ሌሎች የዘካት ዓይነቶች

3055

      የዕዳዎች ዘካት

ዕዳ

ተበዳሪው ለባለ ገንዘቡ መክፈል ያለበት ገንዘብ ነው፡፡

      ሌሎች በዘካ ከፋዩ ላይ ያላቸውን ዕዳ ዘካትን የሚመለከት ድንጋጌ

      መጠኑ ንሷብ የሚሞላ ወይም ከዚያ ያነሰ ዕዳ ያለበት ሰው ዘካ ግዴታ አይሆንበትም፡፡ ዕዳው የዘካት መክፈያውን መጠን የማያጎድል ከሆነ በዕዳው ልክ ከገንዘቡ ይቀነስና በቀሪው ዘካት ይከፈልበታል፡፡

      ምሳሌ፡ አንድ ግለሰብ 10000 ዶላር ቢኖረውና ግምቱ 10000 ዶላር የሆነ ዕዳ ቢኖርበት ዕዳው ንሳቡን ሙሉ በሙሉ የሚውጠው በመሆኑ የዘካ ግዴታ የለበትም፡፡ ዕዳው 9950 ዶላር ከሆነም ቀሪው ንሷብ ስለማይሞላ ዘካት አይኖርበትም፡፡ ዕዳው 4000 ዶላር ቢሆን ግን ካለው ገንዘብ ይቀነስና በቀሪው 6000 ዶላር ዘካ ይከፈልበታል፡

      ተበዳሪ ገንዘቡን ለንግድ ሥራ ብቻ ላይጠቀም ይችላል። በተወሰኑ ዓመታት ተከፍሎ በሚያልቅ ክፍያ መኖሪያ ቤት በዱቤ ሊገዛ ወይም በተበደረው ገንዘብ በብዙ ሚሊዮን ለሚገመት ትልቅ ፕሮጅክት የሚውሉ መሳሪያዎችን ሊገዛ ይችላል። ሌላው ነጋዴ የፋብሪካውን የማምረት አቅም ለማሳደግ በሚሊዮኖች የሚገመት የማስፋፊያ ሥራ ለማከናወን ሊወስን ይችላል። እነዚህ የእንቬስትመንት ብድሮች የዘካት ክፍያን ሊያስቀሩ ይችላሉ ወይ?

      ይህ ማለት መጠኑ የበዛ የዘካት ገቢን ድሆችን ማሳጣት ማለት ነው። ከዚህም አልፎ አብዛኞቹ የዘመኑ ባለሀብቶች ዘካት መክፈል ላይኖርባቸው ነው ማለትም ያስችላል። ይህን ጉዳይ በማስመልከት ዙልቀዕዳ 1409 ዓመተ ህጅራ ሰኔ 1989 ዓመተ ልደት ኩዌት ውስጥ የተካሄደውና በዘመኑ የዘካ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ሁለተኛ ጉባኤ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል ፡-

      አንደኛ - ተበዳሪው ከመሰረታዊ ፍላጎቶቹ የሚተርፉ ቋሚ ንብረቶች ከሌሉት ለንግድ ሥራ የሚውሉ ብድሮች በሙሉ ዘካት ከሚከፈልበት ገንዘብ ይቀነሳሉ፡፡

      ሀለተኛ - ተበዳሪው ከብድሮቹ አንጻር መሆን የሚችሉ ከመሰረታዊ ፍላጎቶቹ የሚበልጡ ቋሚ ንብረቶች ከሌሉት፣ ለእንዱስትሪ ፕሮጅክቶች የሚውሉ የኢንቬስትመንት ብድሮች በሙሉ ዘካት ከሚከፈልበት ገንዘብ ይቀነሳሉ፡፡ እነዚህ የኢንቭስትመንት ብድሮች በጊዜ ገደብ የሚከፈሉ በሚሆኑበት ሁኔታ ዘካት ከሚከፈልበት ገንዘብ ላይ ለብድሩ የሚፈለገው ዓመታዊ ክፍያ ብቻ ይቀነሳል፡፡ ከዕዳው አንጻር የሚሆን እቃ ከኖረና ዕዳውን የሚሸፍን ከሆነ ግን ዕዳው ዘካት ከሚከፈልበት ገንዘብ አይቀነስም፡፡ የማይሸፍን ከሆነ የቀረው ዘካት ከሚከፈልበት ገንዘብ ላይ ይቀነሳል፡፡

      ሦስተኛ - በተለምዶ በተራዘመ ጊዜ የሚከፈሉ የመኖሪያ ቤት መግዣ ዕዳዎች ተበዳሪው በእጁ የቀረውን ገንዘብ ንሷብ ከሞላ ዓመታዊውን የዕዳ ክፍያ ከቀነሰ በኋላ ዘካት ይከፍልበታል፡፡

      ዘካ ከፋዩ በሌሎች ላይ ያለውን ብድር ዘካት የሚመለከት ድንጋጌ

      1 - በከሰረ ሰው ላይ ያለ፣አቅም እያለው ላለመክፈል በሚያጓትት ሀብታም፣ወይም መበደሩን ጭራሽ በካደ ሰው ላይ ያለውን ብድር የመሳሰለ መሰብሰቡ የሚያስቸግር ብድር፣ በየዓመቱ የዘካት ክፍያ የለበትም፡፡ ዘካው መከፈል ያለበት ብድሩ ሲመለስለት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

      2 - አቅም ባለውና በማያጓትት ተበዳሪ ላይ ያለውን የመሳሰለ ለመመሰብሰብ የማያስቸግር ብደር ከሆነ ግን ገንዘቡ እርሱ ዘንድ እንዳለ ስለሚቆጠር በየዓመቱ ዘካውን የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡

      የቦንድ ሰነዶች ዘካት

ቦንድ

ቦንድ ሰነዱን ያመነጨው ወገን ሰነዱን ለያዘው ወገን የክፍያ ቀነ ገደቡ ሲደርስ በሰነዱ የሰፈረውን የገንዘብ መጠን ስምምነት ከተደረገበት የጥቅም መቶኛ ጋር እዲከፍል የሚያስገድድ የምስክር ወረቀት ነው፡፡

      ይህ ግልጽና ሐራም የሆነ አራጣ (ሪባ) ነው፡፡ ወለድን የሚጨምር ዕዳ ነውና፡፡ ግልጽ ከሆነ ወለድ ጋር የሚሰጡ ብድሮች በመሆናቸው ሰነዶች በአጠቃላይ መልካቸው የማይፈቀዱ ናቸው፡፡ በሰነዶች የሚገለገል ሰው ተውበት አድርጎ ወደ አላህ መመለስ ይኖርበታል፡፡

      የቦንድ ዘካትንና መጠኑን የሚመለከት ድንጋጌ

      የቦንድ ሰነዶች ለገዟቸው ወገኖች የሚከፈል በቀነ ቀጠሮ የተገደቡ ብድሮች ናቸው፡፡ ስለዚህም የቦንድ ዘካት በብድር ዘካት ድንጋጌ ውስጥ የሚካተት በመሆኑ ብድሩ በራሱ ወይም ከሌላው የባለንብረቱ ገንዘብና የንግድ ሸቀጥ ጋር ተጣምሮ የዘካ መክፈያ ንሷብ ከደረሰ ዓመት ሲሞላው የዘካት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ የሚከፈለውም የአንድ አስረኛ ሩብ (2.5%) ነው፡፡ ሰነዶቹ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንጂ ሊዘረዘሩ የማይችሉ ከሆነ በሚዘረዘሩበት ጊዜ ላለፉት ዓመታት ጭምር ዘካ ይከፈልባቸዋል፡፡

      የአገልግሎት ማብቂያ ክፍያ የጡረታ ክፍያና የጡረታ አበል ዘካት

የአገልግሎት ዘመን ማብቂያ ክፍያ

ይህ በሕጎችና ደንቦች መሰረት አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ተሟልቶ ሲገኝ፣በተቀጣሪው የአገልግሎት ዘመን መጨረሻ ላይ ቀጣሪው ለተቀጣሪው ሊከፍለው የሚገባ ገንዘብ ነው፡፡

የጡረታ ክፍያ

የጡረታ አበል ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ተሟልተው በማይገኙበት ሁኔታ፣መንግሥት ወይም የሚመለከታቸው ድርጅቶች በማህበራዊ ዋስትና ሕግ ሥር ለታቀፈ ሠራተኛ ወይም ተቀጣሪ የሚሰጥ የገንዘብ ክፍያ ነው፡፡

የጡረታ አበል

አንድ ሰራተኛ ወይም ተቀጣሪ የአገልግሎት ዘመኑ ካበቃ በኋላ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ተሟልቶ ሲገኝ በሕጎችና ደንቦች መሰረት ከመንግሥት ወይም ከሚመለከተው ድርጅት በየወሩ ሊከፈለው የሚገባ የገንዘብ ክፍያ ነው፡፡

      የጡረታ አበልን የሚመለከት ድንጋጌ

      ተቀጣሪው ወይም ሠራተኛው በአገልግሎት ዘመኑ ውስጥ ለዘካት ግዴታ ሸርጥ የሆነው የሙሉ ባለቤትነት መብት በጡረታ ተቆራጩ ላይ ስለሌለው፣ገንዘቡን ማውጣትም ሆነ ማንቀሳቀስ የማይችል በመሆኑ በዚህ ገንዘብ ላይ የዘካት ግዴታ የለበትም፡፡

      የዚህን ገንዘብ መጠን ወስኖ ለተቀጣሪው ወይም ለሠራተኛው በአንዴ ወይም በየጊዘው በተወሰነ ወቅት እንዲሰጠው ውሳኔ ሲተላለፍ ብቻ ባለቤትነቱ የተሟላ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ በተቀበለው ገንዘብ ላይ ዘካት ይከፍላል፡፡ በመጀመሪያው የዘካት ጉባኤ እንደ ተወሰነው የተቀበለውን ገንዘብ ከንሷብና ከዓመት መሙላት አኳያ ከሌላ ገንዘቡ ጋር በማጣመር ዘካ ይከፍልበታል፡፡ [ዶ/ር ሰላሕ አስሳዊ፣ የዘመኑ ፍቅህ ነክ ጉዳዮች ፣ገጽ 61]

      የክራይ ገቢዎች ዘካት

የክራይ ገቢዎች

ሪል እስቴት፣መኪና እና የማምረቻ ፋብሪካዎችን የመሳሰለ፣ በራሱ የሚነገድበት ሳይሆን ባለበት ሁኔታ ተከራይቶ ገቢ ለማስገኘት የተዘጋጀ የሚከራይ ሁሉም ዐይነት ንብረት ነው፡፡

      እነዚህ ንብረቶች በሚያስገኙት የክራይ ገቢ እንጂ በራሳቸው በንብረቶቹ ላይ የዘካት ክፍያ ግዴታ እንደ ሌለባቸው ሁሉም የዕውቀት ባለቤቶች በሙሉ ድምጽ ተስማምተዋል፡፡ ባለቤቱ የሚያስገኙትን ገቢ ከንሷብና ከዓመት መሙላት አኳያ፣ ከሌላ ንብረቱ፣ካለው ጥሬ ገንዘብና የንግድ ሸቀጦች ጋር በማጣመር ልክ እንደ ገንዘብ ዘካት ሁሉ የአንድ አስረኛ ሩብ (2.5%) ዘካ ይከፍልበታል፡፡ [ዶ/ር ሰላሕ አስሳዊ፣ የዘመኑ ፍቅህ ነክ ጉዳዮች ፣ገጽ 60]

      የቀጣሪ የኢንሹራንስ ክፍያ ዘካት

ኢንሹራንስ

መድህን ሰጭው ለዋስትና ሲባል ከደንበኛው ተቀብሎ ሳይከፍለው ይዞት የሚያቆየው ገንዘብ ነው፡፡

      የርሱ ንብረት ባለመሆኑና ለዘካት ክፍያ ቅድመ ሁኔታ የሆነው የሙሉ ባለቤትነት መብት ገና ያልተረጋገጠ በመሆኑ ዘካው በዋስትና ሰጭው ላይ ግዴታ አይሆንም፡፡ [ዶ/ር ሰላሕ አስሳዊ፣ የዘመኑ ፍቅህ ነክ ጉዳዮች ፣ገጽ 58]

      የአእምሯዊ ንብረት ዘካት

አእምሯዊ ንብረት

የሳይንሳዊና ስነ ጽሑፋዊ መብትን የመሳሰለ የአእምሮ ወጤት፣ወይም እንደ እንዱስትሪ ምርት የፓተንት መብት ያለ፣ወይም እንደ የንግድ ስምና የንግድ ምልክት ያለ ነጋዴው ደንበኞችን ለመሳብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የመሳሰለ፣አንድ ግለሰብ ቁሳዊ ባልሆነ ነገር ላይ የሚኖረው ሕሊናዊ ሥልጣን ነው፡፡

      የአእምሯዊ ንብረት ዘካትን የሚመለከት ድንጋጌ

      የአእምሯዊ ንብረት መብት በተለምዶ በሸሪዓው ተቀባይነት ያለው፣የገንዘብነት ዋጋ ያለውና በሸሪዓዊ ማእቀፎች መሰረት መፈጸም የሚችል ሆኗል፡፡ በመሆኑም በሸሪዓው የተከበረ መብት ከመሆኑ አንጻር ሊጣስና ሊደፈር የማይችል መብት ነው፡፡ የዘካት ሸርጥን የማያሟላ በመሆኑ የዘካት ግዴታ በራሱ በደራሲነትና በፈልሳፊነት መብቱ ላይ አይኖርም፡፡ መብቱ ወደ ገንዘብነት ሲለወጥ ግን በሚያስገኘው ገቢ ላይ የገንዘብ ዘካት ይከፈልበታል [ዶ/ር ሰላሕ አስሳዊ፣ የዘመኑ ፍቅህ ነክ ጉዳዮች ፣ገጽ 58]

      የቅጥር የደሞዝና የነጻ ሞያዎች (ፍሪላንስ) ትርፍ ዘካት

የቅጥር ክፍያዎችና ደሞዝ

አንድ ሠራተኛ ለሠራው ሥራ የሚከፈለው ገንዘብ ነው፡፡

      ዘካውን የሚመለከት ድንጋጌ

      የዚህ ገንዘብ ዘካት የሚከፈለው ገንዘቡን ሲቀበሉ በየክፍያው ወቅት ሳይሆን፣ግለሰቡ ባለውና ዘካት ከሚከፈልባቸው የተቀሩ ንብረቶች ጋር ከንሷብና ዓመት ከመሙላት አንጻር ሁሉንም አንድ ላይ በማጣመር ንሷብ ከሞላ በኋላ ዓመት ሲሆነው ነው፡፡ አጠቃይ ንብረቱ ንሷብ ከሞላ ዓመት እስከ ሆነ ድረስ፣እያንዳንዱ ክፍልፋይ ዓመት ባይሞላ እንኳ በዓመቱ መጨረረሻ ላይ ዘካውን ይከፍልበታል፡፡ የሚከፈለው መጠን የአንድ አስረኛ ሩብ ማለትም 2.5% ነው፡፡

      ሐራም የሆነ ገንዘብ ዘካት

ሐራም የሆነ ገንዘብ

እንደ በክትና አስካሪ መጠጥ ሐራምነቱ በራሱ ውስጥ ባለው ጎጂነትና መጥፎነትም ይሁን፣ወይም ሀብቱን በማፍራቱ ሂደት ውስጥ በግድ መንጠቅን በመሳሰለ መንገድ የሌሎችን ሐቅ ከፈቃዳቸው ውጭ በመውሰድ፣ወይም እንደ አራጣና ጉቦ ያሉ ሰጭና ተቀባይ ተስማምተው ቢያደርጉት እንኳ ሸሪዓው በማይቀበላቸው ስልቶች የተነጠቀ ገንዘብን የመሳሰለ፣ ሸሪዓው በባለቤትነት መያዙን እና መጠቀሙን ያገደውና የከለከለው ሁሉም ዓይነት ገንዘብ ነው፡፡

    ሐራም የሆነ ገንዘብ ዘካትን የሚመለከት ድንጋጌ

    - እንደ አስካሪ መጠጥ (ኸምር) እና አሳማ ያለው በራሱ ሐራም የሆነው ገንዘብ በሸሪዓው አመለካከት ለአገልግሎት የማይውልና በሸሪዓው በተረጋገጠው መሰረት ሊወገድ የሚገባ በመሆኑ ከዘካት ጋር ግንኙነት የለውም፡፡

    - ለዘካት አስፈላጊ የሆነው የሙሉ ባለቤትነት ቅድመ ሁኔታ ባለመሟላቱ፣በራሱ ውስጥ ባለው ምክንያት ሳይሆን ገንዘቡን በማፍራቱ ረገድ ሸሪዓዊ እንከን ያለበትን ገንዘብ በያዘው ግለሰብ ላይ የዘካት ግዴታ አይኖርም፡፡ ገንዘቡ ወደ ባለቤቱ ሲመለስ ብዙ ዓመታት የቆየ ቢሆን እንኳ በተመራጩ የፉቀሃእ አቋም መሰረት ያንድ ዓመት ዘካት ብቻ ይከፍልበታል፡፡

    - ሕገወጥ የሆነውን ሐራም ገንዘብ የያዘ ሰው ወደ ትክክለኛ ባለንብረቱ ገንዘቡን ሳይመልሰው ቀርቶ እጁ ባለው ላይ ዘካት ከከፈለ የያዘውን ገንዘብ በተመለከተ ኃጢአቱን እንደተሸከመ ይቀራል፡፡ ያወጣው ገንዘብ የዘካት ክፍያ ሳይሆን ሸሪዓው ካጸናበት የዕዳ መክፈል ግዴታ ውስጥ ከፊሉ ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ባለቤቱን ካወቀ ገንዘቡን ወደ ባለንብረቱ መመለስ፣ የባለቤቱን ማንነት የማወቅ ጥረቱን ካሟጠጠ በኋላ ደግሞ ስለ ባለቤቱ ሆኖ ገንዘቡን ለምጽዋት ካልሰጠ በስተቀር ራሱን ከተጠያቂነት ነጻ ማድረግ አይችልም፡፡

    መመሪያዎች ሐራም የሆነ ገንዘብ አያያዙ እንዴት እንደሆነ

    ሀ) ሸሪዓዊ ባልሆነ አካሄድ ሐራም የሆነ ገንዘብ የያዘ ሰው የፈለገውን ጊዜ ያህል ቢቆይ የግል ንብረቱ ሊያደርግ አይችልም፡፡ መቼውንም ቢሆን ገንዘቡን ለባለቤቱ ወይም የሚያውቅ ከሆነ ለወራሹ መመለስ ዋጅብ ነው፡፡ ባለቤቱን ለማወቅ ያደረገው ጥረት ተስፋ የሌለው ከሆነ ከገንዘቡ ለመገላገልና ስለ ባለቤቱ ሆኖ ለመመጽወት ዓላማ ገንዘቡን ለበጎ አድራጎት መስኮች መለገስ ይኖርበታል፡፡

    ለ) አንድ ሰው ሐራም ለሆነ ሥራ ገንዘብ የተከፈለው ከሆነ፣ወደ ሰጠው ሰው መመለስ በወንጀል ላይ ማገዝ በመሆኑና ገንዘብ ከፍሎ ወንጀል የሚያሰራ ወንጀለኛ መተኪያና ካሳ ከፋይም ተቀባይም እንዳይሆን ተቀባዩ ገንዘቡን ለከፈለው ሰው አይመልስም፡፡

    ሐ) እንደ አራጣ ትርፍ ያለ የሐራም ገንዘብ፣ገንዘቡ ሐራም እንዲሆን ባደረገው ሕገወጥ ተግባሩ የቀጠለ ከሆነ በበጎ አድራጎት መስኮች ወጭ ይደረጋል እንጂ ወደ ተወሰደበት ወገን አይመለስም፡

    መ) የሐራም ገንዘቡን በዓይነቱ እንዳለ ለባለቤቱ መመለስ አስቸጋሪ ከሆነ ገንዘቡ በእጁ ያለው ሰው ተመጣጣኙ ወይም ዋጋውን፣የሚታወቅ ከሆነ ለባለቤቱ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ አሊያ ተመጣጣኙን ወይም ዋጋውን ስለ ባለቤቱ ሆኖ በመመጽወት ዓላማ ለበጎ አድራጎት መስኮች ያውላል፡፡ [ዶ/ር ሰላሕ አስሳዊ፣ የዘመኑ ፍቅህ ነክ ጉዳዮች ፣ገጽ 58]<



Tags: