ፍድያ (ቤዛ) እና ሀድይ

3404

      አንደኛ - ፍድያ (ቤዛ)

      የቤዛ ትርጓሜ

ፍድያ (ቤዛ)

ፍድያ (ቤዛ) ሐጅ ወይም ዑምራ አድራጊው ዋጅብ የሆነውን በመተው ወይም የታገደውን ነገር በመፈጸሙ ግዴታ የሚሆንበት እርድ ነው፡፡

    አንደኛ - ዋጅብ የሆነውን የመተው ፍድያ (ቤዛ)

    ከሐጅ ወይም ከዑምራ ዋጅቦች አንዱን፣ሙዝደሊፋ ማደርን ወይም መላጨትንና የመሳሰሉትን የተወ ሰው፣ቤዛ (ፍድያ) ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ እሱም እርድ ሲሆን የግመል አንድ ሰባተኛ፣ወይም የበሬ አንድ ሰባተኛ፣ያንድ ዓመት ዕድሜ ያላት ፍየል፣ወይም የስድስት ወርና ከዚያ በላይ የሆነ በግ ታርዶ ሥጋው በመካ ሐረም ውስጥ ለድኾች የሚከፋፈል ነው፡፡

    ቤዛውን ማቅረብ ያልቻለ ሰው አስር ቀናትን ከተቻለ ሦስቱን እዚያው በሐጅ ሰባቱን ደግሞ ወደ ቤተሰቦቹ ሲመለስ ይጾማል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ያለገኘም ሰው ሦስትን ቀኖች በሐጅ ወራት፤ሰባትንም በተመለሳችሁ ጊዜ መጾም አለበት፤ይህች ሙሉ ዐሥር (ቀናት) ናት፤ይህም (ሕግ) ቤተሰቦቹ ከቅዱሱ መስጊድ አቅራቢያ ላልኾኑ ነው፤አላህንም ፍሩ፤አላህም ቅጣተ ብርቱ መኾኑን ዕወቁ፡፡›› [አል-በቀራህ፡196]

    ሁለተኛ - የታገደውን ነገር የመፈጸም ፍድያ (ቤዛ)

    1 - የተሰፋ ልብስ የመልበስ፣ራስን የመሸፈን፣ሽቶ የመቀባት፣ጸጉር የመላጨትና ጥፍር የመቆረጥ ቤዛ፡፡

    ለነዚህ ከሚከተሉት ሦስት ነገሮች አንዱን ይመርጣል ፡-

    ሀ) ሦስት ቀናት መጾም፡፡

    ለ) ስድስት ምስኪኖችን ለያንዳንዳቸው ግማሽ ሷዕ

    ሩዝና የማሳሰሉትን የቀለብ ምግብ መመገብ፡፡

    ሐ) አንድ ፍየል ማረድ፡፡

    ለዚህ ማስረጃው ቀጣዩ የአላህ ቃል ነው ፡- ‹‹ሀድዩም እስፍራው እስከሚደርስ ድረስ ራሶቻችሁን አትላጩ፤ከናንተም ውስጥ በሽተኛ ወይም በራሱ እውከት ያለበት የኾነ ሰው፣(ቢላጭ) ከጾም ወይም ከምጽዋት ወይም ከመሥዋዕት ቤዛ አለበት፤›› [አል-በቀራህ፡196]

    ከላይ ከተጠቀሱት እገዳዎች መካከል ሆን ብሎ ወይም በከዕብ (ረዐ) ላይ እንደ ደረሰው ዓይነት ማድረግ አስፈልጎት አንዱን የፈጸመ ሰው፣በቤዛ ያካክሳል፡፡ ቤዛውም የመታወክ ቤዛ (ፍድየቱል አዛ) ይባላል፡፡ እነዚህን እገዳዎች በመርሳት የጣሰ ሰው ምንም የለበትም፡፡

    ጥፍር መቆረጥ
    ጸጉር መላጨት
    ሽቶ መቀባት
    ጸጉርን በሚነካው ነገር መሸፈን
    የተሰፋ ልብስ መልበስ

    2 - ከወሲባዊ ተራክቦ በመለስ ያለው ንኪኪና ከአንደኛው ተሐል’ሉል በኋላ የሚፈጸም ወሲብ ቤዛ፡፡

    ይህም ከላይ እንደ ተጠቀሰው የመታወክ ቤዛ (ፍድየቱል አዛ) ዓይነት ነው፡፡

    3 - ማሳሰቢያ፡፡

    የዚህ ማካካሻ ቤዛ ግመል ማረድ [ሁለት ሙድ ግማሽ ሷዕ ሲሆን 1020ግራም ያህል ይመዝናል፡፡] ሲሆን ካላገኘ ሦስት ቀናት በሐጅ ሰባት ቀናት ደግሞ ወደ ቤተሰቦቹ ከተመለሰ በኋላ መጾም ነው፡፡ በዚህ ሐጁ የሚበላሽ ስለሆነ ማሟላትና በመጪው ዓመት መክፈል (ቀዷእ) ግዴታ ይሆንበታል፡፡

