የሐጅ (ዑምራ) አፈጻጸምና ተልቢያ

4870

      ኑሱክ

      የኑሱክ ትርጓሜ

የኑሱክ የቋንቋ ትርጉም

ዕባዳ ማለት ነው፡፡

የኑሱክ ሸሪዓዊ ትርጉም

ሐጅ ወይም ዑምራ የሚያደርግ ሰው በአንደበት የሚለውና በተግባር የሚፈጽመው ክንውን ነው፡፡

      የኑሱክ ንይያ

      እሕራም ማድረግ የፈለገ ሰው ገላውን ታጥቦ፣ንጽሕናውን አሟልቶ፣የእሕራም ልብስ ሲለብስና ወንድ ከተሰፉ ልብሶች ነጻ ሲሆን የሐጅን ወይም የዑምራን ኑሱክ ለመጀመር ንይያ ያደርጋል፡፡ ለማከናወን የነየተውን ኑሱክ በአንደበቱ ጭምር በመግለጽ ዑምራ አድርጎ ከዚያ በሐጅ ተመቱዕ ለማድረግ ከፈለገ ‹‹ለብ’በይከ አልሏሁም’መ ዑምረተን ሙተመት’ትዐን ብሃ እለል ሐጅ›› ይላል፣ወይም ‹‹ለብ’በይከ አል’ሏሁም’መ ዑምረተን›› ይላል፡፡

      ሐጅ ብቻ ነይቶ ከሆነ ደግሞ ‹‹ለብ’በይከ አልሏሁም’መ ሐጀን›› ማለት የተወደደ ነው፡፡ አነስ (ረዐ) የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹ለብበይከ ዑምረተን ወሐጃ›› (አላህ ሆይ! አቤቱ ለዑምራና ለሐጅ ጥሪህን ተቀብዬ አቤት ብያለሁ›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋልና፡፡ በአንደበቱ ምንም ሳይል ቀርቶ በልቡ ብቻ ንይያ ካደረገም በቂው ነው፡፡

      የኑሱክ ዓይነቶች

      1 - ተመት’ቱዕ (ዑምራ ከዚያ ሐጅ)

      ይህ በሐጅ ወራት ውስጥ ለዑምራ እሕራም አድርጎ ዑምራውን ከፈጸመና ከእሕራሙ ከወጣ በኋላ በዚያው ዓመት ለሐጅ እሕራም የሚያደርግበት ዓይነት ነው፡፡ በተመቱዕ ሐጅ የሚያደርግ ሰው መካ በሚደርስበት ጊዜ የዑምራ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ እነሱም ፡- ጠዋፍ፣ሰዕይ፣ጸጉር መላጨት ወይም ማሳጠር፣ከዚያም ከእሕራሙ በመውጣት መደበኛ ልብሱን መልበስ ሲሆኑ፤የዙልሕጃ ስምንተኛ ቀን ሲደርስ ለሐጅ እሕራም አድርጎ የሐጅ ተግባራትን ማከናወን ነው፡፡ በዚህ የተመቱዕ አፈጻጸም ዓይነት የተጠቀመ ሰው ሀድይ (በመካ የሚሰዋ እንስሳ) የማረድ ግዴታ አለበት፡፡

      2 - ቅራን (የሐጅና ዑምራ ጥምረት)

      ይህ አፈጻጸም ለሐጅና ዑምራ በጥምረት እሕራም ማድረግ ወይም ለዑምራ እሕራም አድርጎ ጠዋፉን ከመጀመሩ በፊት ሐጅን በዑምራው ላይ ማስገባት ነው፡፡ በቅራን አፈጻጸም ዓይነት ሐጅ የሚያደርግ ሰው የሐጅ ተግባራት በሙሉ እስኪሟሉ ድረስ በእሕራሙ የሚቀጥል ሲሆን በማጣመሩ ምክንያት ሀድይ የማረድ ግዴታ ይኖርበታል፡፡

      3 - እፍራድ (ሐጅን ብቻ በነጠላ)

      ይህ ሐጅ ብቻ በነጠላ የሚከናወንበት የአፈጻጸም ዓይነት ሲሆን፣በዚህ የተጠቀመ ሐጅ አድራጊ እስከ መጨረሻው የሐጅ ተግበራት ፍጻሜ ድረስ በእሕራሙ ይቀጥላል፡፡ የሀድይ ግዴታም የለበትም፡፡

      ከሁሉም ተመራጩ ኑሱክ (አፈጻጸም) ነቢዩ ﷺ ሶሓባን [ሙስሊም በዘገቡት የዓእሻ ሐዲስ መሰረት፡፡] በዚህ ያዘዟቸው በመሆኑ የተመቱዕ አፈጻጸም ነው፡፡ ከዚያ ቅራን ቀጥሎም እፍራድ ነው፡፡

      በሦስቱ ኑሱኮች (የሐጅ ሥርዓት አፈጻጸም) መካከል ያለው ልዩነት

  ተመት’ቱዕ ቅራን እፍራድ
ሐጅ ብቻ ዑምራና ሐጅ ዑምራ ከዚያ ሐጅ ሐጅ
አፈጻጸሙ ለሐጅ ብቻ አንድ ጊዜ እሕራም ያደርጋል፡፡ ለሐጅና ለዑምራ አንድ እሕራም ብቻ ያደርጋል፡፡ ሁለት ጊዜ እሕራም ያደርጋል፡፡ የመጀመሪያው ለዑምራ ነው፡፡ ዑምራውን ካደረገ በኋላ ከእሕራሙ ይወጣና ለሐጅ እሕራም ያደርጋል፡፡
እሕራም
እሕራም በእሕራም ጊዜ ‹‹ለብበይከ ሐጅጃን›› ይላል፡፡ በእሕራም ጊዜ ‹‹ለብበይከ ዑምረተን ወሐጅጃ›› ይላል፡፡ በመጀመሪያው እሕራም ጊዜ ‹‹ለብበይከ ዑምረተን›› ይላል፡፡ ከዚያም ለሐጅ እሕራም ሲያደርግ ‹‹ለብበይከ ሐጅጀን›› ይላል፣ወይም ‹‹ለብበይከ ዑምረተን ሙተመትትዐን ብሃ እለል ሐጅ›› ይላል፡፡
ተልቢያ ሀድይ (የሚሰዋ እንስሳ) ግዴታ አይሆንም፡፡ ሀድይ (የሚሰዋ እንስሳ) ግዴታ ይሆናል፡፡ ሀድይ (የሚሰዋ እንስሳ) ግዴታ ይሆናል፡፡
ሀድይ አንድ መደረግ ያለበት ጠዋፍ ሲኖረው እሱም የሐጅ ጠዋፍ ነው፡፡ አንድ መደረግ ያለበት ጠዋፍ ሲኖረው እሱም የሐጅ ጠዋፍ ነው፡፡ ሁለት ጠዋፎች ሲኖሩት አንደኛው ለዑምራ ሁለተኛው ለሐጅ፡፡
ጠዋፍ አንድ ሰዕይ ብቻ ሲኖረው እሱም የሐጅ ሰዕይ ነው፡፡ አንድ ሰዕይ ብቻ ሲኖረው እሱም የሐጅ ሰዕይ ነው፡፡ ሁለት ሰዕይ ሲኖሩት፣አንደኛው ለዑምራ ሁለተኛው ለሐጅ ነው፡፡

      ተልቢያ

      የተልቢያ ትርጓሜ

ተልቢያ

ተልቢያ ‹‹ለብ’በይከ አልሏሁምመ ለብ’በይከ፣ለብ’በይከ ላ ሸሪከ ለከ ለብ’በይከ፣እን’ነል ሐምደ ወን’ንዕመተ ለከ ወልሙልከ፣ላሸሪከ ለከ›› የሚለው የሙሕሪሙ ቃል ነው፡፡

    ይህም እብን ዑመር (ረዐ) እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ተልቢያ እንደዚህ ነበር [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] በሚለው ሐዲስ መሰረት ነው፡፡ ‹‹ለብ’በይከ አልሏሁም’መ ለብ’በይከ›› ማለት ትርጉሙ፡- ‹‹አላህ ሆይ! (የሐጅ) ጥሪህን ተቀብያለሁ አቤት! አሁንም አቤት!›› ማለት ነው፡፡

    ተልቢያ የአላህን ውዳሴና ምስጋናውን፣ተገዥነትንና ለትእዛዙ ምላሽ መስጠትን፣አንድነቱንና ተውሒዱን መግለጽን፣እንደዚሁም ከሽርክ ነጻ መሆንን አካቷል፡፡

    ተልቢያን የሚመለከት ድንጋጌ

    ተልቢያ ማለት ሱንና ሲሆን ወንድ ድምጹን ከፍ ሲያደርግበት ሴት ግን ፍትና እንዳይኖር ሲባል በዝግታ ድምጽ ትላለች፡፡

    የተልቢያ ወቅትና ቦታው

    እሕራም ያደረገ ሰው ከእሕራሙ በማስከተል ተልቢያ ማለት ይጀምራል፡፡ በጉዞው ላይ ተልቢያውን አብዝቶ ያስተጋባል፡፡

    ተልቢያ በብዙ ቦታዎች ላይ ሱናነቱ የጸና ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ፡-

    ወደ ከፍታ ቦታ ሲወጡ፣ወደ ሸለቆ ሲወርዱ፣የፈርድ ሶላት ከተሰገደ በኋላ፣ሲመሽና ሲነጋ፡፡

    በዑምራ ወቅት ከዕባን ከፊትለፊት ሲያይና ጥቁሩን ድንጋይ ሲሳለም ተልቢያን የሚያቋርጥ ሲሆን በሐጅ ጊዜ ደግሞ ዒድ ቀን የአልዐቀባን ጀምራ መወርወር ሲጀምር ያቋርጠዋል፡፡