በጫማዎች፣የግር ሹራቦች፣ በተጎዳ አካል ላይ የታሰሩና

4527

      አንደኛ፡ሽፍን ጫማ (ኹፍፍ) የእግር ሹራብ (ካልሲ)

      የሽፍን ጫማ (ኹፍ) እና የእግር ሹራብ ትርጓሜ

ሽፍን ጫማ (ኹፍፍ)

ከቆዳ የተሰራ የእግር መልበሻ

የእግር ሹራብ (ካልሲ)

ከጥጥና ከመሳሰሉት የተሰራ የእግር መልበሻ

    በጫማዎችና በእግር ሹራቦች ላይ ማበስን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች

    በጫማዎችና በእግር ሹራቦች ላይ ማበስ በበርካታ ሐዲሶች መሰረት ተደንግጓል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አነስ ብን ማሊክ (ረዐ) ጫማዎችን ስለማበስ ተጠይቀው ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ (በጫማዎቹ ላይ) ያብሱ ነበር፡፡›› [በቡኻሪና በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ጫማዎችንና የግር ሹራቦችን ለማበስ መሟላት ያለባቸው ሸርጦች

    1 - ከተሟላ ጦሃራ በኋላ የተለበሱ መሆን ፡- ሙጊራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹በአንድ ጉዞ ላይ ከነቢዩ ﷺ በርኩበና ጫማዎቻቸውን ላወልቅላቸው ጎንበስ ስል፣ተዋቸው በጦሃራ ላይ ሆኜ (ካጠብኳቸው በኋላ) ነውና ያስገባኋቸው አሉና በጫማዎቹ ላይ አበሱ፡፡›› ብለዋል፡፡›› [በቡኻሪና በሙስሊም የተዘገበ]

    2 - ሁለቱን እግሮች እስከ ቁርጭምጭሚቶች ድረስ የሚሸፍኑ መሆን፤ከቁርጭምጭሚቶች በታች የሚቀሩ ጫማዎች ከሆኑ አይታበሱም፡

    3 - ንጹሕ (ጣህር) ከሆኑ ነገሮች የተሰሩ መሆን፡፡

    4 - ሐላልና የተፈቀዱ መሆን፣ለወንዶች ከሆነ ሐርን የመሳሰለ ነገር አለመሆን፡፡

    5 - ማበሱ ለዚህ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆን፤ነቢዩ ለማበስ የተወሰነ የጊዜ ገደብ (ለነዋሪ ሰው አንድ ቀንና አንድ ሌሊት፣ለመንገደኛ ሦስት ቀናት) አስቀምጠዋልና ይህንን መተላለፍ ኤፈቀድም፡፡

    6 - ማበሱ ለከፍተኛው ሐደሥ ሳይሆን ለመለስተኛው ሐደሥ ንጽሕና (ለዉዱእ) ብቻ መሆን፡፡ ሰፍዋን ብን ዐስሳል (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹በጉዞ ላይ ስንሆን የአላህ መልእክተኛ ﷺ በጫማዎቻችን ላይ እንድናብስና ገላን ለመታጠብ ግዴታ (ለጀናባ) ብቻ እንጅ በዓይነ ምድርም ሆነ በሽንት ለሦስት ቀናት እንዳናወልቃቸው ያዙን ነበር፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ህም ማለት ገላን የመታጠብ ግዴታ (ጀናባ) ያለበት ሰው እግሮቹን ከጫማዎቹ አውጥቶ አጥቦ የማስገባት ግዴታ አለበት ማለት ነው፡፡

    በጫማዎችና በእግር ሹራቦች ላይ እንዴት እንደሚታሰብ

    የላይኛው የጫማ ክፍል በውሃ በራሱ አጆች ከእግር ጣቶች አንስቶ ወደ እስከ ቅልጥም ድረስ አንድ ጊዜ ታበሳል፡፡ የቀኙ እግር በቀኙ የግራውም በግራው እጅ ታበሳል፡፡