    4 - በዑምራ የሚፈጸም ወሲብ ቤዛ፡፡

    ቤዛው አንድ ፍየል ሲሆን ዑምራው የተበላሸ በመሆኑ የመክፈል ግዴታ (ቀዷእ) ይኖርበታል፡፡

    5 - የአደን አውሬን የመግደል ቤዛ፡፡

    የተገደለው አውሬ አቻ ካለው አቻውን ከመስጠትና ዋጋውን ተምኖ በገንዘቡ ምግብ ገዝቶ ለምስኪኖች ከማከፋፈል አንዱን ይመርጣል፡፡ ለየንዳንዱ ምስኪን ሁለት ሙድ100 ይመግባል፡፡ ወይም በያንዳንዱ ሁለት ሙድ ፈንታ አንድ ቀን ይጾማል፡፡

    አቻና ተመሳሳይ ያለው እንስሳ ሲባል የሚመሳሰለው ወይም ተቀራራቢነት ያለው ለማለት እንጅ የማይቻል በመሆኑ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት ማለት አይደለም፡፡

    ምሳሌ - ሰጎን ቢያድን ከግመል ጋር የመመሳሰል ሁኔታ ስላለ አንድ ግመል መክፈል ይኖርበታል፡፡ ወይም ተገምቶ በዋጋው ሩዝ ወይም አጃ ገዝቶ ለያንዳንዱ ምስኪን ሁለት ሁለት ሙድ ይመግባል፡፡ ወይም በያንዳንዱ ሁለት ሙድ ምትክ አንድ ቀን ይጾማል፡፡

    የሜዳ አህያ አድኖ ቢሆን አንድ በሬ ይከፍላል፡፡ እንደዚሁ እያለ ማመሳሰሉን ይቀጥላል፡፡ የታደነው አውሬ እንደ አንበጣ ወይም አሞራ ያለ ሆኖ ከቤት እንስሳት ውስጥ አቻ የሌለው ከሆነ ዋጋውን ተምኖ በገንዘቡ ምግብ ገዝቶ ድሆችን ከመመገብና በየሁለት ሙዱ አንድ ቀን ከመጾም መካከል አንዱን ይመርጣል፡፡ ዋጋውን የሚተምኑት በጉዳዩ ላይ ልምድ ያላቸው የታመኑ ሰዎች ይሆናሉ፡፡

    በሐጅና ዑምራ ላይ እያሉ የጋብቻ ውል ማሰር ከመሰረቱ ውሉ ትክክለኛ ተደርጎ የማይወሰድ በመሆኑ ቤዛ የለበትም፡፡

    ሁለተኛ - ሀድይ

    የሀድይ ትርጓሜ

    ሀድይ

    ለአላህ ዕባዳ ተብሎ ወይም በተመቱዕና በቅራን አፈጻጸም ወይም በመታገድ (እሕሷር) ምክንያት ለመካ ሐረም የሚበረከት የእርድ እንስሳ ነው፡፡

    ፍየል
    ግመል

    የሀድይ ዓይነቶች

    1 - የተመቱዕና የቅራን ሀድይ

    በተመቱዕ ወይም በቅራን የአፈጻጸም ዓይነት ሐጅ ባደረገ ሰው ላይ የሀድይ ግዴታ ያለበት ሲሆን እሱም አንድ ፍየል፣የበሬ ወይም የግመል አንድ ሰባተኛ ነው፡፡ ሀድዩን ማቅረብ ያልቻለ ሰው አስር ቀናትን ከተቻለ ሦስቱን እዚያው በሐጅ ሰባቱን ደግሞ ወደ ቤተሰቦቹ ሲመለስ ይጾማል፡፡

    ይህ ግዴታ የመካ ነዋሪዎች ያልሆኑትን የሚመለከት ሲሆን የመካ ሰው ከሆነ ግን ሀድይም ሆነ ጾም የለበትም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹እስከ ሐጅ በዑምራ የተጣቀመ ሰው፣ከሀድይ የተገራውን (መሠዋት) አለበት፤ያላገኘም ሰው ሦስትን ቀኖች በሐጅ ወራት፤ሰባትንም በተመለሳችሁ ጊዜ መጾም አለበት፤ይህች ሙሉ ዐሥር (ቀናት) ናት፤ይህም (ሕግ) ቤተሰቦቹ ከቅዱሱ መስጊድ አቅራቢያ ላልኾኑ ነው፤›› [አል-በቀራህ፡196]

    2 - የተጠው’ዉዕ ሀድይ

    ይህ በእፍራድ (በነጠላ) ሐጅ ወይም ዑምራ የሚያደርገው ሰው በፍላጎቱ የሚያበረክተው፣ወይም በተመቱዕና በቅራን አፈጻጸም የተጠቀመ ሰው ካለበት ግዴታ በተጨማሪ አክሎ የሚለግሰው፣ወይም ሙሕሪም ያልሆነ ሰው ለአላህ ብሎ መካ ውስጥ እንዲታረድ የሚልከው ሀድይ ነው፡፡

    ነቢዩ ﷺ ‹‹አንድ መቶ የእርድ ግመል ሀድይ ሰጥተዋል፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]

    የተጠውዉዕ፣የተመቱዕና የቅራን ሀድይ ሥጋን መብላቱ ለአቅራቢው የተፈቀደ ሲሆን ነቢዩ ﷺ ያደረጉት በመሆኑ የተወደደም ነው፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ አዝዘው ከታረደ ግመል ሁሉ ሥጋ ተወስዶ ተቀቅሎ መረቁን ጠጥተዋል፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    3 -የእሕሷር (የመታገድ) ሀድይ

    እሕሷር ማለት የሐጅ ወይም የዑምራን ወይም የሁለቱንም ተግባራት ከማሟላት መታገድና መከልከል ነው፡፡

    ለሐጅ ወይም ለዑምራ እሕራም አድርጎ ጠላት ወደ አላህ ቤት እንዳይገባ ያገደው ሰው፣ወይም የሆነ አደጋ አጋጥሞት ወደዚያ መድረስ ያቃተው ሰው፣በታገደበት ቦታ ላይ ሀድዩን ያርድና ተሐል’ሉል አድርጎ ከእሕራም ይወጣል፡፡

    አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ብትታገዱም ከሀድይ (ከመሥዋዕት) የተገራውን (መሠዋት) አለባችሁ፤›› [አል-በቀራህ፡196] የእሕሷር ሀድይ አንድ ፍየል፣የግመል ወይም የበሬ አንድ ሰባተኛ ነው፡፡

    ሀድዩ የሚታረድበት ቦታ

    የተመቱዕ፣የቅራንና የተጠው’ዉዕ ሀድይ የሚታረደው በሐረም ክልል ውስጥ ነው፡፡ እዚያ ታርዶ ሥጋው ለድሆች ይከፋፈላል፡፡ ከመካ ሐረም ውጭ ቢታረድ ተቀባይነት የለውም፡፡

    የእሕሷር ሀድይ ግን በታገደበት ቦታ ላይ ይታረዳል፡፡

    ሀድይ የሚታረድበት ጊዜ

    1 - የተመቱዕ የቅራንና የተጠው’ዉዕ ሀድይ

    ወቅቱ በመሠዊያው ቀን (የውም አን’ነሕር) ከዒድ ሶላት በኋላ ጀምሮ እስከ አይ’ያም አት’ተሸሪቅ የመጨረሻው ቀን ማለትም ወርሐ ዙልሕጃ አስራ ሦስተኛው ቀን ጸሐይ መጥለቅ ድረስ ነው፡፡

    2 - የእሕሷር ሀድይ ወቅቱ የታገዱበት ወቅት ነው፡፡

    ሀድይን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች
    ሐጅ አድራጊው በቅራን ወይም በተመቱዕ አፈጻጸም የተጠቀመ ከሆነ ስለሱ ሆኖ ሀድዩን የሚያርድለት ታማኝ ወኪል መወከል ይፈቀዳል፡፡ ተመራጩ ግን ነቢዩ ﷺ እንዳደረጉት ሁሉ ለራሱ ማረድ ነው፡፡ የቤዛ እርድ የኡድሕይያን እርድ መተካት አይችልም፡፡ ፍድያ (ቤዛ) በተመቱዕ ሐጅ ላደረገ ሰው ሲሆን ኡድሕይያ ግን ሱናነቱ ሐጅ ለሚያደርገውና ለሌላውም ጭምር ነው፡፡


Tags: