ሐጅን የሚመለከት የትውውቅ መቅድም

5332

      መካ በታሪክና በገሃዱ ሁኔታ

መካ

ሸለቆ የሚል ትርጉም ካለው የሴማዊ ቋንቋ ‹‹በከ›› ቃል የተገኘ ስም ነው፡፡

      የመካ ስም በካ በሚል ቃል በቀጣዩ የአላህ ቃል ውስጥ ተመልክቷል፡- ‹‹ለሰዎች (መጸለያ) መጀመሪያ የተኖረው ቤት ብሩክና ለዓለማት ሁሉ መምሪያ ሲኾን፣ያ በበካህ (መካ) ያለው ነው፡፡›› [ኣል-ዒምራን:96]

      የመካ ታሪክ የመጀመሪያ ነዋሪዎቿ ወደ ሆኑት ነቢዩ ኢብራሂምና ልጃቸው ነቢዩ እስማዒል ዘመን ከልደት በፊት ወደ አስራ ዘጠነኛው ምእተ ዓመት ይመልሰናል፡፡ አላህ ስለ ኢብራሂም ሲናገር ፡- ‹‹ጌታችን ሆይ! አዝመራ በሌለው ሸለቆ ውስጥ በተከበረው ቤትህ (በከዕባ) አጠገብ ከዘሮቼ አስቀመጥሁ፤ጌታችን ሆይ! ሶላትን ያቋቁሙ ዘንድ (አስቀመጥኳቸው)፤ከሰዎችም ልቦችን ወደነሱ የሚናፍቁ አድርግ፤ያመሰግኑህም ዘንድ ከፍሬዎች ስጣቸው፡፡›› [ኢብራሂም:37]

      ብሏል፡፡ ከእናታቸው ከሃጀር ውሃና ምግብ ሲሟጠጥ በነቢዩ እስማዒል እግሮች ስር የዘምዘም ውሃ በነቢዩ ኢብራሂም ዱዓእ መነጨ፡፡

      ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዐረብ ጎሳዎች ወደ ውሃው ምንጭ መጉረፍ ጀመሩና ደረቁ ሸለቆ ሕይወት መዝራት ጀመረ፡

      በአከባቢው የሚሰፍሩ የዐረብ ጎሳዎች ወደ ቦታው መጉረፋቸውን በመቀጠል እየበዙ መጡ፡፡ ጎሳዎቹን የመምራትና የማስተዳደርር ኃላፊነት ወደ ቁረይሽ ጎሳ እጅ ገባ፡፡ በተከበረችው የመካ ከተማና በመላው ዓለም የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ታላቅ የለውጥ ተጽእኖ የነበራቸው ነቢዩ ሙሐመድ ﷺ እስከ መጡበት ጊዜ ድረስ የቁረይሽ ጎሳ መሪነቱ እንደያዘ ቆየ፡፡

      ሙሐመድ ﷺ በመካ በነቢይነት ከአላህ ወደ መላው የሰው ልጆች ተላኩ፡፡ ከዕባ የሙስሊሞች ቅብላ (በሶላት ጊዜ ፊታቸውን የሚያዞሩበት አቅጣጫ) ሆነ፡፡ መካም የእስላማዊው ደዕዋ (ጥሪ) ማእከል ሆነች፡፡ የመካ ነዋሪዎች ግን ከሰዎች ሁሉ ከጥሪው ያፈነገጡ ከሁሉም በላይ ተከታቹን ያሰቃዩ ስለነበር፣ሙስሊሞች ወደ መዲና ለመሰደድ ተገደው የእስላም መንግሥት እዚያ ተመሰረተ፡፡ በኋላ ነቢዩ ﷺ በድል አድራጊነት ወደ መካ ተመለሱ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መካ ትልቅ እስላማዊት አገር ሆናለች፡፡

      የተከበረችው የመካ ከተማና በተለይም የመካው ሐረም ከሙስሊሞች ኸሊፋዎችና መሪዎች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ተችሯታል፡፡ ሁሉም ከተማዋን በማሳደግ፣ በማስፋፋትና የእስላም ብርሃን ወደ መላው ዓለም የሚፈነጥቅበት ማእከል ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

      የመካ ትሩፋት

      1 - ወደ ሐረም የገባ ሰው ሰላም የሚያገኝ መሆኑ

      አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹የገባውም ሰው ጸጥተኛ ይኾናል፤›› [ኣል-ዒምራን:97] ይህም ወደ መካ ሐረም የገባ ሰው አይነካም፣የደህንነት ዋስትና ያገኛል ማለት ነው፡፡

      2 - ሐሳዊ መሲሕም (ደጃል) ሆነ ወረርሽኝ በሽታ ወደ ሐረሙ የማይገባ መሆኑ

      ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹መዲናና መካ በመላእካ የተከበቡ ናቸው፣በያንዳንዱ መንገድ ላይ መልአክ አለ፤ደጃልም ሆነ ወረርሽኝ በሽታ አይገባባቸውም፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      3 - በተከበረው የመካ መስጊድ የሚሰገደው ሶላት ሌላ ቦታ ከሚሰገደው በመቶ ሺህ የሚበልጥ መሆኑ

      ከጃቢር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹በመስጅድ አልሐራም የሚሰገድ አንድ ሶላት ሌላ ቦታ ከሚሰገደው መቶ ሺህ ሶላት በላጭ ነው፡፡›› [በእብን ማጃህ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      4 - ከቦታዎች ሁሉ አላህ ዘንድ ይበልጥ የተወደደ መሆኑ

      የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹በአላህ እምላለሁ (መካ) ከአላህ መሬት ሁሉ በላጭ ነሽ፤በአላህ ዘንድም ከአላህ ምድር ሁሉ ይበልጥ ተወዳጅ ነሽ፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      የተከበረችው መካ

      መካና ሐረምን የሚመለከቱ ልዩ ድንጋጌዎች

      1 - በተግባር ፈጸመውም አልፈጸመ ሐረም ውስጥ ክፉ ለመስራት ባሰበ ሰው ላይ ብርቱ ማስጠንቀቂያ የተላለፈ መሆኑ

      አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹በርሱም ውስጥ (ከትክክለኛ መንገድ) በመዘንበል (በእልሓድ) በዳይ ኾኖ (ማንኛውንም ነገር) የሚፈልግ ሰው፣ከአሳማሚ ቅጣት እናቀምሰዋለን፡፡›› [አልሐጅ፡25]

      እልሓድ ወይም ከቀጥተኛ መንገድ መውጣት ሁሉም ዓይነት የአላህ ትእዛዝ ጥሰትን የሚያካትት ነው፡፡ ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ‹‹አላህ ዘንድ ከሁሉም ይበልጥ የተጠሉት ሰዎች ሦስት ናቸው›› ብለው ከነዚህ ውስጥ ‹‹በሐረም ውስጥ የአላህ ትእዛዝን ጥሰት የሚፈጽም ሰው (ሙልሕድ)›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ጠቅሰዋል፡፡

      2 - በርሱ ውስጥ መዋጋትና ደም ማፋሰስ ሐራም መሆኑ

      አላህ ፡- ‹‹ቤቱንም (ከዕባን) ለሰዎች መመለሻና ጸጥተኛ ባደረግን ጊዜ (አስታውስ፤›› [አል-በቀራህ:125]

      ብሏል፡፡ ወደ መካ የገባ ሰው የሰላምና የደህንነት ዋስትና ያገኛል፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ﷺ ‹‹መካ ውስጥ የጦር መሳሪያን መያዝ ለማንኛችሁም አይፈቀድም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ያሉት፡፡

      በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹መካን አላህ ነው የታፈረ ክልል አድርጎ የከለለው፣ሰዎች አይደሉም የከለሉት፤ሰለዚህም በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሰው፣በውስጡ ደም ማፋሰስም ሆነ ዛፍ መቁረጥ አይፈቀድለትም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      ውጊያና ደም ማፍሰስ

      3 - ለካፍሮችና ለሙሽሪኮች ወደ ሐረም መግባት የተከለከለ መሆኑ

      አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው፤ከዘህም ዓመታቸው (ዘጠነኛው ዓመተ ህጅሪያ) በኋላ፣የተከበረውን መስጊድ አይቅረቡ፤›› [አል-ተውባህ:28]

      ነቢዩ ﷺ በሚና እያሉ ፡- ‹‹ከዚህ ዓመት በኋላ ሙሽሪክ የሆነ ሰው ሐጅ እንዳያደርግና ራቆቱን የሆነ ሰውም ጠዋፍ እንዳያደርግ (በከዕባ ዙሪያ እንዳይዞር)›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ተብሎ እንዲታወጅ አዘዋል፡፡

      4 - ሐረም ውስጥ አውሬ ማደን፣ዛፍ መቁረጥና ለበጎ ሥራ ካልሆነ በስተቀር የወደ ዕቃን መውሰድ ሐራም መሆኑ

      ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹መካን አላህ የማይፈቀድ የታፈረ ክልል አድርጎታል፣ከኔ በፊትም ሆነ ከኔ በኋላ ለማንም አልፈቀደም፤ከቀኑ ለአንድ ሰዓት ለኔ ብቻ ነው የተፈቀደው፤ስለሆነም እርጥብ ተክሉ አይቀነጠስም፣ዛፉ አይቆረጥም፣የአደን አውሬው እንዲበረግግ አይደረግም፣ለሰናይ ተግባር ካልሆነ በስተቀር ወድቆ የተገኘ እቃም አይወሰድም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      የሐጅ ሥርዓት ክንውኖች (መሻዕር)

የሐጅ ሥርዓት ክንውኖች (መሻዕር)

የሐጅ ዕባዳ መለያ የሆኑ ግልጽ ምልክቶቹ ናቸው፡፡

    1 - ዐረፋት

    ዐረፋ ብዘው ዐረፋት ሲሆን፣በዚህ የተሰየመው ኣደምና ሐዋእ እዚያ ቦታ ላይ ስለ ተዋወቁ ወይም ሰዎች ኃጢአቶቻቸውን አውቀው የሚቀበሉበት በመሆኑ ነው፡፡

    ዐረፋ ከሐረም ክልል ውጭ የሚገኝ የሐጅ ሥርዓት ማከናወኛ አንዱ ሥፍራ (መሽዐር) ነው፡፡ ከመስጅድ አልሐራም በምሥራቃዊ ደቡብ በኩል በ22 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ጠቅላላ የቆዳ ስፋቱ 10.4 እስኩዌር ኪሜ ነው፡፡ በወርሐ ዙልሕጃ ዘጠነኛው ቀን ሐጃጆች ይሰባሰቡበታል፡፡

    ዐረፋት

    የነሚራ መስጊድ

    ነሚራ ከመስጊዱ በስተ ምዕራብ የሚገኝ ተራራ ሲሆን የነሚራ መስጊድ በስሙ ይጠራል፡፡

    ነቢዩ ﷺ በዑረና ሸለቆ ሰፍረው እዚያ ኹጥባ ያደረጉ ሲሆን ነቢዩ ﷺ ኹጥባ ባደረጉበትና ሶላት በሰገዱበት ቦታ ላይ በዐባሳውያን ሥርወ ኽላፋ ዘመን መጀመሪያ ላይ በዑረና ሸለቆ ውስጥ መስጊዱ ተሰራ፡፡ በሰዑዲይ ዘመን ማስፋፊያና ግንባታ ተካሂዶለት ስፋቱ ከ110 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ሐጃጆች በወርሐ ዙልሕጃ ዘጠነኛው ቀን ይሰባሰቡበታል፡፡

    የነሚራ መስጊድ

    የሰኸራት (የቋጥኞች) መስጊድ

    ዐረፋት ውስጥ ከረሕማ ኮረብታ ሥር ወደ ላይ ሲወጣ በስተቀኝ የአላህ መልእክተኛ ﷺ በዐረፋ ዋዜማ በአጠገባቸው ቆመው የነበረ ትላልቅ ቋጥኞች ባሉበት ቦታ የሚገኝ መስጊድ ሲሆን፣በወርሐ ዙልሕጃ ዘጠነኛው ቀን ሐጃጆች ይሰባሰቡበታል፡፡

    የሰኸራት መስጊድ

    የረሕማ ተራራ

    የትላልቅ ድንጋዮች ክምር የሆነ ትንሽ ተራራ ሲሆን ከመካ በስተ ምሥራቅ በ20 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ አናቱ ለጥ ያለ የተስተካከለና ዙሪያው 640 ሜትር ሲሆን በወርሐ ዙልሕጃ ዘጠነኛው ቀን ሐጃጆች ይሰባሰቡበታል፡፡

    የረሕማ ተራራ

    2 - ሚና

    ሚና ተብሎ የተሰየመው በመሠዋዕት ምክንያት ደም የሚፈስበት በመሆኑ ነው፡፡ ሚና ከመስጅድ አልሐራም በስተ ሰሜን ምሥራቅ በ7 ኪሜ ርቀት ላይ መካና ሙዝደሊፋ መካከል ይገኛል፡፡ ሐጃጆች ለቸኮለ የዙልሕጃን 11ኛና 12ኛውን ሌሊት፣ለሚዘገይ 13ኛውንም ሌሊት የየሚያድሩበት ሲሆን፣መስጅድ አልኸይፍና ሦስቱ ጀመራት (የጠጠር መወርወሪያ ገንዳዎች) ያሉበት በሐረም ክልል ውስጥ የሚገኝ የሐጅ ሥርዓት ማከናወኛ ቦታ (መሽዐር) ነው፡፡

