ዘካት ድንጋጌውና ሸርጦቹ

3317

      የዘካት ትርጓሜ

የዘካት የቋንቋ ትርጉም

መጨመርና መፋፋት ማለት ነው፡፡

የዘካት ሸሪዓዊ ትርጉም

በተወሰነ መጠን በተወሰነ ጊዜ ለተወሰነ ክፍል የሚከፈል ገንዘብ ነው፡፡

      ዘካት የሚይዘው የላቀ ደረጃ

      ዘካት እስላም ከደነገጋቸው ግዴታዎች አንዱ ሲሆን ሦስተኛው የእስላም ማእዘን ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፤ዘካትንም ስጡ፤›› [አል-ኑር፡56]

      ነቢዩም ﷺ ፡- ‹‹እስላም በአምስት (ማእዘኖች) ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ (እነሱም) ፡- ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ የርሱ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንቡን ጠብቆ አዘውትሮ መስገድ፣ዘካን መስጠት፣ የሐጅ ሥርዓተ ጸሎት መፈጸምና ረመዷንን መጾም ናቸው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      ዘካት የማይከፍሉትን የሚመለከት ብያኔ

      አንድ ሰው ዘካን የማይከፍለው ወይ ግዴታነቱን የሚክድ በመሆኑ ነው፣ወይ ደግሞ በንፉግነቱ ምክንያት ነው፡፡

      1 - ግዴታነቱን በማስተባበል ዘካትን የከለከለ ሰው

      የዘካን ግዴታነት ያስተባበለ ሰው፣ግዴታነቱን እያወቀ ከሆነ አላህንና መልእክተኛውን አስተባብሏልና በምልዓተ ኡማው ሙሉ ድምጽ ካፍር ሆኗል፡፡

      2 - በንፉግነቱ ዘካን የከለከለ ሰው

      በገንዘብ ወዳድነቱና በንፉግነቱ ዘካን የከለከለ ሰው ተገዶ እንዲከፍል ይደረጋል፣ከከባዳ ኃጢአቶችና ከአስከፊ ወንጀሎች አንዱን የፈጸመ ቢሆንም በዚህ ካፍር አይሆንም፡፡ ነቢዩﷺ ዘካት የሚከለክሉ ሰዎችን አስመልክተው ፡- ‹‹የወርቅም ይሁን የብር ባለቤት ሆኖ (የዘካት) ተገቢ ክፍያቸውን የማይፈጽም ሰው፣በትንሳኤው ቀን የእሳት ሰሌዳ ይዘረጋለታል፤በገሀነም እሳት ውስጥ በዚያ ጎኑ ግንባሩና ጀርባው ይግልበታል፡፡ በቀዘቀዘ ቁጥር እንደገና ተመልሶ ይግልለታል፡፡ ይህም በባሮች መካከል እስከሚፈረድና አንዱ ቀን በሃምሳ ሺህ ዓመታት በሚቆጠርበት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ከዚያ ወይ ወደ ጀነት፣ ወይ ወደ እሳት የሚወስድ መንገዱን ያያል፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      አልከፍልም ብሎ ከተዋጋ ለአላህ ትእዛዝ ተገዥ እስኪሆን ድረስ ይወጋል፡፡ አላህ ፡- ‹‹ቢጸጸቱም፣ሶላትንም ቢሰግዱ፣ዘካንም ቢሰጡ፣የሃማኖት ወንድሞቻችሁ ናቸው፤አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡›› [አል-ተውባህ፡5] ብሏልና፡፡

      ነቢዩምﷺ ፡- ‹‹ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድም መልእክተኛው መሆኑን እሰኪ መሰክሩ፣ሶላትንም ደንቡን አሟልተውና አዘውትረው እስኪሰግዱና ዘካትንም አስኪከፍሉ ድረስ ሰዎችን እንድዋጋ ታዝዣለሁ፡፡ ይህንን ካደረጉ በእስላም መብት ካልሆነ በስተቀር ደማቸውንና ገንዘባቸውን ከኔ ጠብቀዋል፣በተቀረው ምርመራቸው በአላህ ዘንድ ነው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      አቡ በክር (ረዐ) ዘካት መክፈል እምቢ ያሉ ሰዎችን ተዋግተዋል፡፡ አንዲህም ብለዋል፡- ‹‹በአላህ እምላለሁ ሶላትንና ዘካትን የለያየን ሰው እዋጋለሁ፤ዘካት ከሀብት የሚወሰድ መብት ነውና፡፡ በአላህ እምላለሁ ለአላህ መልእክተኛ ﷺ ይሰጡ የነበረውን የግመል ማሰሪያ ገመድ ቢከለክሉኝ በመከልከላቸው እዋጋቸዋለሁ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]

      ዘካትን ግዴታ ከማድረጉ ጀርባ ያለው ጥበብ

      1 - የከፋዩን ነፍስ ከንፉግነት ቆሻሻ፣ከኃጢአትና ከጥፋት ደዌ ማጽዳትና ማጥራት፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ከገንዘቦቻቸው ስትሆን በርሷ የምታጠራቸው እና የምታፋፋቸው የሆነችን ምጽዋት ያዝ፤›› [አል-ተውባህ፡103]

      2 - ገንዘብን የሚያጸዳ፣ሀብትን የሚያፋፋና በረከት እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑ፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሰደቃ (የዘካት ክፍያ) ከንብረት ምንም ነገር አያጎድልም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      3 - አንድ የአላህ ባሪያ ለአላህ ትእዛዛት ያለውን ተገዥነትና የአላህን ፍቅር ከገንዘብ ፍቅር የሚያስቀድም መሆን አለመሆኑን መፈተን፡፡

      4 - ያጡትን በመርዳት፣ድሆችን በማገዝና የችግረኞችን ችግር በመቅረፍ በሙስሊሙ ሕብረተሰብ መካከል መዋደድን፣መተሳሰብንና እስላማዊ ተራድኦን በከፍተኛ ደረጃ እውን ማድረግ፡፡

      5 - በአላህ መንገድ መለገስንና አላህ ከሰጠው ለሌሎች ማካፈልን ማለማመድ፡፡

      የዘካት ትሩፋት

      1 - የአላህን እዝነትና ርህራሄውን ለማግኘት ምክንያት ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹ችሮታየም ነገሩን ሁሉ ሰፋች፤ለነዚያም ለሚጠነቀቁ ዘካንም ለሚሰጡ . . በእርግጥ እጽፋታለሁ፡፡›› [አል-አዕራፍ፡156]

      2 - የአላህን እገዛ ለማግኘትም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ‹‹አላህም ሃይማኖቱን የሚረዳውን ሰው፣በእርግጥ ይረዳዋል፤ አላህ ብርቱ አሸናፊ ነውና፡፡ (እነርሱም) እነዚያ በምድር ላይ ብናስመቻቸው፣ሶላትን እንደሚገባ የሚያስተካክሉ፣ዘካንም የሚሰጡ፣›› [አል-ሐጅ፡40-41]

      3 - ለኃጢአቶች መታበስ ምክንያት ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋ ሁሉ ምጽዋት (ሰደቃ) ኃጢአትን ያጠፋል፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

      ዘካት የሚከፈልባቸው ንብረቶች

      1-ከመሬት የሚወጣ ጠቃሚ ሀብት ዘካት

      2-የወርቅና የብር (የሁለቱ ጥሬ ገንዘቦች) ዘካት

      3-የንግድ እቃዎች ዘካት

      4-የቤት እንስሳት ዘካት


      ዘካን ግዴታ የሚያደርጉ ቅድመ ሁኔታዎች

      1 - እስላም

      አላህ የካፍሮችን ሥራ የማይቀበል በመሆኑ፣ዘካት ከካፍር ተቀባይነት የለውም፡፡

      2 - ነጻነት

      የጫንቃ ተገዥ ንብረት የጌታው ንብረት በመሆኑ ዘካት ግዴታ አይሆንበትም፡፡

      3 - ንብረቱ ዘካት የሚከፈልበት መጠን (ንሷብ) የደረሰ መሆን

      ንሷብ ትርጓሜ

ንሷብ

እዚያ ሲደርስና ሲሞላ ዘካት መክፈል ግዴታ የሚሆንበት የተወሰነ የሀብት መጠን ነው፡፡

      ለንሷብ መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ

      ሀ) ንሷቡ ለአንድ ሰው የግድ አስፈላጊ ከሆኑ እንደ ምግብ፣ልብስና መጠለያ ካሉ መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚተርፍ መሆን፡፡ ዘካት ግዴታ የተደረገው ድሆችን ለመርዳት በመሆኑ የባለ ገንዘቡ ፍላጎትም የተሟላ መሆን ግዴታ ይሆናል፡፡

      ለ) ንሷቡ ያንድ የተወሰነ ግለሰብ አንጡራ ንብረት መሆን፣ያንድ ግለሰብ ሙሉ ንብረት ባልሆነ ሀብት ላይ ዘካት ግዴታ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ ያህል ለመስጊድ ሥራ የተሰበሰበ ገንዘብ፣ወይም ለሕዝብ አገልግሎት የተለገሰ የወቅፍ (ኢንደውመንት) ገንዘብ፣በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሂሳብ ውስጥ የሚገኝ ገንዘብ፡፡

      4 - ገንዘቡ በንብረትነት ከተያዘ ዓመት የሞላው መሆን

ዓመት

አንድ ሙሉ የህጅሪያ ዘመን አቆጣጠር ዓመት ነው፡፡

    ይህም የዘካት መክፈያ ንሷብ የሞላው ንብረት በባለቤቱ እጅ ለአስራ ሁለት የጨረቃ አቆጣጠር (lunar month) ወራት የቆየ መሆን ማለት ነው፡፡ ይህ ቅድመ ሁኔታ ወርቅና ብርን፣የንግድ እቃዎችን፣ግመልና የቀንድ ከብትን፣በግና ፍየልን ብቻ የሚመለከት ሲሆን የአዝርዕትና የእርሻ ውጤቶች እንዲሁም ማዕድናትና የተቀበሩ ንብረቶች ዓመት የመሙላት ሸርጥ አያስፈልጋቸውም፡፡