የጀማዓ ሶላት

4253

    የጀማዓ ሶላትን የሚመለከት ብያኔ

    ችሎታ ያላቸውን ወንዶች ሶላትን በጀማዓ እንዲሰግዱ ሸሪዓው አዞ የሚተውትን አስጠንቅቋል፡፡ ሶላቱል ጀማዓ ላይ የማይገኙትን ለማቃጠል ነቢዩ ﷺ አስበዋል፡፡ ማየት ለተሳነው ሰው እንኳ ነቢዩ ﷺ ከጀማዓ እንዲቀር አልፈቀዱለትም፡፡ ለዚህ ማስረጃው የሚከተሉት ናቸው፡-

    1 - የፍርሃት ሶላትን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹በውስጣቸውም በኾንክና ሶላትን ለነርሱ ባስሰገድካቸው ጊዜ፣ከነሱ አንዲት ጭፍራ ካንተ ጋር ትቁም፤›› [አል-ኒሳእ፡102]

    አላህ በዚህ አንቀጽ በጦር ሜዳ ፍርሃት ውስጥና በጉዞ ላይ ሆነው በጀማዓ እንዲሰግዱ ያዘዘ ከሆነ፣በሰላሙ ጊዜና እቤት እያሉ ደግሞ ትእዛዙ የበለጠ የጸና ይሆናል፡፡

    2 - ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ነቢዩ ﷺ ፡ ‹‹በመናፍቃን ላይ ይበልጥ ከባዱ ሶላት፣የዕሻእ ሶላትና የፈጅር ሶላት ነው፡፡ በሁለቱ ውስጥ ያለውን (ታላቅ አጅር) ቢያውቁት ኖሮ በሆድ እየተሳቡም ቢሆን መጥተው (በጀማዓ) በሰገዱ ነበር፡፡ ሶላት እንዲሰገድ አዝዤና አንድ ሰው ሰዎችን እንዲመራ መድቤ፣የእንጨት ሸክሞች ከያዙ ሰዎች ጋር በመሆን በሶላት ላይ የማይገኙ ሰዎችን ቤቶች ሄጄ በላያቸው ላይ በእሳት ማጋየት አስቤያለሁ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ነቢዩ ﷺ ጀማዓ ሶላት ግዴታ ባይሆን ኖሮ ከሶላቱ የቀሩትን ሰዎች ለማቃጠል ባላሰቡ ነበር፡፡ ግዴታ ባይሆን ኖሮ ጀማዓ የማይሰግዱ ሰዎች በመናፍቅነት ባልተፈረጁም ነበር፡፡

    3 - መሪ ስለሌለው እቤቱ መስገድ እንዲፈቅዱለት ለጠየቃቸው ዓይነ ስውር ነቢዩ ﷺ ‹‹የሶላት ጥሪውን (አዛን) ትሰማለህን?›› ሲሉት አዎ አላቸውና ‹‹እንግዲያውስ ምላሽ ስጥ (መጥተህ ስገድ)፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለውታል፡፡

    4 - እብን መስዑድ (ረዐ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ነገ አላህን ሙስሊም ሆኖ ለመገናኘት የሚወድ ሰው፣እነኚህን ሶላቶች ጥሪ በሚደረግላቸው ቦታ በመገኘት ተጠባብቆ ይስገዳቸው፡፡ አላህ ለነቢያችሁ ﷺየቅን መመሪያ ነቢያዊ ፈለጎችን (ሱነኑል ሁዳ) የደነገገ ሲሆን፣ሶላቶቹ ከሱነኑል ሁዳ አንዱ ናቸው፡ እቤቱ ቀርቶ እንደሚሰግደው ዓይነት ሰው ከጀማዓ ቀሪ የሆነ ሰው፣ እቤታችሁ ከሰገዳችሁ የነቢያችሁን ሱንና የተዋችሁ ትሆናላችሁ፤ የነቢያችሁን ሱንና ከተዋችሁ ደግሞ ትጠማላችሁ፡፡ ዉዱእ አድርጎና ዉዱኡን አሳምሮ ከነኚህ መስጊዶች ውስጥ ወደ አንዱ መስጊድ ያቀና ሰው፣በያንዳንዱ እርምጃ አንድ ሰናይ ተግባር (ሐሰነህ) ይመዘግብለታል፤አንድ ደረጃም ከፍ ይደረጋል፤አንድ እኩይ ተግባርም (ሰይይአህ) ይታበስለታል፡፡ መናፍቅነቱ የታወቀና የለየለት እንጂ ሌላው (ጀማዓ ሶላትን) እንደማይተው በእርግጥ አይተናል፡፡ (መራመድ ያልቻለውን እንኳ) በግራና በቀኝ በሁለት ሰዎች መካከል ተደግፎ አምጥተው ሶፍ ውስጥ ያቆሙት ነበር፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    የጀማዓ ሶላት ጥበብና ትሩፋቱ

