የጾም ትሩፋትና ብያኔው

5476

      የጾም ትርጓሜ

የጾም የቋንቋ ትርጉም

ከአንድ ነገር መቆጠብና ራስን መከልከል ነው፡፡

የጾም ሸሪዓዊ ትርጉም

ከጎሕ መቅደድ ጀምሮ እስከ ጸሐይ መጥለቅ ድረስ ለአላህ ዕባዳ ብሎ ራስን ከምግብ፣ከመጠጥና ከወሲብ አግዶ መያዝ ማለት ነው፡፡

    የጾም ትሩፋት

    ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደተጻፈ፣በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ)፣ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ የተቆጠሩ ቀኖች (ጹሙ)፤ከናንተም ውስጥ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የሆነ ሰው፣ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን መጾም አለበት፤በነዚያም ጾምን በማይችሉ ላይ፣ቤዛ ድኸን ማብላት አለባቸው፤ (ቤዛን በመጨመር) መልካምንም ሥራ የፈቀደ ሰው እርሱ (ፈቅዶ መጨመሩ) ለርሱ በላጭ ነው፤ መጾማችሁም ለናንተ የበለጠ ነው፤የምታውቁ ብትኾኑ (ትመርጡታላችሁ)፡፡ (እንድትጾሙ የተጻፈላችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ፣ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾኑ ቀርኣን የወረደበት የረመዳን ወር ነው፤ከናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው፤በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መጾም አለበት፤አላህ በናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፤በናንተም ችግሩን አይሻም፤ ቁጥሮችንም ልትሞሉ፣አላህንም ቅኑን መንገድ ስለ መራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑትም ዘንድ (ይህንን ደነገገላችሁ)፡፡›› [አል-በቀራህ፡183-185]

    ጾም ታላቅ ትሩፋትና እጥፍ ድርብ ሠዋብ ያለው ዕባዳ ሲሆን አላህ የጾምን ክቡርነትና ታላቅነቱን ለመግለጽ የኔ ነው በማለት ከራሱ ጋር አያይዞታል፡፡

    ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው ሐዲስ አልቁድሲ ውስጥ የአላህ መልእክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል ፡- ‹‹የኣደም ልጅ (መልካም) ሥራ ሁሉ (ምንዳው) እጥፍ ይደረጋል፤አንድ ሐሰና (መልካም ሥራ ምንዳው) ከአስር እጥፍ እስከ ሰባት መቶ እጥፍ ነው፡፡ አላህ ፡- ‹ከጾም በስተቀር፣ እሱ ለኔ ነውና እኔ ነኝ ምንዳውን የምሰጠው፣ሥጋዊ ፍላጎቱን፣ምግቡንና መጠጡን ለኔ ብሎ ነው የሚተወው፡፡ ለጾመኛ ሰው ሁለት ደስታዎች ሲኖሩት፤ጾሙን (ማታ) በሚፈስክበት ጊዜ የሚያገኘው ደስታና (በወዲያኛው ሕይወት) ከጌታው ጋር ሲገናኝ የሚያገኘው ደስታ ነው፡፡ የጾመኛው የአፍ ጠረን ለውጥ አላህ ዘንድ በእርግጥ ከሚስክ ሽቶ የበለጠ መዓዝ አለው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብሏል፡፡

    ከጾም መደንገግ ጀርባ ያለው ጥበብ

    1 - ለትእዛዙ በመገዛትና ለሸሪዓው ተመሪ በመሆን የአላህን ፍራቻ (ተቅዋን) እውን ማድረግ ነው፤አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡›› [አል-በቀራህ፡183]

    2 - ለነፍሲያ ትዕግስትን ማለማመድ፣ሥጋዊ ፍላጎቶችን መርታት ይቻል ዘንድ የመንፈስ ጥንካሬን ማጎልበት፡፡

    3 - የሰው ልጅ በጎ ሥራን እንዲለማመድ፣ለድሆችና ለችግረኞች ማዘንና ማሰብን እንዲያውቅ ማሰልጠን፡፡ ይህም አንድ ሰው ለራሱ ሲራብና የረሃብን ምንነት በተግባር ሲረዳ ልቡ ለድሆች እዲለሰልስና ችግራቸው እንደሰማው በማድረግ ነው፡፡

    4 - የአካል እረፍትና ጤንነትን በጾም እውን ማድረግ፡፡

    ጾምን የሚመለከት ብያኔ

    አላህ የደነገገው ጾም በሁለት ይከፈላል ፡-

    1 - የግዴታ ጾም

    የግዴታ ጾም ሁለት ዓይነት ነው ፡-

    ሀ- አላህ አንድ ባሪያው ላይ መጾሙን ግዴታ አድርጎ የደነገገው ጾም ሲሆን ይህም ከእስላም ማእዘናት አንዱ የሆነው የረመዷን ጾም ነው፡፡

    ለ- አንድ የአላህ አገልጋይ በራሱ ላይ ግዴታ እንዲሆን ምክንያት የሚሆንበት እንደ የስለት (የነዝር) ጾምና የማበሻ (ከፍ’ፋራ) ጾም ያለው ነው፡፡

    2 - የተወደደ (ሙስተሐብ) ጾም

    ይህ ሸሪዓው መጾሙን የተወደደ ያደረገው ሰኞና ሐሙስ ቀን መጾምን፣ከየወሩ ሦስት ቀናት መጾምን፣የዓሹራ ቀን ጾም፣የዝልሕጅጃ ወር የመጀመሪያዎቹን አስር ቀናትና የዐረፋ ቀን ጾምን የመሳሰለው ነው፡፡

    ጾም ግዴታ እንዲሆን መሟላት ያለባቸው ሸርጦች

    1 - ሙስሊም መሆን፣በካፍር ላይ ግዴታ አይሆንም፡፡

    2 - ለአቅመ አዳም/ሔዋን መድረስ፣በሕጻን ልጅ ላይ ግዴታ አይሆንም፡፡ ልጆች ይለማመዱት ዘንድ ከቻሉ እንዲጾሙ ይታዘዛሉ፡፡

    3 - መጾም መቻል፣መጾም ከአቅሙ በላይ በሆነ ደካማ ላይ ግዴታ አይሆንም፡፡

    4 - የገላ እረፍትና ጤንነትን በጾም እውን ማድረግ፡፡

    የረመዷን ጾም

    የረመዷን ወር ከእስላም ማእዘናት አንዱ ማእዘን ሲሆን አላህ በባሮቹ ላይ መጾሙን ግዴታ አድርጎ ደንግጓል፡፡ አላህ ፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደተጻፈ፣በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ)፣ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡›› [አል-በቀራህ፡183] ብሏል፡፡

    የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹እስላም በአምስት (ማእዘናት) ላይ ነው የተመሰረተው›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለው ከነዚህ ‹‹ረመዷንን መጾም›› አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

    ከረመዷን ትሩፋት በከፊል

    1 - ረመዷን መጾምና ሌሊቱን በሶላትና በሌሎች ዕባዳዎች ማሳለፍ ያለፈውን ኃጢአት ያስተሰርያል፡፡ ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹የአላህን ቃል በማመንና ምንዳውን በማሰብ ረመዷንን የጾመ ሰው ያለፈው ኃጢኣአቱ ይሰረይለታል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹የአላህን ቃል በማመንና ምንዳውን በማሰብ ረመዷንን (ሌሊት በሶላትና በዕባዳ) የቆመ ሰው ያለፈው ኃጢአቱ ይሰረይለታል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - የመወሰኛውን ሌሊት (ለይለቱል ቀድርን) በሶላትና በዕባዳ ያሳለፈ ሰው ላለፈ ኃጢአቱ ምሕረት ያገኛል፡፡ ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹የአላህን ቃል በማመንና ምንዳውን በማሰብ ረመዷንን የጾመ ሰው ያለፈው ኃጢአቱ ይሰረይለታል፡፡ የአላህን ቃል በማመንና ምንዳውን በማሰብ የመወሰኛውን ሌሊት (ለይለቱል ቀድርን በሶላትና በዕባዳ) የቆመ ሰው ላለፈ ኃጢአቱ ምሕረት ይደረግለታል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - በረመዷን የሚደረግ ዑምራ ምንዳው ከነቢዩ ﷺ ጋር ከተደረገ ሐጅ ጋር እኩል ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹በረመዳን የተደረገ ዑምራ ከሐጅ ወይም ከኔ ጋር ከተደረገ ሐጅ ጋር እኩል ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    4 - በወርሐ ረመዷን የጀነት በሮች ይከፈታሉ፤የጀሀነም በሮች ይዘጋል፤ሰይጣናት ይታሰራሉ፤ነፍስ ወደ በጎ ተግባራት ታቀናለች፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹የረመዳን ወር ሲገባ የሰማይ በሮች ይከፈታሉ፡፡ የጀሀነም በሮች ይዘጋሉ፡፡ ሰይጣኖችም በሰንሰለት ይታሰራሉ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ስለዚህም ሙስሊሞች ተውበት ለማድረግ መጣደፍ፣ከእኩይ ሥራዎች መራቅና ፊታቸውን ወደ አላህ U ለመመለስ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡

    5 - ወርሐ ረመዷን የቁርኣን ወር በመሆኑ በዚህ ወር ውስጥ የቁርኣን ንባብን ማብዛት ተገቢ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ፣ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾኑ ቀርኣን የወረደበት የረመዳን ወር ነው፤›› [አል-በቀራህ፡185]

    6 - ወርሐ ረመዷን የደግነት የልገሳና የሰደቃ ወር ነው፡ ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ በጎ ነገር በመለገስ ከሰዎች ሁሉ የበለጠ ቸር ሲሆኑ፣ከምንጊዜም በላይ እጅግ ለጋስ የሚሆኑት በረመዷን ወር ነበር፡፡ ከጅብሪል በየዓመቱ በረመዷን ይገናኙና የአላህ መልእክተኛ ﷺ ቁርኣንን ለጥናት በርሱ ላይ ይቀሩ ነበር፡ ከጅብሪል ጋር ሲገናኙ የአላህ መልእክተኛ ﷺ በበጎ ሥራና በልገሳ ከተለቀቀ ንፋስ ይበልጥ ቸር፣ፈጣንና ሁሉን አዳራሽ ነበሩ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ረመዷን መግባቱ በምን ይረጋገጣል?

    የረመዷን ወር መግባቱ የሚረጋገጠው ጨረቃዋን በማየት ነው፡፡ ለጋዋ ጨረቃ በሸዕባን ወር ሃያ ዘጠነኛው ቀን ከጸሐይ መጥለቅ በኋላ በምዕራብ በኩል በዓይን ከታየች የረመዷን ወር ገብቷል ማለት ነው፡፡

    በሸዕባን ሰላሳኛው ቀን ከጸሐይ መጥለቅ በኋላ ጨረቃዋ ካልታየች፣ ደመና አቧራ ወይም ጭስ ኖሮ ማየት ካልተቻለ፣የሸዕባን ወር ሰላሳ ይሞላና ቀጣዩ ቀን ረመዷን ይሆናል፡፡ ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹(የረመዳንን ጨረቃ) አይታችሁ ጹሙ፤(የሸዋልን ጨረቃ) አይታችሁትም ፈስኩ (አፍጥሩ)፡፡ ደመና ከሆነባችሁ ወሩን (ሸዕባንን) ሰላሳ አድርጉት፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በረመዷን ወር ውስጥ መፈሰክ

