የወርቅና የብር (የሁለቱ ጥሬ ገንዘቦች) ዘካት

10503

      የወርቅና የብር (የሁለቱ ጥሬ ገንዘቦች) ትርጓሜ

ሁለቱ ጥሬ ገንዘቦች

ሁለቱ ጥሬ ገንዘቦች ወርቅ ብርና እነሱን በመወከል ዛሬ የልውውጥ መሳሪያ የሆኑት የወረቀት ኖቶች ናቸው፡፡

    የወርቅና የብር ዘካትን የሚመለከት ብያኔ

    ዘካው ዋጅብ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹እነዚያንም ወርቅንና ብርን የሚያደልቡትን፣በአላህም መንገድ ላይ የማያወጧትን በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው፡፡›› [አል-ተውባህ፡34]

    ነቢዩም ﷺ ፡- ‹‹የወርቅም ይሁን የብር ባለቤት ሆኖ (የዘካት) ተገቢ ክፍያቸውን የማይፈጽም ሰው፣በትንሳኤው ቀን የእሳት ሰሌዳ ይዘረጋለታል፤በገሀነም እሳት ውስጥ በዚያ ጎኑ ግንባሩና ጀርባው ይግልበታል፡፡ በቀዘቀዘ ቁጥር እንደገና ተመልሶ ይግልለታል፡፡ ይህም (አላህ) በባሮች መካከል እስከሚፈርድበትና አንዱ ቀን በሃምሳ ሺህ ዓመታት በሚቆጠርበት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ከዚያ ወይ ወደ ጀነት፣ወይ ወደ እሳት የሚወስድ መንገዱን ያያል፡፡›› [በሙስሊም ተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የወርቅና የብር ዘካት ግዴታ እንዲሆን መሟላት ያለባቸው ሸርጦች

    1 - ገንዘቡ በንብረትነት ከተያዘ ዓመት የሞላው መሆን፡፡

    2 - በገንዘቡ ላይ የተሟላ የባለቤትነት መብት መኖር፡፡

    3 - መጠኑ አነስተኛውን የዘካት መክፈያ ንሷብ የሞላ መሆን፡፡

    የወርቅና የብር ዘካት የሚከፈልበት መጠን (ንሷብ)

    1 - የወርቅ የዘካት መክፈያ መጠን ሃያ ዲናር (85 ግራም) ነው፡፡

    አንድ የወርቅ ዲናር = አራት ግራም ከሩብ ሲሆን፣የዘካት

    መክፈያ መጠኑ በግራም 4.25 x 20 = 85 ግራም ንጹሕ ወርቅ ነው፡፡

    2 - የብር ንሷብ ደግሞ ሁለት መቶ ድርሃም (595 ግራም) ነው፡፡

    አንድ የብር ድርሃም = 2.975 ግራም ሲሆን፣የብር ዘካት

    መክፈያ መጠኑ በግራም 2.975 x 200 = 595 ግራም ንጹሕ ብር ነው፡፡

    3 - የወረቀት ገንዘብ (የባንክ ኖት) የዘካት መክፈያ ንሷብ ዘካው በሚወጣበት ጊዜ ባለው የወርቅ ወይም የብር ንሷብ ዋጋ ተመን ልክ ይሰላል፡፡ ያንዳቸው መጠን የዘካት መክፈያ ንሷብ ከሞላ የዘካት ግዴታ ይጸናበታል፡፡

    ምሳሌ - ያንድ ግራም ወርቅ ዋጋ 30 ዶላር ቢሆን የሀብቱ መጠን 85 x 30 = 2550 ዶላር ከደረሰ ከዚህ ገንዘብ ላይ ዘካት መክፈል ግዴታ ይሆንበታል፡፡

    የወረቀት ገንዘብ
    ብር
    ወርቅ

    የወርቅና የብር ዘካት መጠን

    በወርቅ በብርና በገንዘብ ኖቶች የሚከፈለው የዘካት መጠን የአንድ አስረኛ ሩብ = 2.5% ነው፡፡

    ከያንዳንዱ ሃያ ዲናር ወርቅ ግማሽ ዲናር ዘካ የሚወጣ ሲሆን ከዚህ ከበለጠ በዛም አነሰ በዚሁ መሰረት ሂሳቡ ይሰላል፡፡

    በየሁለት መቶ ዲርሃም ብር አምስት ድርሃም ዘካት የሚከፈል ሲሆን መጠኑ ከጨመረም በዚሁ መሰረት ሂሳቡ ይሰላል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ሁለት መቶ ድርሀም ካለህና ዓመት ከሞላው አምስት ድርሀም (የዘካት ክፍያ) አለበት፡፡ በወርቅ ሃያ ዲናር እስኪኖርህ ድረስ ምንም (የዘካት ክፍያ) የለብህም፡፡ ሃያ ዲናር ካለህና ዓመት ከሞላው ግማሽ ዲናር (የዘካት ክፍያ) አለብህ፤ከዚህ የሚበዛው በዚሁ መሰረት ሂሳቡ ይሰላል፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    - ተግባራዊ ምሳሌ :-

    አንድ ሰው 9000 ዶላር ኖሮት ገንዘቡ በርሱ ሙሉ ንብረትነት ዓመት ሙሉ ቢቆይ የዘካት ግዴታ ይኖርበታል?

    አንደኛ - የዘካት መክፈያ ንሷብ ወርቅን ወይም ብርን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንደሚከተለው ይሰላል ፡-

    የሚከፈልበት መጠን (ንሷብ) = ሰማንያ አምስት ግራም ንጹሕ ወርቅ ዘካው ግዴታ በሆነበት ቀን፣ የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ 30 ዶላር ነው ብንል 30 × 85 = 2550 ዶላር ይሆናል፡፡ ስለዚህም የዚህ ግለሰብ ገንዘብ ዘካት የሚከፈልበትን መጠን (ንሷብ) ሞልቶ አንድ ዓመት በርሱ ንብረትነት አሳልፏልና ዘካውን የመክፈል ግዴታ አለበት ማለት ነው፡፡

    ሁለተኛ - ይህ ግለሰብ መክፈል ግዴታ የሚሆንበትን የዘካት መጠን ሂሳብ እንደሚከተለው እናሰላለን ፡-

    የሚከፈለው ዘካት መጠን = 2 .5% = 9000 × 2 .5 × 100 = 250 ዶላር ሆናል፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ ከገንዘቡ 225 ዶላር ዘካ መክፈል ዋጅብ ይሆንበታል፡፡

    ወርቅና ብርን አንዱን ከሌላው ጋር ማጣመርን በተመለከተ

    አንድ ሰው ወርቅና ብር ካለውና ከሁለቱ አንዳቸውም ንሷብ የማይሞላ ከሆነ፣ሚዛን የደፋው የዑለማእ አቋም ዘካት አይከፍልም የሚለው ነው፡፡ ሁለት የተለያዩ ዓይነቶች በመሆናቸው ወርቅም ለብቻው ብርም ለብቻው ይከፈልበታል እንጂ አንዱን ከሌላው ጋር አጣምሮ ንሷብ በመሙላት አንድ ላይ ዘካት አይከፈልባቸውም፡፡ ንሷብ እንዲሞላ ለማድረግ ተብሎ ሁለቱን አንድ ላይ ማጣመርን የሚያስረዳ ማስረጃ አልተላለፈም፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ከአምስት ወቄት ባነሰ ላይ ሰደቃ (የዘካት ክፍያ) የለበትም፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡ ወርቅና ብርን ያጣመሩት ከአምስት ወቄት ባነሰ ብር ላይ የዘካት ግዴታ ጥለዋል ማለት ነው፡፡

    የጌጣጌጥ ዘካት

    ጌጣጌጥ በሁለት ይከፈላል ፡- አንደኛው የወርቅና የብር ጌጣጌጥ ሲሆን፣ሌላው ወርቅና ብር ያልሆኑ ጌጣጌጦች ናቸው፡፡

    1 - የወርቅና የብር ጌጣጌጥ

    አንደኛው ዓይነት ፡ ለጥሪትነትና ለድልብነት የሚቀመጥ፣ ወይም ለንግድ ዓላማ ተብሎ የሚያዝ ሲሆን በነዚህ ዘካት መክፈል ዋጅብ ነው፡፡

    ሁለተኛው ዓይነት ፡ ለጌጥነት ለመጠቀምና ለአገልግሎት ዓላማ የሚያዝ ሲሆን ራስን ነጻ ለማድረግና ለጥንቃቄ ሲባል በዚህም ዘካት መክፈል ተመራጭ ነው፡፡ አንዲት ሴት በእጇ ሁለት ወፋፍራም የወርቅ አምባር ካደረገች ሴት ልጇ ጋር ወደ ነቢዩ ﷺ መጣችና ‹‹የዚህን ዘካ ትከፍያለሽን?›› አሏት፡፡ የለም አልከፍልበትም አለቻቸው፡፡ ‹‹አላህ በትንሳኤው ቀን ሁለት የ(ገሀነም) እሳት አምባሮችን ቢያጠልቅልሽ ደስ ይልሻልን?›› ሲሉ አወለቀቻቸውና ለነቢዩ ﷺ ሰጥታ ‹‹ሁለቱም ለአላህና ለመልእክተኛው ﷺ ይሁኑ›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] አለች፡፡

    ለልማትና እርባታ የታለመ ገንዘብ ሳይሆን ልክ እንደ አልባሳትና የቤት እቃዎች ሁሉ ግላዊ መገልገያና መጠቀሚያ፣ለሴቶች የሚያስፈልጉ ጌጦች በመሆናቸውና በመሰረቱ ዘካ እንዲከፈልበት ገንዘብ የሚራባ ወይም መራባትና መልማት የሚችል መሆን ስለሚኖርበት፣ ከዑለማእ መካከል በጌጣጌጥ ዘካት መክፈልን ግዴታ የማያደርጉ አሉ፡፡

    ለጥንቃቄ ሲባል ግን ለተፈቀደ አገልግሎትና ለጌጣጌጥነት በተዘጋጀው ላይ ዘካ መክፈሉ ተመራጭ ነው፡፡ ይኸኛው አቋም ይበልጥ ጠንቃቃና ራስን ከኃላፊነት ነጻ የሚያደርግ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹የሚያጠራጥርህን ነገር ለማያጠራጥርህ ነገር ተወው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    የብር ጌጣጌጥ
    የወርቅ ጌጣጌጥ

    2 - ወርቅና ብር ያልሆኑ ጌጣጌጦች

    ይህ እንደ አልማዝ፣የከበረ ድንጋይና ዕንቁን የመሳሰለው ሲሆን ዋጋቸው የፈለገውን ያህል ከፍተኛ ቢሆን ለንግድ ዓላማ የተዘጋጁ ካልሆነ በስተቀር ዘካት አይከፈልበትም፡፡ ለንግድ ዓላማ የታቀደ ከሆነ በንግድ እቃዎች ገንዘብ ዘካት ውስጥ ይጠቃለላል፡፡

    ዕንቁ
    የከበረ ድንጋይ
    አልማዝ