    ሚና

    አልጀመራት

    ጀምራህ ብዙው ጀመራት ሲሆን፣ትንሽ ጠጠር ማለት ነው፡፡ በሚና የሚገኙት ሦስቱ የሐጅ ሥርዓት ማከናወኛ ጀመራት፣ጀምረት አስሱግራ (ትንሹ ጀምራ)፣ጀምረት አልውስጧ (መካከለኛው ጀምራ) እና ጀምረት አልዐቀባ ናቸው፡፡ ጀመራት ሰይጣን የተገለጠበትንና ነቢዩ ኢብራሂም ሰይጣኑን የወገሩበትን ቦታ ለማመልከት በሦስት ጉድጓዶች (ገንዳዎች) ውስጥ የቆሙ የድንጋይ ምሰሶዎች ናቸው፡፡ በጀምረት አልውስጧ እና በጀምረት አልዐቀባ መካከል ያለው ርቀት 247 ሜትር ያህል ሲሆን፣በውስጧ እና በሱግሯ መካከል ያለው ርቀት ደግሞ 200 ሜትር ያህል ነው፡፡

    መስጊድ አልኸይፍ

    ከሚና ተራራ ደቡባዊ ግርጌ ጀምረት አስሱግራ አቅራቢያ ይገኛል፡፡

    የአልኸይፍ መስጊድ

    3 - ሙዝደሊፋ

    ሙዝደሊፋ በሚና እና በዐረፋ መካከል የሚገኝ ስፍራ ሲሆን ሐጃጆች በምድረ ዐረፋ ከቆሙ በኋላ የሚያድሩበት ቦታ ነው፡፡ መሀል ሙዝደሊፋ ውስጥ መሽዐሩል ሐራም ሲገኝ ለሐጃጆች እዚያ ቆመው ዱዓእ ማድረግ፣አላህን ማወደስና ማመስገን የተወደደ ነው፡፡ ሙዝደሊፋ ከዙልሕጃ ዘጠነኛ ቀን ጸሐይ መጥለቅ በኋላ ከዐረፋ በሚወርዱበት ጊዜ ሐጃጆች የሚያድሩበት ቦታ ነው፡፡

    ሙዝደሊፋ

    4 - መስጅድ አልሐራም

    የተከበረው ከዕባ

    የተከበረው ከዕባ የባለ ስድስት ጎን (ኪዩቢክ) ቅርጽ ያለው ቤት ነው፡፡

    የእስማዒል ጎጆ

    ይህ ቁረይሾች ቤቱን ለመሥራት በፈለጉ ጊዜ የግንባታ ወጭ አጥሯቸው ሰይሟላ የቀረ የቤቱ አንድ አካል መሆኑን ለማመልከት ቅስት ግድገዳ ያደረጉበት የቤቱ ሰሜናዊ ክፍል ነው፡፡ ስያሜው የተለምዶ ስያሜ እንጂ ሸሪዓዊ ስያሜ አይደለም፡፡

    ሐጀሩል አስወድ (ጥቁሩ ድንጋይ)

    ጥቁሩ ድንጋይ በከዕባ ምዕራባዊ ክፍል ከተከበረው ከዕባ በር በስተ ግራ የሚገኝ ሲሆን፣ከጀነት የሆነ ድንጋይ ነው፡፡ ሐጀሩል አስወድ ተሰባብሮ የተምር ፍሬዎች መጠን ካላቸው በጣም ትናንሽ ከሆኑ ስምንት ጠጠሮች በስተቀር የቀረ ነገር የለም፡፡

    ሩክን አልየማኒ (የየመን ማእዘን)

    የከዕባ ደቡባዊ ምዕራብ ማእዘን ሲሆን፣በየመን አቅጣጫ በኩል በመሆኑ ሩክን አልየማኒ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሩክን አልየማኒን ልዩ የሚያደርገው ኢብራሂምና እስማዒል ከፍ ባደረጉት የመጀመሪያው የቤቱ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑ ነው፡፡

    ሙልተዘም

    ሙልተዘም በሐጀሩል አስወድና በከዕባ በር መካከል ያለው ክፍል ሲሆን ስፋቱ ሁለት ሜትር ያህል ነው፡፡ ዱዓእ ተቀባይነት የሚያገኝበት ቦታ በመሆኑ በሁለት ጉንጮች፣በደረት፣በሁለት ክንዶችና በመዳፎች ወደሱ ከመለጠፍ ጋር ዱዓእ ማድረግ ሱና ነው፡፡

    የተከበረው ከዕባ
    ሩክን አልየማኒ
    ጥቁሩ ድንጋይ