    በረመዷን ወር መፈሰክና ቀኑን አለመጾም ሐራምና እጅግ ከባዳ (ከባእር) ከሆኑ ኃጢአቶች አንዱ ነው፡፡ ከረመዷን ቀናት ውስጥ ያለ ሸሪዓዊ ምክንያት (ዑዝር) አንድ ቀን ያልጾመ ሰው ተውበት ካላደረገ በስተቀር ለዘለዓለም ቢጾም እንኳ ሊተካው አይችልም፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹አላህ ከፈቀደለት ፈቃድ ውጭ ከረመዳን አንድ ቀን የፈሰከ ሰው፣የዕድሜ ልክ ጾም (ቢጾም) እንኳ አይከፍልለትም፡፡›› [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የረመዷን ጾምን መፈሰክ ቅጣቱ እጅግ ከባድ ነው፡፡ አቡ ኡማማ አልባህሊ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹ተኝቼ እያለሁ ሁለት ሰዎች መጥተው ከትከሻ እስከ ክርን ያለውን ሁለት እጆቼን በመያዝ ደረቅና አስቸጋሪ ወደ ሆነ ተራራ ወስደው ወደ ተራራው ውጣ አሉኝ፡፡ እኔ አልችለውም ስላቸው እኛ እንዲቀልህ እናደርግልሃለን አሉኝና እስከ አናቱ ድረስ ወጣሁ፡፡ እዚያ ስደርስ ከፍተኛ የሆነ የጩኸት ድምጽ ሰማሁ፡፡ ይህ የጩኸት ድምጽ ምንድነው? ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ይህ የእሳት (የጀሀነም) ሰዎች የስቃይ ጩኸት ነው አሉኝ፡፡ ከዚያም ይዘውኝ ሄዱና ተዘቅዝቀው ከተረከዛቸው በላይ ባለው ጅማት የተሰቀሉ፣ የአፋቸው ጎኖች ተሰንጥቆ የተቀደደና ከተሰነጠቀው የአፋቸው ሁለት ጎኖች ደም የሚወርድ ሰዎችን አየሁ፡፡ እነዚህ እነማን ናቸው ? ስል ጠየቅሁ፡፡ እነኚህ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ጾማቸውን የሚፈስኩ ሰዎች ናቸው አሉኝ፡፡›› [በእብን ሕባን የተዘገበ] ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

    በወርሐ ረመዷን የሰለፎች ሁኔታ

    የሰለፎች አርአያ ሙሐመድ ﷺ ናቸው

    እብን አልቀይም (ረዐ) ፡- ‹‹በወርሐ ረመዷን ከ(ነቢዩ) ﷺ መመሪያ መካከል ከየዓይነቱ ዕባዳዎችን ማብዛት ሲሆን፣ረመዷን ውስጥ ጅብሪል (ዐሰ) አብሯቸው በመሆን ቁርኣንን ያስጠናቸውና ይከልስላቸው ነበር፡፡ ከጅብሪል ሲገናኙ የአላህ መልእክተኛ ﷺ በበጎ ሥራና በልገሳ ከተለቀቀ ንፋስ ይበልጥ ቸር፣ለበጎ ሥራ ፈጣንና ለሁሉ ደራሽ ነበሩ፡፡

    የአላህ መልእክተኛ ﷺ በጎ ነገር በመለገስ ከሰዎች ሁሉ የበለጠ ቸር ሲሆኑ ከምንጊዜም በላይ እጅግ ለጋስ የሚሆኑት በረመዷን ወር ነበር፡፡ በረመዷን ሰደቃ መስጠትን፣በጎ መስራትን፣ቁርኣን መቅራትን፣ሶላትና ዝክርን፣ እዕትካፍን ያበዙ ነበር፡ በሌሎች ወራት በማያደርጉት ሁኔታ ረመዳንን በተለያዩ ዕባዳዎች ልዩ ያደርጉት ነበር፡፡

    ሌላው ቀርቶ የቀንና የሌሊት ጊዜያቸውን ለዕባዳ ለማዋል ሲሉ አንዳንድ ጊዜ ጾማቸውን በጾም ያገናኙ (ሳያፈጥሩ ተከታዩን ቀን ይጾሙ) ነበር፡፡›› [እብን አልቀይም፣ ዛድ አልመዓድ ቅ 2 ገጽ 30] ብለዋል፡፡

    ሰለፎችና ቁርኣን በረመዷን

    እንደ ወርሐ ረመዷን ባሉ ምርጥ ወቅቶች በተለይም ለይለቱል ቀድር ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በሚጠበቁ ሌሊቶች የጊዘውን አጋጣሚ ለመጠቀም ሲባል ቁርኣን መቅራትን ማብዛት የተወደደ ነው፡፡

    ኢማም አልቡኻሪ (ረዐ) በረመዳን የመጀመሪያው ሌሊት ባልደረቦቻቸው እሳቸው ዘንድ ይሰበሰቡና በየረክዓው ሃያ ኣያ ቁርኣን እየቀሩ ሃያ ረክዓ ያሰግዷቸው ነበር፡ ቁርኣኑን በሙሉ እስኪጨርሱ እንዲህ ያደርጉ ነበር፡ በሱሕር ጊዜ ከቁርኣን ከአንድ ሦስተኛ እስከ ግማሽ የሚሆነውን ይቀሩ የነበረ ሲሆን፣በየሌሊቱ በእፍጣር ሰዓት ሙሉውን ቁርኣን በማኽተም (በመጨረስ) በየኸትሙ ተቀባይነት ያለው ዱዓእ አለ ይሉ ነበር፡፡ [ሰፍወት አስ’ሰፍወህ ቅ 4 ገጽ 170]

    ከኢማም አሽ’ሻፊዒ በተላለፈው መሰረት ሶላት ውስጥ ከሚቀሩት በተጨማሪ ረመዷን ውስጥ ስላሳ ጊዜ ቁርኣን ያኸትሙ ነበር፡፡ [ሰፍወት አስ’ሰፍወህ ቅ 2 ገጽ 255]

    ሰለፎችና ሶላቱል ቅያም (ተራዊሕ) በረመዷን

    ከሳእብ ብን የዚድ በተላለፈው መሰረት ፡- ‹‹በዑመር ብን አልኸጣብ (ረዐ) ዘመን በረመዷን ወር ሃያ ረክዓ ይሰግዱ ነበር፤እያንዳንዳቸው ከመቶ ኣያት በላይ ያላቸውን የቁርኣን ሱራዎች ይቀሩበትም ነበር፤በዑሥማን ብን ዐፋን (ረዐ) ዘመን ከሶላቱ ቅያም (የመቆም ቆይታ) ርዝመትና ክብደት የተነሳ በምርኩዞቻቸው ላይ ይደገፉ ነበር፡፡›› [በይሀቂ በሱነን አልኩብራ ቅጽ 2 ገጽ 699 የዘገቡት] ብለዋል፡፡

    ዐብደላህ ብን አቡ በክር (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት አባቴ ‹‹ረመዷን ውስጥ (ከተራዊሕ) ስንወጣ ጎሕ እንዳይቀድና ፈጅር እንዳይሆን በመስጋት አገልጋዮች ምግብ ቶሎ እንዲያቀርቡ እናጣድፍ ነበር፡፡›› [ሙወጥጠእ ማሊክ፣ ቅጽ 1 ገጽ 116] ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

    ናፊዕ ከዐብደላህ ብን ዑመር (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹በወርሐ ረመዷን (ሶላቱል ቅያምን) እቤታቸው ይሰግዱ የነበረ ሲሆን ሰዎች (ተራዊሕ ሰግደው) ከመስጊድ ሲወጡ፣(ዐብዱላህ) የውሃ እቃቸውን ይዘው ወደ አላህ መልእክተኛ ﷺ መስጊድ ይሄዱና የሱብሕን ሶላት እዚያ ከሰገዱ በኋላ እንጂ አይወጡም ነበር፡፡›› [በይሀቂ በሱነን አልኩብራ ቅጽ 2 ገጽ 696 የዘገቡት] ብለዋል፡፡