የገላ ትጥበት (ጉስል)

14769

      የገላ ትጥበት (ጉስል) ትርጓሜ

የጉስል የቋንቋ ትርጉም

አንድን ነገር ሙሉ በሙሉ ውሃ አዳርሶ ማጠብ ነው፡፡

የጉስል ሸሪዓዊ ትርጉም

አላህን ለመግገዛት ዓላማ በተለየ መንገድ ገላን ሙሉ በሙሉ አዳርሶ መታጠብ ነው፡፡

    የገላ ትጥበት (ጉስልን) ግዴታ የሚያደርጉ ነገሮች

    1 - የአባለዘር ፈሳሽ (መኒይ) ከብልት መውጣት

    መኒይ (ወንዴ የዘር ፈሳሽ) ስሜት በሚሰጥ ሁኔታ ከብልት የሚደፈቅና ከወጣ በኋላ የመሟሸሽ ሁኔታ የሚከተለው ነጭ ወፍራም ፈሳሽ ነው፡፡ የተምር እሸት ጠረን ያለው ሲሆን ከስንዴ ሊጥ ጠረን የቀረበ ነው፡፡

    አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹የረከሳችሁም ብትኾኑ (ገላን የመታጠብ ግዴታ ካለባችሁ ገላችሁን) ታጠቡ፡፡›› [አል-ማኢዳህ፡6]

    ነቢዩም ﷺ ለዐሊይ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ውሃውን በመድፈቅ ከረጨህ (ገላህን) ታጠብ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]

    ጠቃሚ ነጥቦች……

    1 - በሕልም ወሲብ ተፈጽሞ የአባለዘር ፈሳሽ ያልወጣ ከሆነ የመታጠብ ግዴታ አይኖርም፤ከነቃ በኋላ ፈሳሹ ከወጣ ግን ገላን መታጠብ ግዴታ ይሆናል፡፡

    2 - የዘር ፈሳሹ ወጥቶ ካየና የሚያስታውሰው ሕልም ባይኖርም በመውጣቱ ምክንያት መታጠብ ግዴታ ይሆናል፡፡ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና፡- ‹‹ውሃ (የመታጠብ ግዴታ) በውሃ (በመኒይ ውሃ) መውጣት ብቻ ነው፡፡›› [በሙስሊም ተዘገበ]

    3 - ብልቱ ውስጥ የፈሳሹ የመንቀሳቀስ ስሜት ቢሰማውና የወጣ ነገር ከሌለ የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡

    4 - መኒይ ያለ ምክንያት ወይም በበሽታ ምክንያት ያለ እርካታ ስሜት እንዲሁ ከወጣ የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡

    5 - ጀናባ (የመታጠብ ግዴታ) ኖሮበት ከታጠበ በኋላ መኒይ ቢወጣ ብዙውን ጊዜ ያለ ስሜት የሚወጣ በመሆኑ ዳግም መታጠብ ግዴታ አይሆንም፡፡ ለጥንቃቄ ዉዱእ ማድረጉ መልካም ነው፡፡

    6 - አንድ ሰው ከእንቅልፉ ከነቃ በኋላ ምክንያቱን የማያስታውሰው እርጥበት ካገኘ ነገሩ ከሦስት ሁኔታዎች አይዘልም፡-

    ሀ- መኒይ ስለ መሆኑ እርግጠኛ መሆን ነው፡፡ እርግጠኛ ከሆነ በሕልሙ ወሲብ መፈጸሙን አስታወሰም አላስታወሰ መታጠብ ግዴታ ይሆናል፡፡

    ለ- መኒይ አለመሆኑን ማረጋገጥ፡፡ አለመሆኑን ካረጋገጠ የትጥበት ግዴታ አይኖርበትም፡፡ የእርጥበቱ ብያኔ የሽንት ብያኔ ይሆናል፡፡

    ሐ- መኒይ ነው አይደለም? ብሎ መጠራጠር፡ ምንነቱን ለመለየት ጥረት ያደርግና መኒይ ነው ብሎ እንዲ ወስድ የሚያደርግ ነገር ካለ መኒይ ነው፣መዚይ ነው ብሎ እንዲወስድ የሚያደርግ ነገር ካለ መዚይ ነው፡ የሚያስታውሰው ምንም ነገር ከሌለ ግን ለጥንቃቄ ሲባል መታጠብ ይኖርበታል፡፡

    7 - መኒይ ካየና ሕልሙ መቼ እንደነበረ ማስታወስ ካልቻለ ገላውን መታጠብ ግዴታ ይሆንበታል፤በመጨረሻ ከእንቅልፍ ከነቃበት ጀምሮ ያሉትን ሶላቶችም ዳግም መስገድ ይኖርበታል፡

