ለሐጅ የመጣ ሰው ወይ ሙተመትዕ ነው፣ወይ ቃሪን ነው፣ወይ ደግሞ ሙፍሪድ ነው፡፡ ሙተመትዕ ከሆነ ዑምራን ካከናወነ በኋላ ከእሕራሙ ይወጣል፡፡ ቀሪንና ሙፍሪድ ግን በእሕራማቸው ይቀጥላሉ፡፡ የሐጅ ተግባራት ክንውን ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ እስከ አስራ ሦስተኛው ቀን መጨረሻ ድረስ የሚቀጥሉ ሲሆን ዝርዝሩ እንደሚከተለው ነው፡-
1 - በስምንተኛው ቀን ከዙህር በፊት እሕራም ማድረግ ሱና ሲሆን መካ ከሆነ ከመካ፣ሚና ከሆነም ከሚና ካለበት ቦታ ሆኖ ገላውን ታጥቦና ሽቶ ተቀብቶ የእሕራም ልብስ በመልበስ እሕራም ያደርጋል፡፡ ለሐጅ ተልቢያ እያለ እሕራም ሲያደርግ እንዲህ ይላል ፡- ‹‹ለብ’በይከ አልሏሁም’መ ሐጅጀን፣ለብ’በይከ አሏሁም’መ ለብ’በይከ፣ለብ’በይከ ላሸሪከ ለከ ለብ’በይከ፣እን’ነል ሐምደ ወን’ንዕመተ ለከ ወልሙልከ፣ላሸሪከ ለከ፡፡›› [በቡኻሪ ተዘገበ]
ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ጥሪህን ተቀብዬ እነሆ ለሐጅ አቤት ብያለሁ፡፡ አላህ ሆይ! ጥሪህን ተቀብዬ እነሆ አቤት ብያለሁ፤ጥሪህን ተቀብዬ እነሆ አቤት ብያለሁ፤አንተ ምንም ሸሪክ የለህምና ጥሪህን ተቀብዬ እነሆ አቤት ብያለሁ፤ሁሉም ምስጋና፣ሁሉም ጸጋ ሁሉም ንግሥና ያንተ ብቻ ነውና አቤት ብዬ ጥሪህን ተቀብያለሁ፣ አንተ ምንም ሸሪክ የሌለህ አንድ አምላክ ነህና፡፡›› ማለት ነው፡፡
2 - ከዚያ ወደ ሚና ያመራና ዙህር፣ዐስር፣መግሪብ፣ ዕሻእና የቀጣዩን ቀን ፈጅር እዚያ ይሰግዳል፡፡ እያንዳንዱን ሶላት በወቅቱ የሚሰግድ ሲሆን ባለ አራት ረክዓ ሶላቶችን ወደ ሁለት አሳጥሮ (በቀስር) ይሰግዳል፡፡ በዘጠነኛው ቀን ጸሐይ እስክትወጣ ድረስ ሚና ውስጥ የሚቆይ ሲሆን በዚህ ጊዜ ተልቢያን ደጋግሞና አብዝቶ ማስተጋባት ሱና ነው፡፡
1 - የዚህ ቀን ጸሐይ ስትወጣ ሐጅ አድራጊው ተልቢያ እያለ ወደ ዐረፋ ይጓዛል፡፡ ሱናው ከተቻለ ወደ ነሚራ በማምራት ጸሐይ ዘንበል እስክትል ድረስ እዚያ መቆየት ነው፡፡ ጸሐይ ዘንበል ብላ የዙህር ሶላት ወቅት ሲገባ የሙስሊሞች ኢማም ወይም እሱን የሚወክል ሰው፣ከሁኔታው ጋር አግባብነት ያለው ኹጥባ (ዲስኩር) ለሐጃጆች ማድረግ ሱና ነው፡፡ በኹጥባው ውስጥ ተውሒድን ያረጋገጣል፣የሐጅ ሕግጋትንና የሃይማኖቱን ዋና ዋና ጉዳዮች ለሐጃጆች ያሳውቃል፡፡
2 - ከዚያም ዙህርና ዐስርን አስቀድሞ በማጣመር (ጀምዑ ተቅዲም) እና በማሳጠር (በቀስር) ይሰግዳል፡፡ ሐጅ የሚያደርገው ሰው በዚህ ቀን ፊቱን ወደ ቅብላ በማዞር ዱዓእ ማብዛትና ለዚሁ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ፣መተናነስና ተገዥነቱን፣ደካማነቱንና መላ የለሽነቱን ለአላህ በመወትወት አጥብቆና ደጋግሞ ልመናውን ማቅረብ የተደነገገ ነው፡፡
ነቢዩ ﷺ ‹‹ከዱዓእ ሁሉ በላጩ የዐረፋ ቀን ዱዓእ ነው፤እኔ ካልኩትና ከኔ በፊት የነበሩ ነቢያትም ካሉት ሁሉ በላጩ ‹ላ እላሀ እል’ላል’ሏሁ ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ፣ለሁልሙልኩ ወለሁልሐምዱ፣ወሁወ ዐላ ኩል’ሊ ሸይእን ቀዲር› ማለት ነው፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
ለተላለፉ (መእሡር ለሆኑ) የዱዓእ ዓይነቶች ትኩረት መስጠትና ካልታዘዙና መሰረት ከሌላቸው የፈጠራ ዱዓእ ዓይነቶች መራቅና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ከቁርኣን የተመቸውን ያህል መቅራትና በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላትና ሰላም ማውረድን ማብዛት መልካም ነው፡፡
3 - ሐጅ አድራጊው የዘጠነኛው ቀን ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ ከዐረፋ ወደ ሙዝደሊፋ ያመራል፡፡ ጸሐይ ከመጥለቋ በፊት ምድረ ዐረፋን ለቆ መሄድ አይፈቀድም፡፡ ጸሐይ ከመጥለቋ በፊት የለቀቀ ሰው በሌሊት እንኳ ቢሆን ወደዚያ ይመለሳል፡፡ ያልተመለሰ ሰው እርድ ማቅረብ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ እርዱ አንድ ፍየል፣ወይም የግመል አንድ ሰባተኛ ወይም የበሬ አንድ ሰባተኛ ነው፡፡
1 - በምድረ ዐረፋ መቆም (ዉቁፍ) ማለት በዘጠነኛው ቀን በዐረፋ መገኘት ማለት ሲሆን፣ይህም በመቆም በመቀመጥ፣ተጋድሞም ሆነ በመጓጓዣ ላይ በመቀመጥም ሊሆን የሚችል እንጂ የግድ መቆም ማለት አይደለም፡፡
2 - በምድረ ዐረፋ መገኘት (ዉቁፍ) ከሐጅ ማእዘናት (አርካን) አንዱ ሩክን በመሆኑ ያለርሱ ሐጅ ትክክለኛ መሆን አይችልም፡፡ ዉቁፍ ያመለጠው ሰው ሐጅ አምልጦታል፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሐጅ ማለት ዐረፋ (ዉቁፍ) ነው፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡
3 - በምድረ ዐረፋ መገኘት (ዉቁፍ) ወቅት የሚጀምረው የዙልሕጃ ዘጠነኛ ቀን ጎህ መቅደድ (ፈጅር) ጀምሮ እስከ አስረኛው ቀን ጎህ መቅደድ ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለአፍታ እንኳ ቢሆን በዐረፋ የተገኘ ሰው ዉቁፍን ያገኘና ሐጁ ትክክለኛ የሆነ ሰው ነው፡፡
በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ዉቁፍ ያመለጠው ሰው ሐጁ ትክክለኛ አይሆንም፡ ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መርፉዕ ሐዲስ ‹‹ጎህ ከመቅደዱ (ከፈጅር) በፊት ለዐረፋ (ዉቁፍ) የደረሰ ሰው፣ለሐጅ ደርሷል፡፡›› [አልባኒ በሶሒሕ አልጃሚዕ ቁጥር 5995 ሶሒሕ ነው ብለውታል፡፡] ተብሏዋልና፡፡
4 - ምድረ ዐረፋ በሙሉ መቆሚያ (የውቁፍ ቦታ) ነው፡፡ ነቢዩﷺ ተራራ አጠገብ ወደ ላይ ሳይወጡ በቋጥኞቹ አቅራቢያ ፊታቸውን ወደ ቅብላ መልሰው በመቆም ፡- ‹‹እዚህ ቦታ ላይ ቆሜያለሁ፣ዐረፋ በሙሉም መቆሚያ ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከቆሙበት ቦታ ላይ መቆም ከተቻለ እሰየው፣ካልተመቸ በማንኛውም የምድረ ዐረፋ ቦታ ላይ ይቆማል፡፡
ወደ ዐረፋ ከመደረሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ባለው ሸለቆ፣የዑራና ሸለቆ በሚባለው ስፍራ መቆም ትክክለኛ አይሆንም፡፡ ወደ ተራራው አይወጣም፣በቋጥኞቹ ላይም አይቆምም፡ ምድረ ዐረፋ ከጥንትም የራሱ የተለየ ድንበር የተከለለለትና ምልክት የተደረገለት ሲሆን ባሁኑ ጊዜም አዳዲስና ድንበሮቹን ከሁሉም አቅጣጫ የሚያመለክቱ ትላልቅ ምልክቶች ተደርጎለታል፡፡