    1 - ወንድማማቾችና ለአላህ ብለው የተዋደዱ ሰዎችን እርስ በርስ ማስተዋወቅ፣የኢማን ግኝት መሰረት የሆነውን የወንድማ ማችነትና የመዋደድ ትስስርን ማጥበቅ፡፡ ለአላህ U ብሎ ከመዋደድ ውጭ ወደ ኢማንም ሆነ ወደ ጀነት የመድረሻ መንገድ የለምና፡፡

    2 - በተከታታይ ለአርባ ቀናት የእሕራም ተክቢራን ከኢማሙ ጋር የደረሰበት ሰው ከመናፍቅነትና ከእሳት ነጻ መሆኑ፡፡ ከአነስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ :- ‹‹የመጀመሪያውን ተክቢራ ደርሶ በጀማዓ ለአርባ ቀናት ለአላህ የሰገደ ሰው፣ሁለት ነጻ መሆን ይጻፍለታል፡- ከእሳት ነጻ መሆንና ከንፋቅ ነጻ መሆን፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - የሙስሊሞችን አንድነት ማሰባሰብ፣ልቦቻቸውን በመልካም ነገርና በቅንነት መሰረት ላይ አንድ ማድረግ፡፡

    4 - በሙስሊሞች መካከል ተራድኦና እርስ በርስ መተጋገዝን መፍጠር፡፡

    5 - የዲኑን አቢይ መለያና ምልክቱን ማጉላትና ብርታቱን ማሳየት፡፡

    6 - በአንዱ የሶላት ሶፍ ነጭና ጥቁሩ፣ዐረባዊውና ዐጀሚው፣ዐዋቂውና ልጅ እግሩ፣ሀብታምና ድሃው፣ሁሉም ጎን ለጎን በአንድ መስጊድ ውስጥ፣በአንድ ኢማም ተመርተው፣በአንድ ጊዜ፣ፊታቸውን ወደ አንድ ቅብላና ወደ አንድ አቅጣጫ አዙረው ስለሚሰግዱ የሙስሊሞችን ልብ አንድ ያደርጋል፡፡

    7 - የአላህን ጠላቶች ማስቆጨት፡፡ ሙስሊሞች በመስጊድ ተሰባስበው አንድ ላይ ጀማዓ መስገድን አጥብቀው እስከያዙ ድረስ ኃይልና ብርታታቸውን እንደያዙ ይኖራሉ፡፡

    8 - ኃጢኣቶችን ማበስና ደረጃን ከፍ ማድረጉ፡፡ ከአቡ ሁሬራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል :- ‹‹አላህ ኃጢቶችን የሚያብስበትንና ደረጃዎችን ከፍ የሚያደርግበትን ነገር ላመላክታችሁን? ሲሉ፣(ሰሓባ) ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አዎ ይንገሩን› አሉና ነቢዩ ﷺ (በብርድና በመሳሰለው) እየከበደ ዉዱእ አሟልቶ ማድረግ፣ወደ መስጊዶች እርምጃዎችን ማብዛት፣ከአንዱ ሶላት በኋላ ተከታዩን ሶላት መጠባበቅ ነው፡፡ ይህ ነው ለአላህ ትእዛዝ ተገዥ መሆን (ሪባጥ) ማለት፤ይህ ነው ነፍስን ለአላህ ማስገዛት (ሪባጥ) ማለት፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    9 - የሕብረት ሶላት በነጠላ ከሚሰገደው ሶላት በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል፡፡ ከዐብዱላህ ብን ዑመር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹ጀማዓ ሶላት በነጠላ ከሚሰገደው ሶላት በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል፡፡›› [በቡኻሪ ተዘገበ] ብለዋል፡፡



Tags: