የወር አበባ እስትሓዳና ንፋሳ

6120

      የወረ አበባ (ሐይድ)

      የወር አበባ ትርጓሜ

የሐይድ የቋንቋ ትርጉም

ሐይድ ማለት ያንድ ነገር መፍሰስና መሄድ ነው

የሐይድ ሸሪዓዊ ትርጉም

ከሴት ማሕጸን በጤናማ ሁኔታ ያለ ምንም ምክንያት በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ የሚወጣ ደም ነው፡፡

      የወር አበባ ደም ባህሪ

      በጣም ከመጥቆሩ የተነሳ የተቃጠለ የመሰለ ጥቁር፣የሕመም ስሜት የሚያስከትል፣መጥፎ ጠረን ያለው ሲሆን፣ሲመጣ ከፍተኛ ሙቀት እንዳለው ይሰማታል፡፡

      የወር አበባ መምጫ ዕድሜ

      የወር አበባ መምጣት የሚጀምርበት የተወሰነ ዕድሜ የለም፡፡ እንደ ሴቲቱ ተፈጥሮና እንደ አካባቢና የአየር ንብረት ይለያያል፡፡ በመሆኑም ሴት ልጅ የወር አበባዋን ባየች ጊዜ ነው አየች የሚበላው፡፡

      የወር አበባ የመቆያ ጊዜ

      የወር አበባ የተወሰነ የመቆያ ጊዜ የለውም፡፡ ለሦስት ቀናት ብቻ የሚቆይባቸው ሴቶች ሲኖሩ ለአራት ቀናት የሚቆይባቸውም አሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ስድስት ወይም ሰባት ቀን ይቆያል፡፡

      ነቢዩ ﷺ የወር አበባ ለብዙ ቀናት ለሚቆይባቸው ለሐምናህ ብንት ጀሐሽ ፡- ‹‹ዕውቀቱ አላህ ዘንድ ነውና የወር አበባ መቆያ ጊዜሽን ስድስት ወይም ሰባት ቀናት አድርጌሽ ውሰጂና ታጠቢ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      ጠቃሚ ነጥቦች

      1 - በመሰረቱ እርጉዝ ሴት የወር አበባ አታይም፡፡ ከመገላገሏ ጥቂት ቀደም ብሎ ደም ካየች የወሊድ ደም ነው፤ከመውለዷ በፊት ብዙ ጊዜ ቀደም ብሎ ካየች ግን የወር አበባ ነው፡፡

      2 - አንዲት ሴት ወር አበባዋ ከተለመደው ጊዜ ቢቀድም ወይም ቢዘገይ፣ለምሳሌ በወሩ መጀመሪያ መምጣት የነበረበት በወሩ መጨረሻ ቢመጣ፣የመቆያ ጊዜውም ለምሳሌ የተለመደው ስድስት ቀን ሆኖ ሰባት ቀን በመሆን ቢጨምር ወይም ከዚያ ቢቀንስ ለዚህ ትኩረት መስጠት አያስፈልጋትም፡፡ ደም ካየች የወር አበባ ነው ካላየች ደግሞ በንጽሕና ላይ ነች ማለት ነው፡፡

      3 - የሴቲቱ ንጽሕና የሚታወቀው የወር አበባ መቆምን ተከትሎ በሚወጣው ነጭ ፈሳሽ ሲሆን ፈሳሹ ካልወጣ የመቆሙ ምልክት መድረቁ ነው፡፡ ነጭ ጥጥ ወደ ብልቷ አስገብታ ምንም የሌለበት ደረቅ ሆኖ ከወጣ ቆሟል ማለት ነው፡፡

      የወር አበባን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች

      1 - ኩድራና ሱፍራን የሚመለከት ብያኔ

      የኩድራና የሱፍራ ትርጓሜ ትርጓሜ
ሱፍራህ፡-

ከሴት ማሕጸን የሚወጣ ወደ ብጫነት ያደላ እዥ መሰል ደም ነው፡፡

ኩድራህ ፡-

ከሴት ማሕጸን የሚወጣ በብጫነትና ጥቁረት መካከል የሆነ የደፈረሰ ውሃ መሰል ደም ነው፡፡

      ኩድራህና ሱፍራህን የሚመለከት ብያኔ

      አንዲት ሴት ወደ ብጫነት ያደላ ወይም በብጫነትና በጥቁረት መካከል የደፈረሰ ውሃ ዓይነት ደም ካየች ወይም እርጥበት ብቻ ካየች ሁኔታው ከሁለት ነገሮች አይዘልም ፡-

      1 - በወር አበባዋ የመቆያ ጊዜ ውስጥ ወይም ከዚሁ ጊዜ ለጥቆ ባለው የቅድመ ንጽሕና ጊዜ ውስጥ አይታው መሆኑ፡፡

      ሁኔታው ይኸ ከሆነ የወር አበባ ብያኔ ይጸናበታል፡፡ ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው ሐዲስ መሰረት ፡- ‹‹ሴቶች ከወር አበባ መጥራታቸውን ለማወቅ ሱፍራ የነካው ጥጥ [ዱርጃ የወር አበባ ቅሪት መኖር አለመኖሩን ለማወቅ የሚወተፍ ነገር፡፡] ያለበት ዱርጃ [ኩርሱፍ ንጹሕ ጥጥ ነው፡፡] (መወተፊያ) ወደሳቸው ሲልኩባቸው ፡- ነጭ ጥጥ ወደ ብልት ገብቶ ምንም የሌለበት ደረቅ ሆኖ እሰኪ ወጣ ድረስ አትቻኮሉ›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]ይሏቸው እንደ ነበር ተዘግቧል፡፡

      2 - የወር አበባዋ በሌለበት የንጽሕና ጊዜ አይታው መሆኑ፡፡

      ሁኔታው ይኸ ከሆነ ደግሞ ምንም ተደርጎ አይቆጠርም፡፡ ዉዱእም ሆነ የገላ ትጥበት ግዴታ አይሆንባትም፡፡ ከኡም ዐጢይያ በተላለፈው መሰረት ፡- ‹‹ከወር አበባ ከጠራን በኋላ ኩድራን እና ሱፍራን ምንም አድርገን አንቆጥርም ነበር፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      የንጽሕና ጠቋሚ ምልክት
      ሱፍራ
      ኹድራ

      2- የወር አበባ መቆራረጥን የሚመለከት ብያኔ ፡-

      አንዲት ሴት አንድ ቀን ደም አንድ ቀን ደግሞ ንጽሕና ካየች ነገሩ ከሁለት ሁኔታዎች አይዘልም፡-

      1- ሁኔታው ሁል ጊዜ በዚህ የሚቀጥል መሆን ፡-

      ይህ የእስትሓዳ ደም ነው፡፡

      2- የሚቆራረጥ መሆን ፡-

      አንዳንድ ጊዜ እየመጣ አንዳንድ ጊዜ የሚጠፋ መሆን፡፡ ሁኔታው ይኸ ከሆነ ብያኔው የሚከተለው ይሆናል፡-

      ሀ- የደሙ መቋረጥ በአንድ ቀን ከቀነሰ ጊዘውን የወር አበባ ጊዜ አድርጋ ትቆጥረዋለች፡፡

      ለ- በንጽሕናው ጊዜ ውስጥ ገብቶ የወጣ ንጹሕ ጥጥን (አልቅስ'ሰቱል በይዳእ) የመሰለ ንጽሕና ጠቋሚ ነገር ካየች፣ይህ ጊዜ ጥቂትም ይሁን ብዙ፣ከአንድ ቀን ያነሰም ይሁን ወይ የበለጠ የንጽሕና ጊዜ ይሆናል፡፡

      እስትሓዳ

      የእስትሓዳ ትርጓሜ

እስትሓዳ

እሰትሓዳ ሁሌም በማያቋርጥ ሁኔታ ወይም ለአጭር ጊዜ ብቻ እየተቋረጠ ከሴት ብልት የሚወጣ የደም ፍሰት ነው፡፡

      በወር አበባ ደምና በእስትሓዳ ደም መካከል ያለው ልዩነት

የወር አበባ ደም የእስትሓዳ ደም
ወፈር ያለ ጥቁር ነው ሳሳ ያለ ቀይ ነው
መጥፎ ጠረን አለው ጠረን የለውም
የማይረጋ ነው የሚረጋ ነው
ራቅ ካለ የማሕጸን ውስጣዊ ክፍል ይወጣል ከቅርብ የማሕጸን ዉስጣዊ ክፍል ይወጣል
ጤናማና ተፈጥሯዊ ደም ነው የበሽታና የጤና መታወክ ብልሹ ደም ነው
ተለይተው በሚታወቁ ጊዛያት ይወጣል ተለይቶ የሚታወቅ ጊዜ የለውም

      እስትሓዳ ያለባት ሴት ሁነታዎች

      የመጀመሪው ሁኔታ፡- ከእስትሓዳ በፊት የታወቀ የወር አበባ መምጫና መሄጃ ጊዜ ልማድ ያላት መሆን፡፡

      በዚህ ሁኔታ ቀደም ሲል የነበራትን የወር አበባ ልማዷን በወር አበባነቱ አስልታ ቀሪውን ወር እስትሓዳ አድርጋ ትወስዳለች፡፡ ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ፋጥማ ብንት አቢ ሑበይሽ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እኔ (እስትሓዳ ስላለብኝ) ንጽሕና የለኝምና ሶላት እተዋለሁ ወይ? ብለው ሲጠይቁ፣የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹ ይኸ በደም ሥር (ምክንያት) ነውና አትተዪ፤ግና የወር አበባ ታይበት የነበረውን ጊዜ ያህል ሶላት ትተሽ ገላሽን ታጠቢና ስገጂ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ ] ብሏቸዋል፡፡

      ሁለተኛው ሁኔታ፡- የታወቀ የወር አበባ ጊዜ ልማድ የሌላት ሆኖ በወር አበባ ደምና በእስትሓዳ ደም መካከል ያለውን ልዩነት ለይታ ማወቅ መቻል፡፡

      ይህችኛዋ ሁለቱን በመለየት ተገቢውን ትፈጽማለች፡፡ እስትሓዳ ለነበረባቸው ፋጥማ ብንት ሑበይሽ ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹የወር አበባ ደም ከሆነ የሚታወቅ ጥቁር ደም ነው፤እሱ ከሆነ ከመሰገድ ተቆጠቢ፡፡ ሌላኛው ከሆነ ደግሞ ዉዱእ አድርጊና ስገጅ ፤ደም ስር እንጅ ሌላ አይደለምና፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብሏቸዋል፡፡

      ሦስተኛው ሁኔታ፡- የታወቀ ልማድም ሆነ የመለየት ብቃት የሌላት መሆን፡፡

      ይህችኛዋ ደግሞ በአብዛኛዎቹ ሴቶች ልማድ መሰረት ትፈጽማለች፡፡የወር አበባ ጊዜው ደም ከታየበት ወቀት አንስቶ የሚጀምር በየወሩ ስድስት ወይም ሰባት ቀናት ይደረግና የወሩ ቀሪ ጊዜ እስትሓዳ ይሆናል፡፡

      ነቢዩ ﷺ ለሐምናህ ብንት ጀሐሽ ፡- ‹‹ዕውቀቱ አላህ ዘንድ ነውና የወር አበባ መቆያ ጊዜሽን ስድስት ወይም ሰባት ቀናት አድርጌሽ ውሰጂና ታጠቢ፡፡ ንጹሕ ሆነሽ መጽዳትሽን ስትረጂ ሃያ ሦስት ሌሊት ወይም ሃያ አራት ሌሊት ከቀናቱ ጋር ሰገጂ፤ጹሚ፡፡ ይህ በቂሽ ነው፡፡ ሴቶች በተለመደ ጊዜ የወር አበባቸውን እደሚያዩትና እንደሚጠሩት ሁሉ አንቺም በየወሩ እንደዚሁ አድርጊ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      አራተኛው ሁኔታ፡- የታወቀ ልማድ ያላትና መለየትም የምትችል መሆን፡፡

      ይህችኛዋ ደግሞ በመለየቱ ሳይሆን በልማዱ መሰረት ታሰላለች፡፡ ለሴት ልማዱ የበለጠ ትክክለኛ ነውና፡፡ ልማዷን የረሳች ከሆነ ግን በመለየት ትጠቀማለች፡፡

      ጠቃሚ ነጥቦች

      1 - አንዲት ሴት የወር አበባዋን ወቅት የምታውቅ ሆና የመቆያ ጊዜው ስንት ቀን እንደሆነ ከረሳች ግን በአብዛኞቹ ሴቶች ልማድ መሰረት ቀኑን ታሰላለች፡፡

      2 - የወር አበባዋን የመቆያ ቀናት ቁጥር የምታውቅ ሆና ወቅቱ በወሩ መጀመሪያ ይሆን ወይም በወሩ መጨረሻ? መቼ እንደሆነ ከረሳች ከወሩ መጀመሪያ አንስታ ታሰላለች፡፡ በወሩ አጋማሽ ላይ ነበር ብላ ካሰበችና በትክክል በስንተኛው ቀን እንደሆነ መለየት ካልቻለች ከወሩ አጋማሽ ጀምራ ታሰላለች፤ከአጋማሹ መነሳት ለትክክለኛነት ይበልጥ የቀረበ ነውና፡፡

      3 - የወር አበባ መቆያ ጊዜው ያበቃ ከሆነና ሴቲቱ እስትሓዳ ያለባት ከሆነ ገላዋን ትታጠብና ብልቷን በጨርቅ ትወትፋለች፤የጡህር ብያኔ ስለሚኖራት ትሰግዳለች፣ትጾማለችም፤ዑዝር ስላላት ከዉዱእ በኋላ የሚፈሳት ደም ችግር አይፈጥርም፡፡ ጦሃራን አስመልክቶ ከሦስት ገጽታዎች አንዱን ትከተላለች፡-

      ሀ- የሶላቱ ወቅት ከገባ በኋላ ለየሶላቱ አዲስ ዉዱእ ማድረግ፡፡ ይህም ብልቷን ከታጠበችና ጨርቅ ካሰረችበት በኋላ ይሆናል፡፡ ነቢዩ ﷺ ለፋጥማ ብንት ሑበይሽ (ረዐ) ፡- ‹‹ከዚያም ለየሶላቱ ዉዱእ አድርገሽ ስገጅ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]ብለዋልና፡፡

      ለ- ዙህርን ወደ ከዐስር ሶላት በፊት በማዘግየት ገላዋን ታጥባ ዙህርና ዐስርን ወዘተ.

      መስገድ፡፡ ነቢዩ ﷺ ለሐምና ብንት ጀሐሽ (ረዐ) ፡-‹‹ዙህርን አዘግይተሸ ዐስርን አፋጥነሽ ገላሽን ከታጠብሽ በኋላ ሁለቱን ሶላቶች ዙህርና ዐስርን አጣምረሽ ለመስገድ፣መግሪብን አዘግይተሸ ዕሻን በማፋጠን ገላሽን ታጥበሽ ሁለቱን ሶላቶች አጣምረሽ አንድ ላይ ለመስገድ ብርታት ካለሽ አድርጊ፡፡ ለፈጅር ሶላት ገላሽን መታጠብ ከቻልሽ አድርጊ፣ጹሚም፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

      ሐ- ለያንዳንዱ ሶላት ገላን መታጠብ፡፡ ‹‹ኡምሙ ሐቢባ (ረዐ) ለሰባት ዓመታት የእስትሓዳ ኖሮባቸው ስለጉዳዩ የአላህ መልእክተኛን ﷺ ሲጠይቁ፣ገላቸውን እንዲታጠቡ አዘዟቸውና ለየሶላቱ ይታጠቡ ነበር፡፡ [በቡኻሪ የተዘገበ]

      4 - አንዲት ሴት በሆነ ምክንያት ደም ከፈሰሳት - ለምሳሌ የማሕጸን ቀዶ ጥገና አድርጋ ደም ቢወጣ ሁኔታዋ ከሁለት ነገር አይዘልም፡-

      ሀ- የወር አበባ የማይመጣባት መሆኑ መታወቅ፡፡

      በዚህ ሁኔታ የእስትሓዳ ብያኔ አይጸናባትም፡፡በማንኛውም ወቅት ከሶላት አትታገድም፡፡ ደሙም የመታወክና የብልሽት ደም ይሆናል፡፡ ለየሶላቱም ዉዱእ ታደርጋለች፡፡

      ለ- የወር አበባ ሊመጣባት የሚችል መሆኑ መታወቅ፡፡ ይህችኛዋን የእስትሓዳ ብያኔ ይጸናባታል፡፡

      5 - እስትሓዳ ካለባት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግን ሸሪዓው ያልከለከለ በመሆኑ ፈቀዳል፡፡

      ንፋሳ (የወሊድ ደም)

      የንፋሳ ትርጓሜ

ንፋሳ

በወሊድ ምክንያት ከሴት ማሕጸን የሚወጣ ደም፡፡

    የንፋሳ መቆያ ጊዜ

    ንፋሳ የተወሰነ አነስተኛ የመቆያ ጊዜ የለውም፤ አብዛኛው ግን አርባ ቀናት ነው፡፡ ከዚ በፊት ከቆመና ከጠራች ግን ገላዋን ታጥባ ትሰግዳለች፡፡

    ንፋሳን ከሚመለከቱ ብያኔዎች መካከል

    1 - አንዲት ሴት ወልዳ ምንም ደም ካልፈሰሳት - ይህ እጅግ በጣም አልፎ አልፎ ብቻ የሚከሰት ነው - ገላን የመታጠብ ግዴታ ሳይኖርባት ዉዱእ አድርጋ ትሰግዳለች፡፡

    2 - ደሙ ከአርባ ቀን በላይ ከቆየና በተለምዶ ከአርባ ቀን በኋላ የሚቆምላት ከሆነ፣ወይም በቅርብ እንደሚቆም የሚጠቁም ምልክት ከታየ እስኪቆም ትጠብቃለች፡፡ ደሙ ከቀጠለ ሙስተሓዳ ናትና እስትሓዳ ብያኔ ይጸናባታል፡፡

    3 - ከአርባ ቀን በፊት ደሙ ቆሞ ንጹሕ ከሆነች ገላዋን ታጥባ ትሰግዳለች፤ትጾማለች፤ከባሏ ጋርም ወሲብ ትፈጽማለች፡፡

    4 - ከአርባ ቀን በፊት ጠርታ በአርባ ቀን ገደብ ውስጥ ዳግም ከመጣባት ፡-

    ሀ- የንፋሳ ደም መሆኑን ካወቀች እሱ ነው ማለት ነው፡፡

    ለ- የንፋሳ ደም አለመሆኑን ካወቀች ግን የጠራች ሆና ትወሰዳለች፡፡

    5 - ንፋሳ የሚጸናው የሰው ልጅነት እድገቱ የተሟላ ጽንስ ከተገላገለች ብቻ ነው፡፡ አስወርዷት እድገቱ ገና ያልተሟላ ጽንስ ከሆነ ግን ሦስት ሁኔታዎች ይኖሩታል፡-

    ሀ- ከመጀመሪያዎቹ አርባ ቀናት ውስጥ የሚገኝ መሆን፡፡ ይኸ የብልሽት ደም ነውና ገላዋን ታጥባ ትሰግዳለች፣ትጾማለች፡፡

    ለ- ከሰማንያ ቀናት ዕድሜው በኋላ መሆን፡፡ ይኸ የንፋሳ ደም ነው፡፡

    ሐ- በአርባና ሰማንያ ቀናት መካከል መሆን፡፡ ይኸ ይስተዋልና ተፈጥሮው የመሟላት ምልክት ከታየበት የንፋሳ ደም ነው፡፡ ካልተስተዋለበት ግን የብልሽት ደም ነው፡፡

    በወር አበባና በንፋሳ ሐራም የሆኑ ነገሮች

    1 - ወሲባዊ ግንኙነት

    አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ከአደፍም ይጠይቁሃል፤እርሱ አስጠያፊ ነው፤ሴቶችንም በአደፍ ጊዜ ራቋቸው፤ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፤አላህ (ከኃጢአት) ተመላሾችን ይወዳል፤ተጥራሪዎችንም ይወዳል፣ በላቸው፡፡›› [አል-በቀራህ፡222]

    ነቢዩም ﷺ ፡- ‹‹ ከግብረ ስጋ ግንኙነት በስተቀር ሁሉንም ነገር አድርጉ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ጠቃሚ ነጥቦች

    1 - የወር አበባ እያለባት ከሚስቱ ጋር ወሲብ የፈጸመ ሰው ኃጢእ ነውና ከፍፋራ (ማበሻ) መክፈል ይኖርበታል፡፡ ሚስቲቱም በፈቃደኝነት እሺ ብላ ፈጽማ ከሆነ በርሷም ላይ ከፍፋራው ይጸናል፡፡

    ማበሻው ከፍፋራ በዲናር ክብደት ልክ ወይም ግማሽ ዲናር ወርቅ መክፈል ነው፡፡ በወር አበባዋ ጊዜ ውስጥ ከባለቤቱ ጋር ወሲብ የፈጸምን ሰው አስመልክቶ እብን ዐባስ (ረዐ) ከነቢዩ ﷺ ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹አንድ ዲናር ወይም ግማሽ ዲናር ምጽዋት ይሰጣል፡፡›› [በአቡዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    አንድ ዲናር 4.25ግራም ወርቅ ነው፡፡

    2 - ሚስቲቱ ከወር አበባ ብትጠራም ገላዋን አስክትታጠብ ድረስ ባል አይገናኛትም፡፡ አላህ ብሏልና ፡- ‹‹ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፤››[አል-በቀራህ፡222]

    ይህም ከወር አበባ ደም እስኪጠሩ ማለት ነው፡፡ ከዚያም አላህ ፡- ‹‹ንጹሕ በኾኑም ጊዜ››› [አል-በቀራህ፡222]

    ይላል፡፡ ይህም ገላቸውን በታጠቡ ጊዜ ማለት ነው፡፡ ከዚያም አላህ ፡- ‹‹አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፤›› [አል-በቀራህ፡222] ይላል፡፡ ይህም ከታጠቡ በኋላ ወሲባዊ ተራክቦ መፈጸም ማለት ነው፡፡

    2 - ሶላት

    ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹የወር አበባ ሲመጣ ሶላት ተዪ፤ሲሄድ ደግሞ ከራስሽ ደሙን እጠቢና ስገጅ፡፡›› [በአቡዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ጠቃሚ ነጥቦች

    1 - አንዲት ሴት ከወር አበባ ከታጠበች በኋላ ያመለጣትን ሶላት መልሳ የመስገድ ግዴታ የለባትም፡፡ ዓእሻ (ረዐ) ሴት በወር አበባ ምክንያት ጾምን ጾማ ስትከፍል ሶላትን ለምን ሰግዳ እንደማትከፍል ተጠይቀው ፡- ‹‹ይህ ነገር ያጋጥመንና ጾምን እንድንተካ ስንታዘዝ ሶላትን ሰግደን እንድንከፍል አንታዘዝም ነበር፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - አንዲት የወር አበባ ያለባት በንጽሕና ላይ ሆና የአንድ ረክዓ ያህል ጊዜ ከወቅቱ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የደረሰችበት ከሆነ መስገድ ግዴታ ይሆንበታል ፡፡

    የደረሰችበት ከወቅቱ ለአንድ ረክዓ በቂ ያልሆነ አጭር ጊዜ ከሆነ ግን ሶላቱ ግዴታ አይሆንባትም፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ከአንድ ሶላት በአንዱ ረክዓ የደረሰ ሰው ሶላቱን አግኝቶ ደርሶበታል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - ጾም

    ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹የወር አበባ ሲመጣባት አትሰግደም አትጾምም አይደለምን? ሲሉ፣(ሴቶቹ) አዎ አሉ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ጠቃሚ ነጥቦች

    አንዲት ሴት ጎሕ ከመቅደዱ በፊት ከወር አበባ ከጠራችና ከነጋ በኋላ እንጅ ያልታጠበች ብትሆን፣ ከጾመች ጾሟ ትክክለኛ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

    4 - የቁርኣንን መጽሐፍ በእጅ መንካት

    አላህ U እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹የተጥራሩት እንጅ ሌላ አይነካውም፡፡›› [አል-ዋቂዓህ፡79]

    ነቢዩም ﷺ ፡- ‹‹ንጽሕና ያለው ሰው እንጅ (ሌላው) የቁርኣንን መጽሐፍ በእጁ አይንካ፡፡›› [ማሊክ ሙወጥጠእ ውስጥ የዘገቡት] ብለዋል፡፡

    5 - ከዕባን መዞር (ጠዋፍ)

    ነቢዩ ﷺ ለዓእሻ (ረዐ) በሐጅ ላይ እያሉ የወር አበባ በመጣባቸው ጊዜ ፡- ‹‹እስክትጠሪ ድረስ በተከበረው ቤት (በከዕባ) ከመዞር በስተቀር ሐጅ አድራጊ የሚፈጽመውን ሁሉ ፈጽሚ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

    ብለዋል፡፡ ከእብን ዐባስ በተላለፈው መሰረት ፡- ‹‹(በሐጅ ስነ ሥርዓት ላይ) ሰዎች በመጨረሻ እንዲያደርጉ የታዘዙት የመሰናበቻ ጠዋፍ ማድረግን ሲሆን የወር አበባ ላለባት ሴት ግን ትእዛዙ ተቃልሏል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    6 - አቋርጦ ለመሄድ ካልሆነ መስጊድ ውስጥ መቀመጥ

    አላህU እንዲህ ብሏልና፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተ የሰከራችሁ ኾናችሁ፣የምትሉትን እስከምታውቁ፣የረከሳችሁም ስትኾኑ መንገድን አላፊዎች ካልኾናችሁ በስተቀር (አከላታችሁን) እስከምትታጠቡ ድረስ ስግደትን አትቅረቡ፡፡›› [አል ኒሳእ፡43]

    ነቢዩም ﷺ ፡- ‹‹እኔ መስጊድን የወር አበባ ላለባትም ሆነ ገላን የመታጠብ ግዴታ (ጀናባ) ላለበት ሰው (እውስጡ እንዲቆዩ) አልፈቅድም፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ጠቃሚ ነጥቦች

    1 - የወር አበባ ያለባት ሴት ጥንቃቄ ካደረገችና መስጊዱ እንዳይበከል ካልሰጋች መስጊድ ውስጥ አቋርጣ ማለፍ ምንም ለበትም፡፡ nይህ ‹‹መንገድን አላፊዎች ካልኾናችሁ በስተቀር›› [አል ኒሳእ፡43]በሚለው የአላህ ቃል አጠቃላይነት ውስጥ ይካተታል፡፡

    2 - በሁለቱ ዒዶች ወደ መስገጃው ሄደው ኹጥባውን፣መልካሙን ነገርና የሙስሊሞችን ዱዓእ መጋራት የተወደደ (ሙስተሐብ) ቢሆንም፣የወር አበባ ያለባት ሴት በዒድ መስገጃ ቦታ ላይ መቀመጥ ግን የተከለከለ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹የወር አበባ ያለባቸው ሴቶች ከመስገጀው ቦታ ገለል ይላሉ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    7 - ጦላቅ (ፍች)

    ባል ወር አበባ ያለባት ሚስቱን መፍታት ሐራም ይሆንበታል፡፡ አላህU እንዲህ ብሏልና፡- ‹‹አንተ ነቢዩ ሆይ! ሴቶችን መፍታት ባሰባችሁ ጊዜ፣ለዒዳቸው (በንጽሕና ወራታቸው መጀመሪያ ከአደፋቸው እንደጠሩ ሳትነኳቸው) ፍቷቸው፤›› [አል ጦላቅ፡1]

    ይህ ማለት ተለይቶ የሚታወቅ የመቆያ ጊዜ በሚጀምሩበት ሁኔታ ላይ ሆነው ፍቷቸው ማለት ነው፡፡

    በወር አበባ ላይ እያሉ ፍች መፈጸም ሐራምና ብድዓ ከመሆኑም ጋር ፍችው ተፈጻሚ ነው፡፡