5 - ሐጅ አድራጊው የዚህን ዕለት ታላቅነትና ትሩፋቱን ማስታወስ ሲገባው፣አላህ ለባሮቹ ቸርነቱንና ችሮታውን የሚያፈስበት፣በመላእኮቹ ላይ በነሱ የሚፎክርበት፣ከእሳት የሚድኑትን የሚያበዛበት ክቡር ቀን መሆኑንም ማስተዋል ይኖርበታል፡፡ ነቢዩﷺ ‹‹ከዐረፋ ቀን ይበልጥ አላህ ባሪያውን በብዛት ከእሳት ነጻ የሚያወጣበት ቀን የለም፡፡ በእርግጥ (ወደ ባሮቹ) ይቀርባል፣ከዚያም ‹እነኚህ ምን ፈልገው ይሆን ? በማለት በመላእኮች ላይ በነሱ ይፎክራል፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡
ስለዚህም ሐጅ አድራጊው የዚህን ወርቃማና ክቡር ቀን ሰዓቶችን በመጠቀም ተውበቱን ማሳደስ፣ራሱን መመርመር ሲገባው፣ ዕለቱን በመዘዋወር፣ንግግርና ጭቅጭቅ በማብዛት
1 - ሓጁ ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ ከዐረፋ ወደ ሙዝደሊፋ ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎችን ላለማወክ ሲባል በጸጥታና በእርጋታ መንቀሳቀስ፣ተልቢያ እያሉና አላህን እየዘከሩ መጓዝ ሱና ነው፡፡
2 - ወደ ሙዝደሊፋ ሲደርስ ጓዙን ከመፍታቱ በፊት የመግሪብና የዕሻእ ሶላቶችን አንድ ላይ በማጠመር (በጀምዕ) ዕሻን በማሳጠር (በቀስር) በመስገድ ይጀምራል፡፡
3 - በዚህ ሌሊት አዳሩን በሙዝደሊፋ ማድረግ ግዴታ ሲሆን የሱብሕ ሶላትን ቶሎ ይሰግዳል፡፡ ዑዝር ካላቸው እንደ አቅመ ደካሞች፣ሴቶች፣ሕጻናትና ከነሱ ጋር ካሉት ወይም በሐጃጆች አገልግሎት ላይ ከተሰማሩት ውጭ ሌሎች ከፈጅር በፊት ከሙዝደሊፋ አይነቃነቁም፡፡ ምክንያት ያላቸው በሌሊቱ መጨረሻ ጨረቃ ከጠለቀች በኋላ ከሙዝደሊፋ መንቀሳቀስ ይፈቀድላቸዋል፡፡
4 - ሐጅ አድራጊው ሱብሕ ከሰገደ በኋላ ወደ መሽዐሩል ሐራም ዘንድ በመምጣት ፊቱን ወደ ቅብላ መልሶና እጆቹን ከፍ አድርጎ ዝክር ተክቢራና ዱዓእ ማብዛት፣ ንጋቱ በደንብ ወገግ ብሎ እስኪጠራ ድረስም በዚሁ መቀጠል የተወደደ ነው፡፡
በሙዝደሊፋ በየትኛውም ቦታ ላይ መቆም ይችላል፡፡ ነቢዩﷺ ‹‹እዚህ ቆሜያለሁ፣ጀምዕ በሙሉ ሙዝደሊፋ ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡ ጀምዕ መዝደሊፋ ለማለት ነው፡፡
5 - ሐጅ አድራጊው ሙዝደሊፋን ለቆ ሲወጣ ሰባት ጠጠሮችን የመጀመሪያውን ቀን ጅማር ብቻ ለመወርወር መልቀም የተወደደ ነው፡፡ ለተቀሩት ቀናት ውርወራ ግን ጠጠሮቹን ከሚና የሚወስድ ሲሆን ከየትኛውም ቦታ ጠጠሩን መውሰድ ይፈቀዳል፡፡
1 - የፈጅር ሶላት ሰግዶ ለጸሐይ መውጣት ጥቂት እስኪቀር ድረስ ራሱን ለዝክርና ለዱዓእ ነጻ ያደርጋል፡፡
2 - ጸሐይ ከመውጣቷ ጥቂት ቀደም ብሎ ሙዝደሊፋን ለቆ ወደ ሚና ይንቀሳቀሳል፡፡ በመንገዱ ላይ ተልቢያን አብዝቶ ያስተጋባል፡፡ ወደ ሙሐስሲር ሸለቆ በሚደርስበት ጊዜ ጉዞውን ያፋጥናል፡፡
ሙሐስሲር ወደ ሚና ከመድረስ በፊት በሙዝደሊፋና በሚና መካከል የሚገኝ ሸለቆ ነው፡፡ ወደ ሚና ሲደርስ የዒድ ቀን ተግባራትን ይፈጽማል፡፡ እነሱም ጠቅለል ባለ መልኩ ፡- የአልዐቀባን ጀምራ መወርወር፣መሥዋዕት ማረድ፣ጸጉር መላጨት ወይም ማሳጠር፣ጠዋፍና ሰዐይ ናቸው፡፡
3 - ሐጅ አድራጊው ወደ ሚና ሲደርስ በሚና አቅጣጫ በኩል የመጨረሻው ከመካ አቅጣጫ በኩል የመጀመሪያው ጀምራ ወደ ሆነው ወደ ጀምረቱል ዐቀባ ያመራል፡፡ ወደ ጀምራው ሲደርስ ተልቢያውን አቋርጦ ሰባት ጠጠሮችን ተራ በተራ አከታትሎ ይወረውራል፡፡ እያንዳንዱን ጠጠር አልሏሁ አክበር እያለ ይወረውራል፡፡
የውርወራው ተወዳጅ ወቅት ከዒድ ቀን ጎህ መቅደድ እስከ አስራ አንደኛው ቀን ጎህ መቅደድ ድረስ ያለው ጊዜ ሲሆን፣በዒድ ቀን ጎህ ከመቅደዱ በፊት በሌሊቱ መጨረሻ ላይ ቢወረውርም ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው ይሆናል፡፡
- አንድ ሙስሊም በጀመራት ውርወራ ጊዜም ሆነ በሌላው የሐጅ ተግባራት ክንዋኔ ላይ ሐጃጅ ወንድሞቹን ከማወክና ከማስቸገር መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡
- ሐጅ አድራጊው የሚወረውረው ጠጠር መወርወሪያ ገንዳው ላይ መውደቁን ማረጋገጥ አለበት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጠጠሩ የሚወረወረው ወደ ቆመው ምሰሶ ስለሚመስላቸው ጠጠሩ ወደ መወርወሪያው ገንዳ አይወድቅም፡፡ ሌሎች ደግሞ ከብዙ ርቀት ስለሚወረውሩ ወደ ቦታው አይደርስም፡፡ እንዲህ የሚያደርግ ሰው የውርወራን ግዴታ አልተወጣም፡፡
- አንድ ሙስሊም ትልቅ ድንጋይ ወይም ጫማን አውልቆ መወርወርን በመሳሰለ ሁኔታ ውርወራውን ከልኩ ከማሳለፍ መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡ ሱናው የጠጠሩ መጠን ከሽንብራ ፍሬ ትንሽ ከፍ የሚል መሆን ነው፡፡
ጃብር ብን ዐብደላህ (ረዐ) ባስተላለፉት ሐዲስ ውስጥ ‹‹ነቢዩﷺ ጀምራን የጣት ውርወራ ጠጠርን በመሰለ ጠጠር ሲወረውሩ አይቻለሁ [ሲሆን የጣት ውርወራ ጠጠር በሁለት አመልካች ጣቶች መካከል አድርገው የሚያፈናጥሩት ትንሽ ጠጠር ነው፡፡]፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] የሚል ተመልክቷል፡፡
- ጠጠሮቹን በሙሉ አንድ ጊዜ ከወረወረ እንደ አንድ ውርወራ ብቻ ይቆጠራል፡፡ መወርወር የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ጠጠሮቹን ወስዶ መወርወሪያው ላይ ቢያኖር ትክክለኛ አይሆንም፡፡
4 - ወንድ የራስ ጸጉሩን ይላጫል፣ወይም ሙሉ በሙሉ ያሳጥራል፤መላጨት በላጭ ነው፡፡ ሴት ግን አንድ የጣት አንጓ ያህል ብቻ ጸጉሯን ታሳጥራለች፡፡
5 - ወደ መካ በመውረድ ጠዋፍ አልእፋዷ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጠዋፍ ረመልም ሆነ እድጥባዕ (ትከሻን እያንቀሳቀሱ በፈጣን እርምጃ መጓዝና የቀኝ ትከሻን ማራቆት) የለበትም፡፡ ከጠዋፉ በኋላ ሁለት ረክዓ ይሰግዳል፡፡ በዚህ ጠዋፍ ተመራጩ ከውርወራና ከመላጨት በኋላ የእሕራም ልብሱን አውልቆ የተለመደ ልብሱን መልበስና ሽቶ መቀባት ነው፡፡
ዓእሻ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ እሕራም ሲያደርጉ ለእሕራማቸው፣ከእሕራም ሲወጡም በቤቱ (በከዕባ) ዙሪያ ጠዋፍ ከማድረጋቸው በፊት ሽቶ እቀባቸው ነበር፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡
6 - የጠዋፉ ወቅት ከዒድ ቀን ጎህ መቅደድ በኋላ የሚጀምር ሲሆን፣ከሙዝደለፋ አስቀድመው ለለቀቁ ደካሞች ከጎህ መቅደድ በፊት በሌሊቱ መጨረሻ ላይ ማድረግም ይቻላል፡፡ ከዒድ ቀን ማዘግየትም የሚፈቀድ ቢሆንም ተመራጭ ግን አይደሰለም፡፡
7 - በተመቱዕ ሐጅ ያደረገ ሰው ከጠዋፉል እፋዷ በኋላ በሰፋና መርዋ መካከል ሰዕይ ማድረግ ሲገባው፣ በእፍራድና በቅራን ሐጅ ያደረገ ሰው ከጠዋፉል ቁዱም በኋላ ሰዕይ አድርጎ የነበረ ከሆነ ከጠዋፉል እፋዷ በኋላ ሰዕይ ማድረግ አያስፈልገውም፡፡
ሐጅ አድራጊው ጠዋፉል እፋዷንና የሚመለከተው ከሆነ ሰዕይን ካከናወነ የዒድ ቀን ተግባሮችን ያጠናቀቀ በመሆኑ የአስራ አንደኛውን ቀን ሌሊት እዚያ ለማደር ወደ ሚና መመለስ ይኖርበታል፡፡
የዒድ ቀን ተግባራትን ከላይ በሰፈረው ቅደም ተከተል መሰረት ማከናወን ሱና ነው፡፡ ይህም በመጀመሪያ ውርወራ፣ከዚያ መሥዋዕት ማረድ፣ቀጥሎ መላጨት፣ ከዚያ ጠዋፍ፣ከዚያ በመቀጠል ሰዕይ ማድረግ ያለበት ሰው ሰዕይ ማድረግ ሲሆን፣ነቢዩ ﷺ የፈቀዱ ስለሆነ አንዱን ከሌላው ማስቀደምም ይቻላል፡፡ ስለዚህም መጀመሪያ ተላጭቶ ከዚያ ጠጠር ቢወረውር ትክክለኛ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
መጀመሪያ መሠዋዕት አርዶ ከዚያ ጠዋፍ ቢያደርግና ቀጥሎ ውርውራ ወዘተ. ቢፈጽምም ትክክለኛ ይሆናል፡፡ ነቢዩﷺ በዚህ ቀን ስለ ቅደም ተከተል ሲጠየቁ ይሉ የነበረው ‹‹አድርገው ችግር የለውም፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ማለት እንጂ ሌላ አልነበረምና፡፡
የመጀመሪያውና ሁለተኛው ተሐል›ሉል (ከእሕራም ሁኔታ መውጣት)
የመጀመሪያው ተሐል›ሉል - በእሕራም ምክንያት በሙሕሪሙ ላይ ታግደው የነበሩ ነገሮች ሁሉ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም የቅደመ ግንኙነት አካላዊ ንኪኪ ወይም የጋብቻ ውል ማሰር ብቻ ሲቀሩ ሁሉም እገዳዎች የሚፈቀዱበት ሁኔታ ነው፡፡ የመጀመሪያው ተሐል’ሉል ከሚከተሉት ውስጥ ሁለቱን በመፈጸም ይገኛል ፡- ጀምረቱል ዐቀባን መወርወር፣መላጨት ወይም ማሳጠር፣ጠዋፍ ማድረግና ሰዕይ ማድረግ ያለበት ሰው ሰዕይ ማድረግ፡፡
ሁለተኛው ተሐል’ሉል - በእሕራም ምክንያት በሙሕሪሙ ላይ ታግደው የነበሩ ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ የሚፈቀዱበት ከእሕራም የመውጣት ሁኔታ ነው፡፡ ሁለተኛው ተሐል’ሉል ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉ በመፈጸም እውን ይሆናል፡፡
የሀድይ እንስሳ ማረድ ከተሐል’ሉል ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ሀድይ የማረዱን ተግባር አስከ አስራ አንደኛው ቀን አዘግይቶ የተቀሩትን የዒድ ቀን ተግባራት ካሟላ ባያርድ እንኳ ከእሕራም ሁኔታ መውጣት ይችላል፡፡
አይ’ያም አት’ተሸሪቅ ከዒድ ቀጥለው ያሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት ሲሆኑ እነሱም ፡- የዙልሕጃ ወር አስራ አንደኛው፣አስራ ሁለተኛውና አስራ ሦስተኛው ቀናት ናቸው፡፡ በዚህ የተሰየሙት የኡድሕይያ ሥጋ ተቆራርጦና ተዘልዝሎ በጸሐይ ይደርቅባቸው ስለነበረ ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ ስለነዚህ ሦስቱ ቀናት ሲናገሩ ‹‹ንቁ! እነኚህ ቀናት የመብላት የመጠጣትና የአላህ ዝክር ቀናት ናቸው፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡
በአስራ አንደኛው ቀን ዋዜማ ሌሊት ሚና ማደር ግዴታ ነው፡፡ በአስራ አንደኛው ቀን ፀሐይ ከእኩለ ቀን ካለፈች በኋላ በሦስቱ ጀምራዎች በያንዳንዳቸው ሰባት ሰባት ጠጠሮች [ጀምራዎች በሚና ጫፍ ላይ የሚገኙ በያንዳንዱ መሀል የቆመ ግዙፍ ምሰሶ ያላቸው ሦስት ገንዳዎች (ገበቴዎች) ሲሆኑ፣የመጀመሪያው ትንሹ ጀምራ፣ሁለተኛው መካከለኛው ጀምራ፣ ሦስተኛው በሚና ጠረፍ በመካ አቅጣጫ የሚገኘው ትልቁ (አልዐቀባ) ጀምራ ናቸው፡፡] ይወረወራሉ፡፡
የጠጠር አወራወር
በመጀመሪያው ጀምራ ይጀምርና ሰባት ጠጠሮችን አንዱን ከሌላው በማስከተል ይወረውራል፡ ከያንዳንዱ ጠጠር ውርወራ ጋር ተክቢራ ይላል፡፡ የሚወረወሩ ጠጠሮች የግድ ገንዳው ላይ መውደቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚያ ትንሽ ራመድ ብሎ ይቆምና እጆቹን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ዱዓእ ያደርጋል፡፡
በመቀጠልም በመካከለኛው ጀምራ እንደ መጀመሪያው ሰባት ጠጠሮችን ይወረውርና እጆቹን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ዱዓእ ያደርጋል፡፡
ከዚያም በአልዐቀባ ጀምራ ሰባት ጠጠሮችን በተመሳሳይ ሁኔታ ይወረውራል፡፡ ከዚህ በኋላ ለዱዓእ አይቆምም፡፡
በአስራ ሁለተኛው ቀንም ሚና ማደር ግዴታ ነው፡፡ በዕለቱ ፀሐይ ዘንበል ካለች በኋላ ሦስቱንም ጀምራዎች በአስራ አንደኛው ቀን በወረወረበት ሁኔታ ይወረውራል፡፡
በዚህ ቀን መቸኮል ከፈለገ ጠጠሮቹን ወርውሮ ከፀሐይ መጥለቅ በፊት ሚናን ለቆ ይሄዳል፡፡ ሚና ውስጥ እያለ ፀሐይ ከጠለቀች ግን ሚና ውስጥ አድሮ አስራ ሦስተኛውን ቀን የጠጠር ውርወራውን ማከናወን ይኖርበታል፡፡
ይህም ተጨማሪ ሰናይ ተግባር ይሆነዋል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹የተቻኮለ ሰው በርሱ ላይ ኃጢአት የለበትም፤የቆየም ሰው በርሱ ላይ ኃጢአት የለበትም፤(ይህም) አላህን ለፈራ ሰው ነው፤›› [አል-በቀራህ:203]
ማለት የተፈለገው የቸኮለ ሰው ከአያም አትተሸሪቅ አሰራ አንደኛውንና አስራ ሁለተኛውን፣የቆየው ደግሞ አስራ ሦስተኛውንም ያሟላል ማለት ነው፡፡
በአስራ ሦስተኛው ቀን ከቀትር በኋላ ቀደም ሲል በአስራ አንደኛው ቀን ባደረገው ሁኔታ ሦስቱን ጀምራዎች ይወረውራል:፡ የውርወራ ወቅቱም ከዚህ ቀን ፀሐይ መጥለቅ ጋር ያበቃል፡፡
ሐጅ አድራጊው የጠጠር ውርወራውን ወደሚቀጥለው የውርወራ ቀንና እስከ መጨረሻው የውርወራ ቀን ድረስም ማዘግየት ይፈቀድለታል፡፡ ሦስቱም የተሸሪቅ ቀናት የውርወራ ቀናት ናቸውና፡፡
የመጀመሪያውን ቀን ውርወራ በሦስቱም ጀምራዎች በመወርወር መጀመር፤ከትንሹ ጀምራ ሲመለስ የሚቀጥለውን ቀን ውርወራ እየወረወረ ሁሉንም ይወረውራል፡፡ ወርውራው ከቀትር በኋላ ብቻ መከናወን ይኖርበታል፡፡
ሐጅ አድራጊው ከመካ መውጣት ከፈለገ የመሰናበቻ ጠዋፍ በከዕባ ዙሪያ ያደርጋል፡፡ ጠዋፉል ወዳዕ ከሐጅ ዋጅቦች አንዱ ሲሆን ከጠዋፉ በኋላ ሰዕይ አይኖርም፡፡ የወር አበባና የወሊድ ደም ካለባቸው ሴቶች ላይ ግዴታነቱ ይነሳል፡፡
ጠዋፍ አልእፋዷን እስከ ጠዋፍ አልወዳዕ ማዘግየት የተፈቀደ ነው፡፡ በላጩ ግን አለማዘግየቱ ነው፡፡ ኒይያው ለጠዋፍ አልእፋዷ ከመሆን ሸርጥ ጋር ከጠዋፉ በኋላ ሰዕይ ቢያደርግ እንኳ ከጠዋፉል ውዳዕ በጠዋፉል እፋዷ ብቻ መብቃቃት ይቻላል፡፡
- ከጠዋፍ ጀርባ ያለው ጥበብ :
ከጠዋፍ፣ከሰዕይ እና ከጠጠር ውርወራ ጀርባ ያለው ጥበብ (ሕክማ) የየየአላህን ዝክርና ውዳሴውን ሕያው ማድረግ ነው፡፡ ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹በቤቱ (በከዕባ) ዙሪያና በሶፋና መርዋ መካከል ጦዋፍ የተደረገው፣የጠጠሮች ውርወራም የአላህን ዝክር ቋሚ ለማድረግ ነው፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
1 - ዑምራ አድራጊው ወደ ሚቃት ሲደርስ ገላውን ታጥቦ ሽቶ ተቀባብቶና የእሕራም ልብስ ለብሶ ‹‹ለብበይከ ዑምረተን›› በማለት ኒይያ ያደርጋል፡፡
2 - ‹‹ለብ’በይከ አል’ሏሁም’መ ለብ’በይከ፣ለብ’በይከ ላ ሸሪከ ለከ ለብ’በይከ፣እን’ነል ሐምደ ወን’ንዕመተ ለከ ወልሙልከ፣ላሸሪከ ለከ›› [በቡኻሪ የተዘገበ] በማለት ተልቢያ ማስተጋባት ይጀምራል፡፡ ቤቱን (ከዕባን) በዓይኑ እስኪያይና ሐጀረል አስወድን እስኪሳለም ድረስ ተልቢያ ማስተጋባቱን ይቀጥልበታል፡፡
3 - ወደ ተከበረው መስጊድ (መስጅድ አልሐራም) ሄዶ የቀኝ እግሩን በማስቀደም የመስጊድ መግቢያ ዱዓእ አድርጎ ይገባል፡፡
4 - ተልቢያውን ያቋርጥና በከዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ማድረግ በመጀመር ጥቁሩን ድንጋይ በመሳለም ከተቻለ በመሳም ካልተቻለ በእጁ እያመላከተ ፡- ‹‹ብስምል’ላህ ወል’ሏሁ አክበር፣አሏሁም’መ ኢማነን ብከ፣ወተስዲቀን ብክታብከ፣ ወወፋአን ብዐህድከ፣ወእት’ትባዐን ልሱን’ነት ነቢይከ መሐመድን ﷺ›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ይላል፡፡
ትርጉሙ፡- ‹‹በአላህ ስም (እጀምራለሁ)፣አላህ ከሁሉም በላይ ኃያል ነው፣አላህ ሆይ! በአንተ በማመን፣የመጽሐፍህንም (የቁርኣንን) እውነተኛነት በማረጋገጥ፣ቃል ክዳንህንም ለመሙላትና የነቢይህን የሙሐመድን ﷺ ሱና በመከተል ነው (ይህን ዕባዳ የምፈጽመው)፡፡›› ማለት ነው፡፡
5 - ቤቱን በስተግራው በማድረግ ከሐጀሩል አስወድ ተጀምሮ በሐጀሩል አስወድ የሚያበቃ ሰባት ዙር በከዕባ ዙሪያ ይዞራል (ጠዋፍ ያደርጋል)፡፡
6 - በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዙሮች በፈጣን አካሄድ (በረመል) መዞር ሱና ሲሆን፣በሁሉም ዙሮች የቀኝ ትከሻውን ገልጦ ፎጣውን ከብብቱ ሥር በማሳለፍ ጫፎቹን በግራ ትከሻው ላይ ማድረግም (እድጥባዕ) ሱና ነው፡፡
7 - በጠዋፍ ጊዜ የፈለገውን ዱዓእ ያደርጋል፡ በሩክን አልየማኒ ትይዩ ሲደርስ ይሳለመውና ተክቢራ ይላል፡፡ መሳለም ካልቻለ ግን በእጁ አያመለክትም፣ተክቢራም አይልም፡፡
በሩክን አልየማኒና በሐጀሩል አስወድ መካከል የሚከተለውን ይላል፡- ‹‹ረብ’በና ኣትና ፊድ’ዱንያ ሐሰነተን ወፊል ኣኽረት ሐሰነተን ወቅና ዐዛበን’ናር፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ትርጉሙ
‹‹ጌታችን ሆይ! በቅርቢቱ ዓለም ሕይወት መልካሙን ነገር ስጠን፣በወዲያኛው የመጨረሻ ሕይወትም መልካሙን ስጠን፡፡›› ማለት ነው፡፡
8 - ሰባተኛውን ዙር ጠዋፍ ሲያበቃ ትከሻውን በፎጣው ይሸፍንና ክፍት ማድረጉን ይተዋል፡፡ እድጥባዕ በዑምራ ጠዋፍ ወይም በጠዋፉል ቁዱም ብቻ እንጂ ከዚህ ውጭ ሱንና አይደለምና፡፡
በመቀጠል ወደ ኢብራሂም መቆሚያ (መቃሙ ኢብራሂም) ያመራና ከተቻለ ከመቆሚያው ኋላ ሁለት ረክዓ ሶላት በመጀመሪያው ከፋቲሓ በኋላ ሱረቱል ካፊሩን በሁለተኛው ሱረቱል እኽላስን በመቅራት ይሰግዳል፡፡ ከመቃሙ ጀርባ መስገድ ካልተቻለው በፈለገበት ቦታ ላይ ይሰግዳል፡
1 - አንድ ሙስሊም ሐጀሩል አስወድን ለመሳለም ወይም ለመሳም ብሎ ጠዋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን መጋፋትና ማስቸገር የለበትም፡፡ በሌሎች ላይ ችግር የሚፈጥር ከሆነ በጠዋፍ ላይ ፈጣን አካሄድን (ረመል) መተው ይኖርበታል፡፡
2 - በጠዋፉ ወቅት የተመቸውን ዓይነት ዱዓእ ያደርጋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሰው ውጭ ጠዋፍ የተለየ ዝክር የለውም፡፡ በጠዋፉ ጊዜ ቁርኣን ቢቀራ ችግር የለውም፡፡
3 - እድጥባዕ በዑምራ ወይም በቁዱም (የመድረሻ) ጠዋፍ ሁሉም ዙሮች ውስጥ ሱንና ነው፡፡
4 - ሴት በጠዋፍ ጊዜ ጌጦቿን ከማሳየትና የሽቶ ጠረን ለሌሎች እንዳይደርስ፣ድምጽዋን በዝክርና በዱዓእ ከፍ ከማድረግ መጠንቀቅ ይኖርባታል፡፡
9 - ከዚያ ወደ መርዋ ያመራና አጠገቡ ሲደርስ ከቁርኣን የሚከተለውን የአላህ ቃል ይቀራል፡- ‹‹ሶፋና መርዋ ከአላህ (ትእዛዝ መፈጸሚያ) ምልክቶች ናቸው፤ቤቱን (ከዕባን) በሐጅ ወይም በዑምራ ሥራ የጎበኘ ሰው፣በሁለቱ (መካከል) በመመላለሱ በርሱ ላይ ኃጢአት የለበትም፤መልካምን ሥራ በፈቃደኛነት የሠራ ሰው (አላህ ይመነዳዋል)፤አላህ አመስጋኝ ዐዋቂ ነውና፡፡›› [አል-በቀራህ:158]
10 - ወደ ሶፋ ይወጣና ፊቱን ወደ ቅብላ አዙሮ አጆቹን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ‹‹ላ እላሀ እል’ላል’ሏሁ ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ፣ለሁልሙልኩ ወለሁልሐምዱ፣ወሁወ ዐላ ኩል’ሊ ሸይእን ቀዲር፡ ኣይቡነ ታእቡነ፣ዓብዱነ፣ሳጅዱነ፣ልረብ’ብና ሓሚዱነ፤ሰደቀል’ሏሁ ወዕደሁ፣ወነሰረ ዐብደሁ፣ወአህዘመል አሕዛበ ወሕደህ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]
በማለት የአላህን ያወድሳል፣ያመሰግናል፡፡ ከዚያም ዱዓእ ያደርግና ዝክሩን እንደገና ይደግመዋል፡፡ አሁንም ዱዓእ ያደርግና ዝክሩን ለሦስተኛ ጊዜ ይደግማል፡፡
11 - ከሶፋ ጉብታ ወርዶ ወደ መርዋ ያመራል፡፡ በሁለቱ አረንጓዴ ምልክቶች [አረንጓዴ ምልክቶቹ በሶፋና መርዋ መካከል ሲመላለሱ እሜት ሃጀር በፍጥነት የተጓዙበትን ቦታ የሚያለክቱ ናቸው፡፡] መካከል በፍጥነት ተጉዞ ወደ መርዋ በመድረስ ሶፋ ላይ የፈጸመውን ሁሉ እዚህም ይፈጽማል፡፡
12 - በሶፋና መርዋ መካከል ሰባት ዙር በፍጥነት ይመላለሳል፡፡ (ሰዕይ መሄጃው አንድ ዙር፣መመለሻውም አንድ ዙር ነው)፡፡ ለሰዕይ የጦሃራ መኖርና ሰዕይና ጠዋፍን ማከታተል ሱና ሲሆን፣ያለ ጦሃራ ቢደረግም ሰዕዩ ትክክለኛ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
13 - ሰዕይ ካደረገ በኋላ ግልጽ ሆኖ በሚታይ ሁኔታ ጸጉሩን ያሳጥራል፤ሴት ከጸጉሯ ከሁሉም አቅጣጫ የጣት አንጓ ያህል ታሳጥራለች፡፡ ለወንድ በላጩ መላጨት ነው፡፡
ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹አላህ ሆይ! ለተላጪዎች ምሕረት አድርግላቸው›› ሲሉ (ሶሓባ) ለአሳጣረዎችም? አሏቸውና ‹‹አላህ ሆይ! ለተላጪዎች ምሕረት አድርግላቸው›› አሉ፡ ለአሳጣሪዎችም? ሲሏቸው (በሦስተኛው ላይ) ‹‹ለአሳጣሪዎችም›› [በቡኻሪ የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡፡
በተመቱዕ ተጠቅሞ ከሆነ ጸጉር ሊያድግበት የሚችል በቂ ጊዜ ስለማይኖር መላጨቱን ለሐጅ አቆይቶ ማሳጠሩ በላጭ ይሆናል፡፡
14 - ከዚያም ከዑምራ እሕራም ተሐል’ሉል አድርጎ ነጻ ይሆናል፡፡ በዚህም ዑምራው ይጠናቀቃል፡፡
ሴት በጠዋፍና በሰዕይ በጠዋፉ በፍጥነት የማትጓዝና በሰዕይም በሁለቱ አረንጓዴ አምዶች መካከል በፈጣን እርምጃ የማትመላለስ ከመሆኗ በስተቀር በሌላው ክንውን ልክ እንደ ወንዱ ነች፡፡ ጸጉሯንም የጣት አንጓ ያህል ከሁሉም አቅጣጫ ታሳጥራለች እንጂ አትላጭም፡፡