    የጫማው ሶልም ሆነ ተረከዝ አይታበስም፡፡ ዐሊይ (ረዐ) ‹‹ሃይማኖት (ዲን) በሰው አስተያየት የሚሆን ቢሆን ኖሮ ከጫማ የላይኛው ክፍል ይልቅ ሶሉን ማበስ ይበልጥ የተገባ በሆነ ነበር፤የአላህ መልክተኛ ﷺ በጫማዎቻው የላይኛው ክፍል ላይ ሲያብሱ ነው ያየሁት፡፡›› [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በጫማዎችና በግር ሹራቦች ላይ የማበሻ ጊዜ ገደብ

    ለነዋሪ ሰው አንድ ቀንና አንድ ሌሊት፣ለመንገደኛ ሦስት ቀናት ከሌሊቶቻቸው ጋር ነው፡፡

    ለዚህ ማስረጃው ቀጥሎ ያለው የዐሊይ (ረዐ) ቃል ነው፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ ለመንገደኛ ሰው ሦስት ቀናት ከሌሊቶቻቸው ጋር፣ለነዋሪ ደግሞ አንድ ቀንና ሌሊት እንዲሆን አድርገዋል፡፡›› [በነሳኢ የተዘገበ]

    ማበሱ የሚቆይበት የጊዜ ገደብ ስሌት

    ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ከሐደሥ በኋላ ከሚደረገው ከመጀመሪያው ማበስ አንስቶ ነው፡፡ ሹራቦቹን ጦሃራ ላይ ሆኖ ከለበሰ በኋላ ጦሃራው ፈርሶ ለመጀመሪያ ጊዜ ካበሰ፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው አንድ ቀንና አንድ ሌሊት (ሃያ አራት ሰዓት) የሚሰላው፡፡

    ለዚህ ምሳሌው ፡- አንድ ሰው ወዱእ አድርጎና እግሮቹን ከታጠበ በኋላ የእግር ሹራቦቹን ለብሶ የፈጅር (የሱብሕ) ሶላት ሰገደ፡፡ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ዉዱኡ ፈረሰ፡፡ አምስት ሰዓት ሲደርስ ዱሓ ለመስገድ ዉዱእ አደረጎ ሹራቦቹ ላይ አበሰ፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀጣ ቀን አምስት ሰዓት ድረስ ሸራቦቹን ለብሶ ማበሱን መቀጠል ይፈቀድለታል፡፡

    ይህ ለነዋሪ ሲሆን ለመንገደኛ ግን ሦስት ቀናት ከሌሊቶቻቸው ጋር ነው፡፡

    በጫማዎችና በግር ሹራቦች ላይ ማበስን (መስሕን) የሚያበላሹ ነገሮች

    1 - የማበሱ የጊዜ ገደብ ማለፍ፡፡

    2 - ሁለቱን ሹራቦች ወይም አንዳቸውን ማውለቅ፡፡

    3 - ከፍተኛው ሐደሥ (ገላን የመታጠብ ግዴታ) መከሰት፡ ሰፍዋን ብን ዐስሳል (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹በጉዞ ላይ ስንሆን የአላህ መልእክተኛ ﷺ በጫማዎቻችን ላይ እንድናብስና ገላን ለመታጠብ ግዴታ (ለጀናባ) ብቻ እንጅ በዓይነ ምድርም ሆነ በሽንት ለሦስት ቀናት እንዳናወልቃቸው ያዙን ነበር፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በሁለቱም እጆች ማበስ
    የጫማን ሶል ማበስ
    ተረከዝን ማበስ
    ካልሲን ማውለቅ መስሑን (ማበስን) ያበላሻል

    በስብራት መደገፊያ፣በቁስል ማሸጊያ ፋሻና በተለጣፊ ፕላስተር ላይ ማበሰ

    በተጎዳ አካል ላይ የሚታሰር ድጋፍ፣የፋሻና የፕላስትር ትርጓሜ

    የስብራት መደገፊያ (ጀቢራህ)

    በስብራት ቦታ ላይ ለድጋፍ የሚታሰር እንደ ጄሶና እንጨት ያለ ነገር ነው፡፡

    ማሸጊያ ፋሻ

    በቁስል ወይም በቃጠሎና በመሳሰለው ምክንያት በተጎዳ ቦታ ላይ ለሕክምና የሚጠመጠም ጨርቅና የመሳሰለ ነገር ነው፡፡

    ፕላስተር

    በቁስልና በመሳሰሉት ላይ ለሕክምና ሲባል የሚለጠፍ ነገር ነው፡፡

    በስብራት መደገፊያ (ጀቢራህ) ላይ ማበስ የተደነገገ ስለመሆኑ ማስረጃ

    ጃቢር (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹ለጉዞ ወጥተን እያለ ከመካከላችን አንዱን ድንጋይ መቶት ራሱን ፈነከተው፡፡ ይህ ሰው በሕልም ወሲብ ምክንያት ገላን የመታጠብ ግዴታ አጋጠመውና ተየሙም ማድረግ የሚያስፈቅድለት ነገር እንዳለ ጠየቃቸው፤በውሃ መታጠብ እስከ ቻልክ ድረስ የሚያስፈቅድልህ ነገር መኖሩን አናውቅም አሉትና በውሃ ታጥቦ ሞተ፡፡ ወደ ነቢዩ ተመልሰው ሲመጡ የሆነውን ነገሯቸው፡፡ ነቢዩም አላህ ይግደላቸውና ገደሉት፤ያላዋቂ መድኃኒት መጠየቅ ነውና ካላወቁ አይጠይቁም ኖራል፡፡ ተየሙም አድርጎ ቁስሉን በጨርቅ አስሮ (ጠምጥሞ) በላዩ ላይ በማበስ ቀሪ አካሉን መታጠብ ብቻ ይበቃው ነበር፡፡›› [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በስብራት መደገፊያ (ጀቢራህ) ላይ ለማበስ መሟላት ለባቸው ቅድመ ግዴታዎች

    1 - የቁስል መጠቅለያ ፋሸም ሆነ የስብራት መደገፊያ እነዚህን ነገሮች በአግባቡ ለማድረግና ለሕክምናው ከሚያስፈልገው ቦታና ከዙሪያው ማለፍ የለበትም፡፡

    2 - ጀቢራም ሆነ የቁስል መሸፈኛ ፋሻን ከጦሃራ በኋላ ማድረግ ግዴታ (ሸርጥ) አይደለም፡፡ አስፈላጊ ሆነው እስከተገኙ ድረስም በከፍተኛውና በመለስተኛው ሐደስ ንጽሕና (በገላ ትጥበትና በዉዱእ) ጊዜ ማበስ ይፈቀዳል፤የተወሰነ የጊዜ ገደብም የላቸውም፡፡ አስፈላጊነታቸው ሲያበቃ መውለቅና በጦሃራ ወቅት አካሉ መታጠብ ይኖርበታል፡፡

    3 - እንደ ፕላስትርና ፋሻ ያሉና ተነስተው መመለስ የሚችሉትን በተመለከተ፡-

    ሀ- ጉዳት የማያስከትል ወይም የመፈወሻ ጊዜውን የማያዘገይ ከሆነ አንስቶ ከስሩ ያለውን ካጠቡ በኋላ ወደ ነበረበት መመለስ ነው፡፡

    ለ- ጉዳት ሳያመጣ ወይም የመዳኛ ጊዜውን ሳያዘገይ አውልቆ ከስሩ ያለውን ማጠብ የማይመች ሆኖ ሲገኝ ግን ያሉበትን አካል በሚታጠብበት ጊዜ በላያቸው ላይ ያብሳል፡፡

    በጀቢራና በፋሻ ላይ እንዴት እንደሚታበስ

    በፋሻ ላይ እንዴት እንደሚታበስ
    በጀቢራ ላይ እንዴት እንደሚታበስ
    በፕላስተር ላይ ይታበሳል