    2 - የግብረ ሥጋ ግንኙነት

    መኒይ ባይፈስም የወንድ ብልት ጫፍ ሙሉ በሙሉ ወደ ሴቲቱ ብልት ሲገባ በሁለቱ ብልቶች መካከል የሚፈጠር ግንኙነት ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋልና፡- ‹‹የግርዛት ቦታ ከግርዛት ቦታ ካለፈ (የወንዱ ብልት ጫፍ ወደ ሴቷ ብልት ከጠለቀ) ገላን መታጠብ ግዴታ ይሆናል፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    3 - የካፍር መስለም

    ይህ ቀይስ ብን ዓስም በሰለሙ ጊዜ ገላቸውን እንዲታጠቡ ነቢዩ ﷺ ያዘዙ [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] በመሆኑ ነው፡፡

    4 - የወር አበባና የወሊድ ደም (ንፋሳ) መቆም

    ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ለፋጥማ ብንት አቡ ሑበይሽ ፡- ‹‹ወር አበባ ሲመጣ ሶላት መስገድ ተዪ፤ሲሄድ ታጥበሽ ስገጂ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

     ብለዋል፡፡ የወሊድ ደምም ብያኔው በሊቃውንት የጋራ ስምምነት መሰረት እንደ ወር አበባ ነው፡፡

    5 - ሞት

    ነቢዩ ﷺ የሴት ልጃቸውን አስከሬን ትጥበት አስመልክተው ለፋጥማ ብንት አቡ ሑበይሽ ፡- ‹‹ሦስት ጊዜ፣ወይም አምስት ጊዜ፣(አስፈላጊ ከሆነም) ከዚም በላይ እጠቢያት፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]ብለዋል፡፡

    የገላ አስተጣጠብ

    በገላ ትጥበት ላይ ግዴታው ለታቀደ የመታጠብ ዓላማ ገላን ሙሉ በሙሉ አዳርሶ በማንኛውም አኳኋን ቢሆን በውሃ መታጠብ ነው፡ ይሁን እንጅ የነቢዩን ﷺ አስተጣጠብ መከተል የተወደደ ነው፡፡

    አስተጣጠባቸው በእመ ምእመናን መይሙና (ረዐ) ገለጻ መሰረት የሚከተለው ነው፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ የጀናባ መታጠቢያቸውን ውሃ አኖሩና ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ በቀኝ መዳፋቸው ውሃውን ዘግነው በግራው ላይ በመገልበጥ ታጠቡ፤ከዚያ ብልታቸውን አጠቡ፤ከዚም ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ መዳፋቸውን መሬት ወይም ግድግዳው ላይ መታ መታ አደረጉ፡፡ ቀጥሎም ተጉመጥምጠው ውሃ በአፍንጫ ወደ ውስጥ ስበው አስወጡ፤ፊታቸውንና ክንዶቻቸውን ታጠቡ፡ ከዚም ፈንጠር ብለው እግሮቻቸውን ታጠቡ፡ ለማድረቂያ ጨርቅ ሳመጣላቸው ስላልፈለጉ በእጃቸው ውሃውን ማራገፍ ያዙ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]

    በዚህም መሰረት አስተጣጠቡ፡-

    1 - መዳፎችን ሁለት ወይም ሦስት ጊዚ ማጠብ፡፡

    2 - ብልትን ማጠብ፡፡

    3 - ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ መዳፍን መሬት ወይም ግድግዳ ላይ መታ መታ ማድረግ፡፡

    4 - ሁለቱ እግሮች ብቻ ሲቀሩ ለሶላት የሚደረግ ዉዱእ ማድረግ፡፡

    5 - በራስ ላይ ውሃ ማፍሰስ፡፡

    6 - ገላን ሙሉ በሙሉ መታጠብ፡፡

    7 - ፈንጠር ብሎ ሁለቱን እግሮች ማጠብ፡፡

    ጠቃሚ ነጥቦች

    - ሴት ለጀናባም ሆነ ለወር አበባ ስትታጠብ የተጎነጎነ ጸጉሯን መፍታት አያስፈልጋትም፤ወደ ጸጉሩ ስር እስከ ተዳረሰ ድረስ ውሃ ካፈሰሰችበት በቂ ነው፡፡

    - ለወር አበባ ወይም ወሊድ ደም ስትታጠብ ትንሽ ጥጥ ወይም ሌላ መሰል ነገር ወስዳ ሚስክ ወይም ሽቶ ጨምራበት የደም ቅሪቱን ማጥፋት የተወደደ ነው፡፡

    - አንድ ሰው ለጀናባ ገላውን ከታጠበ ለዉዱእ ንይያ አደረገም አላደረገ በዚህ ትጥበት ብቻ ሶላት መስገድ ይችላል፡፡

    ጀናባ ባለበት ሰው ላይ ሐራም የሆኑ ነገሮች

    1 - ሶላት ፡-

    አላህU እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተ የሰከራችሁ ኾናችሁ፣የምትሉትን እስከምታውቁ፣የረከሳችሁም ስትኾኑ መንገድን አላፊዎች ካልኾናችሁ በስተቀር (አከላታችሁን ) እስከምትታጠቡ ድረስ ስግደትን አትቅረቡ፡፡››[አል ኒሳእ፡43]

    2 - በተከበረው ቤት ዙሪያ መዞር (ጠዋፍ)

    ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹በተከበረው ቤት (ከዕባ) መዞር ሶላት ነው፡፡›› [በነሳኢ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - የቁርኣንን መጽሐፍ በእጅ መንካት

    አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹የተጥራሩት እንጅ ሌላ አይነካውም፡፡››[አል-ዋቂዓህ፡79]

    ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ንጽሕና ያለው ሰው እንጅ (ሌላው) የቁርኣንን መጽሐፍ በእጁ አይንካ፡፡›› [ማሊክ ሙወጥጠእ ውስጥ የዘገቡት] ብለዋልና፡፡

    4 - ቁርኣንን መቅራት

    ዐሊይ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከመጸዳጃ ቦታ መጥተው ቁርኣንን ያስተምሩን፣ሥጋንም ከኛ ጋር ይበሉ ነበር፤ከጀናባ በስተቀር ከቁርኣን የሚያግዳቸው ምንም ነገር አልነበረም፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]ብለዋልና፡፡

    5 - አቋርጦ ለማለፍ ካልሆነ በስተቀር መስጊድ ውስጥ መቀመጥ

    አላህU እንዲህ ብሏልና፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተ የሰከራችሁ ኾናችሁ፣የምትሉትን እስከምታውቁ፣የረከሳችሁም ስትኾኑ መንገድን አላፊዎች ካልኾናችሁ በስተቀር (አከላታችሁን ) እስከምትታጠቡ ድረስ ስግደትን አትቅረቡ፡፡›› [አል ኒሳእ፡43]

    ሶላት
    በከዕባ ዙሪያ መዞር (ጠዋፍ)
    ሙስሐፍ (የቁርኣን መጽሐፍ) በእጅ መንካት
    ቁርኣን መቅራት
    መስጊድ ውስጥ መቀመጥ

    ተወዳጅ (ሙስተሐብ) የሆኑ ትጥበቶች

    1 - ለጁሙዓ መታጠብ ፡-

    ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ለጁሙዓ ሶላት ዉዱእ ያደረገ ሰው ጥሩና መልካም ነው፤ገላውን የታጠበ ሰውም (ጥሩና መልካም ሲሆን) መታጠብ የበለጠ ተመራጭ ነው፡፡›› [በአቡ ዳውድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    2 - ለሐጅና ለዑምራ እሕራም ሲደረግ ፡-

    ዘይድ ብን ሣቢት (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹ነቢዩ ﷺ ለእሕራም የተሰፉ ልብሶችን አውልቀው ገላቸውን መታጠባቸውን መመልከታቸውን ዘግበዋል፡፡ [በትርምዚ የተዘገበ]

    3 - አስከሬን ካጠቡ በኋላ መታጠብ ፡-

    ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹የሞተን ሰው ያጠበ ሰው (ለራሱም) ይታጠብ፡፡›› [በእብን ማጀህ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    4 - ከያንዳንዱ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ መታጠብ ፡-

    ከአቡ ራፊዕ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ፡- ከዕለታት አንድ ቀን ነቢዩ ﷺ ሚስቶቻቸውን አዳረሱና ከዚችኛዋም ዘንድ ከዚያኛዋም ዘንድ ገላቸውን ታጠቡ፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ ! አንድ ትጥበት ብቻ ቢያደርጉስ? አልኳቸውና፡- ‹‹ይኸ የበለጠ የጠራ፣የበለጠ ያማረና የበለጠ የጸዳ ነው፡፡›› አሉ ብለዋል፡፡ [በአቡ ዳውድ የተዘገበ]

    ተገቢ አይደለም

    1- የሶላት ወቅት እስኪወጣ ድረስ ጀናባን ሳይታጠቡ መቆየት፡፡

    2- ሴት ከወር አበባ ስትጠራ ጌዴታ የሆነውን ሶላት አለመስገድ፡፡ ለዙህር ሶላት ወቅት ማብቂያ ያንድ ረክዓ ጊዜ ብቻ ቀርቶ ቢሆን ገላዋን ታጥባ መስገድ ግዴታ ይሆንባታል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ጸሐይ ከመውጣቷ በፊት ለአንድ ረክዓ የደረሰ ሰው የሱብሕ ሶላትን ደርሶበታል፡፡ ጸሐይ ከመጥለቋ በፊት ለአንድ ረክዓ የደረሰ ሰው የዐስር ሶላትን ደርሶበታል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም ተዘገበ] ብለዋል፡፡