበላሹ ነገሮች

5782

    የጾም ማእዘናት

    የመጀመሪያው ማእዘን ፡ ጾምን ከሚያበላሹ ነገሮች ከጎሕ መቅደድ እስከ ጸሐይ መጥለቅ ድረስ ተቆጥቦ መዋል፡፡

    አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለናንተ እስከሚገለጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ጠጡም፤ ከዚያም ጾምን እስከ ሌሊቱ ድረስ ሙሉ፤›› [አል-በቀራህ፡187]

    ሁለተኛው ማእዘን ፡ ንይ’ያ

    ንይያ ማለትም ለአላህU ዕባዳ ብሎ ጾምን ከሚያስፈስኩ ነገሮች ለመቆጠብ ቁርጠኛ ውሳኔ ማድረግ፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሥራዎች (የሚለኩት ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) ውሳኔ ነው፤እያንዳንዱ ሰውም በንይ’ያው መሰረት ነው የሚያገኘው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ንይ’ያ በጾም
    ጾሙ የግዴታ ጾም ከሆነ ንይ’ያው አስቀድሞ ከሌሊቱ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ጾሙ ግዴታ ያልሆነ በፈቃደኝነት የሚጾም ነፍል ከሆነ ግን ጾምን የሚያበላሽ ነገር እስካልፈጸመ ድረስ ከነጋ በኋላ ቀን ነይቶ መጾም ይቻላል፡፡ እመ ምእመናን ዓእሻ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ አንድ ቀን መጥተው የሚበላ ነገር አላችሁን? ሲሉ የለም አልን፤ ‹እንግዲያውስ እኔ ጾመኛ ነኝ› አሉ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በጾም ጊዜ የሚፈቀዱ ነገሮች

    1 - ገላን መታጠብና ራስን ለማቀዝቀዝ ውሃ ውስጥ መቀመጥ፡፡

    2 - ምራቅና አክታን መዋጥ፡፡

    3 - ምንም ነገር ወደ ጉሮሮ እንዳልፍ ከማድረግ ግዴታ ጋር በምላስ ብቻ ምግብ መቅመስ፡፡

    4 - ጥሩ መዓዛ ያላቸውን ነገሮችና የአየር ማደሻ ሽታን ማሽተት፡፡

    ስዋክን (መፋቂያ) መጠቀም ለጾመኛ ሰው

    የጥርስ መፋቂያን መጠቀም ከቀትር በፊትም ሆነ ከቀትር በኋላ፣በማንኛውም ወቅት፣ስዋኩ እርጥብም ይሁን ደረቅ የተደነገገ ሲሆን እርጥብ ከሆነ ግን ወደ ጉሮሮ እንዳያልፍ መጠንቀቅ ማድረግ ይገባል፡፡ ካለፈ ጾም ያስፈጥራልና፡፡

    በጾም የሚወደዱ ነገሮች

    1 - ሱሑር መበላትና ለፈጅር አዛን ጥቂት ጊዜ እስኪቀር ድረስ ማዘግየት

    ነቢዩ ﷺ ‹‹ሱሑር ብሉ ሱሑር በረካ አለበትና፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡ የሱሑር ሱንና በብዙም ሆነ በትንሽ ምግብ፣አንድ ጊዜ ውሃ በመጎንጨትም ቢሆን ሊገኝ ይችላል፡፡

    ነቢዩ ﷺ ‹‹ሱሑርን መመገብ በረካ አለውና አትተውት፣አንዳችሁ አንድ ጊዜ ውሃ መጎንጨት ቢሆን እንኳ (አትተውት)፡፡ አላህና መላእኮቹ ሱሑርን በሚበሉት ላይ ሶላት (ምሕረትና ዱዓእ) ያወርዳሉና፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ሱሑርን ወደ ሌሊቱ መጨረሻ ማዘግየት የተወደደ ነው፡፡ ዘይድ ብን ሣቢት (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት፡ ‹‹ከአላህ መልእክተኛ ﷺ ጋር ሱሑር በልተን ከዚያ ወደ ሶላት ተነሳን›› ሲሉ አነስ ብን ማሊክ ‹‹በሁለቱ መካከል የነበረው ጊዜ ምን ያህል ነበር?›› ብለው ጠየቁ፣ ‹‹ሃምሳ የቁርኣን ኣያ የሚቀራበት ያህል ነው›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡፡

    አዛን እየተደረገ መጠጣት

    አንድ ሰው አዛን በመደረግ ላይ መሆኑን ቢሰማና የሚጠጣውን ነገር በእጁ ይዞ የሚገኝ ከሆነ እስኪያበቃ መጠጣት ይችላል፡፡ ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹አንዳችሁ (የመጠጫ) እቃውን በእጁ ላይ እንደያዘ አዛን ሲደረግ ከሰማ (ጠጥቶ) ፍላጎቱን እስኪያረካ ድረስ አያስቀምጠው፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ዑለማእ ይህን ሐዲስ ጎህ ቀዷል አልቀደደም ብሎ የተጠራጠረውን ሰው የሚመለከት ያደርጉታል፡፡ ጎህ መቅደዱን ያረጋገጠ ሰው ግን መብላትም ሆነ መጠጣት አይገባውም፣እርግጠኛ ከሆነ በኋላ ከፈጸመው ግን ጾሙ ተበላሽቷልና መክፍል (ቀዷእ) ግዴታ ይሆንበታል፡፡

    2 - ፍጥርን ማፋጠን

    ጾመኛው ጸሐይ መጥለቋን ካረጋገጠ ጾሙን ቶሎ መፈሰክ የተወደደ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሰዎች ፍጥርን እስካፋጠኑ ድረስ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ይቀጥላሉ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ማታ ሲፈሰክ በእሸት ተምር፣ ካልተገኘ በተምር ማፍጠርና የፍሬዎቹ በኢተጋማሽ (ውትር) ቁጥር መሆን የተወደደ ነው፡፡ ተምር ካልተገኘ ደግሞ ውሃ በመጎንጨት ማፍጠር ነው፡፡

    አነስ ብን ማሊክ (ረዐ) ባስተላለፉት ሐዲስ ነቢዩ ﷺ ‹‹ነቢዩ ﷺ ከመስገዳቸው በፊት በእሸት ተምር፣እሸቱ ከሌለ በተምር ፍሬዎች፣ ካልተገኘም ውሃ በመጎንጨት ያፈጥሩ ነበር፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የሚያፈጥርበት ምንም ነገር ካልተገኘ በልቡ ፍጥር መነየት ብቻ በቂ ይሆናል፡፡

    በስሕተት ያፈጠረ ሰው

    አንድ ጾመኛ ጸሐይ የጠለቀች ወይም ገና ጎህ ያልቀደደ መስሎት ቢበላና ግምቱ የተሳሳተ መሆኑ ቢረጋገጥ ጾሙን የመክፈል ግዴታ አይኖርበትም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹በርሱ በተሳሳታችሁበት ነገርም በናንተ ላይ ኃጢአት የለባችሁም፤ግን ልቦቻችሁ ዐውቀው በሠሩት፣(ኃጢኣት አለባችሁ)፤አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡›› [አል-አሕዛብ፡5]

    ነቢዩምﷺ ‹‹በስሕተት፣በመርሳትና ተገደው በሠሩት ነገር የመጠየቅ ኃላፊነትን አላህ ከኔ ኡመት ላይ አንስቷል፡፡›› [በእብን ማጃህ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - በፍጥር ጊዜ የሚደረግ ዱዓእ

    የአላህ መልእክተኛﷺ ሲያፈጥሩ ፡- ‹‹ዘሀበ አዝ’ዘመኡ፣ ወብተል’ለትል ዑሩቁ፣ወሠበተል አጅሩ እንሻአል’ሏህ›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ይሉ ነበር፡፡

    ትርጉሙ ‹‹ጥማቱ ሄደ፣ጅማቶቹ ራሱ፣ በአላህ ፈቃድ አጅሩም (ምንዳው) ጸና፡፡›› ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ‹‹ጾመኛ ሰው በሚያፈጥርበት ጊዜ እምቢ የማይባል (መቅቡል የሆነ) ዱዓእ አለው፡፡›› [በእብን ማጃህ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    4 - አልባሌና መጥፎ ቃላትን መተው

    ነቢዩ ﷺ ‹‹አንዳችሁ በሚጾምበት ቀን መጥፎ ነገር አይናገር፤ድምጹንም ከመጠን በላይ ከፍ አያድርግ (አይጣላ፣አይጯጮህ)፡፡ ሌላ ሰው ቢዘልፈው ወይም ቢጣላው እኔ ጾመኛ ነኝ፣እኔ ጾመኛ ነኝ ይበልም፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ‹‹በሐሰት መመስከርን እና በዚያ መሰረት መስራትን እርግፍ አድርጎ ያልተወን ሰው፣ምግብና መጠጡን ከመተው አላህ ጉዳይ የለውም፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    5 - ዕባዳዎችን ማብዛት

    ቁርኣን መቅራትን፣አላህን መዘከርን፣የተራዊሕ ሶላትና ቅያም አል’ለይልን፣የለይለቱል ቀድርን ምሽት በዕባዳ ሕያው ማድረግን፣ረዋትብ ሱናዎች መስገድን፣ሶደቃ መስጠትን፣ልገሳና ደግነትን፣ለበጎ ሥራዎች ወጭ ማድረግን፣ጾመኞችን ማስፈጠርን፣ዑምራ ማድረግን የመሳሰሉ ዕባዳዎችን ማብዛት ረመዷን ውስጥ የሚሰራ መልካም ሥራ አጅሩ እጥፍ ድርብ በመሆኑ እጅግ የተወደደ ነው፡፡

    ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ በጎ ነገር በመለገስ ከሰዎች ሁሉ የበለጠ ቸር ሲሆኑ ከምንጊዜም በላይ እጅግ ለጋስ የሚሆኑት በረመዷን ወር ነበር፡፡ ከጅብሪል በየዓመቱ በረመዷን ይገናኙና የአላህ መልእክተኛ ﷺ ቁርኣንን ለጥናት በርሱ ላይ ይቀሩ ነበር፡፡ ከጅብሪል U ጋር ሲገናኙ የአላህ መልእክተኛ ﷺ በበጎ ሥራና በልገሳ ከተለቀቀ ንፋስ ይበልጥ ቸር፣ፈጣንና ሁሉን የሚያዳርሱ ነበሩ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    6 - በመጨረሻዎቹ የረመዷን አስር ቀናት ለዕባዳ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ

    ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት፡- ‹‹ነቢዩ ﷺ የረመዷን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ሲጀምሩ ሽርጣቸውን ያጠብቁ [ከወገብ በታች የሚታጠቁትን ሽርጥ ማጥበቅ ማለት ከተለመደው በላይ ልዩ ጥረት ማድረግን የሚያመለክት ሲሆን፣አባባሉ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መራቅንም ያመለክታል ተብሏል፡፡]፣ሌሊቶቹን (በዕባዳ) ሕያው ያደርጉና ቤተሰባቸውንም (ለዕባዳ) ይቀሰቅሱ ነበር፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በጾም የሚጠሉ ነገሮች

    1 - መጉመጥመጥንና ውሃ በአፍንጫ መሳብን ከልክ በላይ ማድረግ

    ይህም ውሃ ከጉሮሮ አልፎ እንዳይሄድና ጾም እንዳይበላሽ ሲባል ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ውሃ በአፍንጫ ስበህ ማስወጣትን ጾመኛ ካልሆንክ በደንብ አድርግ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    2 - ስሜት በሚቀሰቅስ ሁኔታ መሳሳም

    ጾመኛ ሰው አባለዘር እንዳይወጣ ወይም ወሲባዊ ስሜቱ እንዳይቀሰቀስ ከፈራ ለዚህ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ሁሉ መራቅ ስለሚኖርበት መሳሳም የተጠላ ነው፡፡

    ጾሜ አይበላሽም ብሎ በራሱ ከተማመነ ግን ማድረጉ ችግር የለውም፡፡ ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት፡- ‹‹ነቢዩ ﷺ ጾመኛ ሆነው ይስሙና ገላ ለገላ ይነካኩ ነበር፤ከማንኛችሁም በላይ ስሜታቸውን የሚቆጣጠሩም ነበሩ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ለዚህም ነው ከተቃራኒ ጾታ ጋር ንኪኪ መፍጠር ለሽማግሌ ሳይሆን ለወጣት የተጠላ የሆነው፡፡ አቡ ሁረይራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹አንድ ሰው ጾመኛ ሆኖ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ንኪኪ ስለማድረግ ነቢዩን ﷺ ሲጠይቃቸው ፈቀዱለት፤ሌላ ሰው መጥቶ ሲጠይቃቸው ደግሞ ከለከሉት፤የፈቀዱለት ሰውዬ ሸማግሌ ሲሆን የከለኩት ደግሞ ወጣት ነበር፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ጾምን የሚያበላሹ ነገሮች

    1 - ረመዷን ውስጥ በቀን ሆን ብሎ መብላትና መጠጣት

    አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለናንተ እስከሚገለጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ጠጡም፤ ከዚያም ጾምን እስከሌሊቱ ድረስ ሙሉ፤›› [አል-በቀራህ፡187]

    ለሥራ ብሎ ማፍጠር
    በመጋገሪዎች እና አስቸጋሪ በሆኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩት፣እንደ ሌላው ሙስሊም ሁሉ የመጾም ግዴታ ስላለባቸው በሥራቸው ክብደት ምክንያት እንዲያፈጥሩ አይፈቀድላቸውም፡፡

    ማሳሰቢያዎች

    - ዘንግቶ የበላ ወይም የጠጣ ጾመኛ ጾሙ ትክክለኛ ሲሆን ሲያስታውስ ወዲያውኑ ማቆም ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ጾመኛ መሆኑን ረስቶ የበላ ወይም የጠጣ ሰው፣ያበላውና ያጠጣው አላህ ነውና ጾሙን ቀጥሎ ያሟላው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    - ለምግብነት በሕክምና መርፌ የሚሰጠው የምግብነትና የመጠጥነት ባህሪ ያለው በአፍ በኩልም ሆነ በአፍንጫ ወደ ውስጥ የሚደርስ ማንኛውም ነገር ጾምን ያበላሻል፡፡ ምግብን የማይተካ እንደ ፔንስሊን ያለና የመሳሰለው መርፌ ግን ለምግብነትም ሆነ ለመጠጥነት የማያገለግል በመሆኑ ጾም አያበላሽም፡፡

    ለቀለብነት የሚውል መድኃኒት ጾም ያበላሻል
    የፔንስሊን መርፌ ጾም አያበላሽም

    - የግድ አስፈላጊ ሆኖ በአፍ በኩል የሚገባ እንደ ህክምና መመርመሪያ ቱቦና የአስም ሕሙማን አየር መንፊያ ያለው ጾም አያበላሽም፡፡

    የአስም አየር መንፊያ ጾም አያበላሽም

    - የዓይን ኩል፣በዓይንና ጆሮ የሚጨመር ጠብታ ጾም ስለማበላሸታቸው ማስረጃ ባለመኖሩና ዓይን መደበኛው የምግብ መግቢያ መንገድ ባለ መሆኑ ጾም አያበላሽም፡ የጆሮና የአፍንጫ ጠብታም እንዲሁ፡፡ የአፍንጫ ጠብታን በተመለከተ ግን ነቢዩ ﷺ ጾመኛ እስትንሻቅን በሚገባ እንዳያደርግ የከለከሉ [በትርምዚ የተዘገበ] በመሆኑና አፍንጫ የምግብ መግቢያ መንገድ ሊሆን በመቻሉ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

    የዓይን ኩል ጾም አያስፈጥርም

    - ለቀለብነት የማያገለግል ወይም ጎጂ የሆነ እንደ ሲጋራ ያለ ነገር፣በምግብ መግቢያ በኩል የሚወሰድ ከመሆኑም በላይ የምግብነትና መጠጥነት ትርጉም ያለው በመሆኑ መውሰዱ ጾም ያበላሻል፡፡

    ሲጋራ ማጤስ ጾም ያበላሻል

    - እንደ መንገድ አቧራና ጥርሶች መካከል የሚቀሩ የምግብ ቅሪቶችን የመሳሰሉ በጥንቃቄ ለማስቀረት የሚያስቸግሩ ነገሮችም ጾም አያበላሹም፡

    በጥርሶች መካከል የሚቀር ቅሪት አያስፈጥርም

    2 - የግብረ ሥጋ ግንኙነት

    አላህ አንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹በጾም ሌሊት ወደ ሴቶቻችሁ መድረስ ለናንተ ተፈቀደላችሁ፤›› [አል-በቀራህ፡187]

    ጾመኛ ሆኖ ወሲባዊ ግንኙነት የፈጸመ ሰው ጾሙ የሚበላሽ ሲሆን፣ያበላሸውን ቀን ጾም ከከፍተኛው ማበሻ (ከፍ’ፋራ ሙገል’ለዛ) ጋር የመክፈል ግዴታ አለበት፡ ይህም ጫንቃን ነጻ ማውጣት፣ካላገኘ ሁለት ወር በተከታታይ መጾም፣ካልቻለ ስልሳ ድኾችን መመገብ ነው፡፡

    አቡ ሁረይራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹አንድ ሰውዬ ወደ ነቢዩ ﷺ መጣና እኔ ጠፍቻለሁ! አለ፤ምን ሆነሃል? አሉት፡፡ በረመዷን (ቀን) ከሚስቴ ጋር ግንኙነት ፈጸምኩ አላቸው፡፡ ጫንቃ ነጻ ማውጣት ትችላለህ? ሲሉት አልችልም አላቸው፡፡ ሁለት ወራት በተከታታይ መጾምስ ትችላለህ? አሉት፡፡ አልችልም አለ፡፡ ስልሳ ድኾችን መመገብ ትችላለህ? አሉት፤ አልችልም አለ፡፡ እስኪ ቁጭ በል አሉትና ተቀመጠ፡፡ ነቢዩ ﷺ በአንድ ትልቅ መስፈሪያ ﷺ ተምር አመጡና ይህን ወስደህ ሶደቃ ስጥ አሉት፡፡ ከኛ የበለጠ ድኃ ለሆነ ሰው ነው? ሲል ጠየቃቸው፡ ነቢዩ ﷺ የጎን ጥርሶቻቸው እስኪታዩ ድረስ ሳቁና ቤተሰብህን መግበው አሉት፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ከፍ’ፋራው በተጠቀሰው ቅደም ተከተል መሰረት መሆን ይኖርበታል፡፡ መጾም የሚችል እስከሆነ ድረስ ድኾችን አይመግብም፤ጫንቃን ነጻ ማውጣት እስከቻለ ድረስም በተከታታይ አይጾምም፡፡

    ሴቲቱ ለወንድዬው አድራጎት ፈቃደኛ ሆና አብራ ከፈጸመች ከፍፋራው እሷንም ይመለከታል፡፡ ባሏ ለግብረ ሥጋ ግንኙነት አስገድዷት ከሆነ ግን ጾሟ የሚበላሽ በመሆኑ ከፍ’ፋራው ሲቀር ጾሙን የመክፈል ግዴታ ይኖርባታል፡፡

    - የአባለዘር ፈሳሽ በፍላጎት ከብልት መርጨት እንደ ግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚታይ ሲሆን፣ጾመኛው በመሳሳም በመተሻሸት ወይም ብልትን በመነካካትና በሌላ ምክንያት እንዲወጣ ካደረገ፣እነዚህ ሁሉ ጾምን የሚጻረር ስሜታዊ ፍላጎት በመሆናቸው ጾሙ ይበላሻል፡ ስለዚህም ያለ ማበሻ ከፍፋራ ጾሙን የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ማስረጃ የተላለፈው የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ብቻ አስመልክቶ በመሆኑ ከፍፋራው አይመለከተውም፡፡

    - በገላ ንክኪ ወይም ስለወሲብ በማሰብ የመዚይ እርጥበት ከብልት ቢወጣ ማስረጃ ባለመኖሩ ጾም አያበላሽም፡፡

    - ጾመኛው ቀን ተኝቶ በሕልሙ ወሲብ ቢፈጽም፣ ወይም በበሽታ ምክንያት የአባለዘር ፈሳሽ ከብልቱ ቢፈስ፣ከርሱ ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ጾሙ አይበላሽም፡፡

    - ከጎህ መቅደድ በፊት በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም በወሲባዊ ሕልም ምክንያት ገላን የመታጠብ ግዴታ (ጀናባ) ኖሮበት ሳይታጠብ የነጋበት ጾመኛ ጾሙ ትክክለኛ ሲሆን፣የሱብሕን ሶላት በጀማዓ ለመስገድ ገላውን መታጠብ ይኖርበታል፡፡ ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ጀናባ እያለባቸው የፈጅር ሶላት ይደርስባቸውና ገላቸውን ታጥበው ይጾሙ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡

    3 - ሆን ብሎ ማስታወክ

    ይህ በፍላጎት ምግብና መጠጥን ከሆድ በአፍ በኩል ማስወጣት ሲሆን፣ከፍላጎት ወጭ ካስመለሰው ግን ጾሙ ላይ ችግር አይፈጥርበትም፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ከፍላጎቱ ውጭ ያስመለሰው ሰው (ጾሙን) መክፈል አይኖርበትም፤ሆን ብሎ ያስታወከ ግን ይክፈል፡፡›› ብለዋልና፡፡

    4 - የወር አበባና የወሊድ ደም

    አንዲት ሴት ጸሐይ ከመጥለቋ ከጥቂት ሰከንዶች በፊት እንኳ ቢሆን የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ካየች ጾሟ ስለሚበላሽ የመክፈል ግዴታ ይኖርባታል፡፡

    ጠቃሚ ነጥብ

    -ዋግምት (ደምን በተለየ ሁኔታ ከሰውነት ማስወጣት) ሚዛን በደፋው የዑለማእ አቋም ጾም አያበላሽም፡፡ ነቢዩ ﷺ እየጾሙ ዋግምት መጠቀማቸው ተዘግቧል፡፡ ከአቡ ሰዒድ አልኹድሪ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ ለጾመኛ ሰው ሚስቱን መሳምና ዋግምትን ፈቅደዋል›› ብለዋል፡፡ ዋግምት ስለሚያደክም የተጠላ ነው፡፡ አነስ ብን ማሊክ (ረዐ) ዋግምትን ለጾመኛ ሰው የተጠላ አድርጋችሁ ትወስዱ ነበርን? ተብለው ሲጠየቁ ‹‹የሚያደክም በመሆኑ እንጂ የተጠላ አድርገን አንወስደውም ነበር›› ብለዋል፡፡

    በቁስል ወይም በጥርስ መነቀል፣ወይም በነስርም ምክንያት ደም መፍሰሱ ችግር አይኖረውም፡፡ በመርፌ አማካይነት ለምርመራም ሆነ ለደም ልገሳ ደም መወሰድም ጾም አያበላሽም፡፡